ሩሲያ ውስጥ 23 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ተሰረቀ

በሩሲያ በሌቦች የተሰረቀው ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Life Novosti

በሩሲያዋ መርማንስክ ተብላ በምትታወቀው የአርክቲክ ግዛት ውስጥ አንድ የባቡር ሃዲድ ተዘርግቶበት የነበረ የብረት ድልድይ በመሰረቁ ምርመራ ሊጀመር ነው።

የግዛቲቱ አቃቤ ሕግ እንዳለው 23 ሜትር ርዝመትና 56 ቶን ክብደት ያለው የብረት ድልድይ ባልታወቁ ሰዎች ነው የተሰረቀው።

ይህ ብዙም አግልግሎት አይሰጥም ነበር የተባለው ድልድይ ከግዛቲቱ ዋና ከተማ በ170 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ በደን የተሸፈነ ስፍራ ላይ የሚገኝ እንደነበር የአካባቢው ጋዜጣ ዘግቧል።

ተነቅሎ የተወሰደው ድልድይ በአካባቢው ይወጣ የነበረን ለየት ያለ ማዕድን የሚያመላልሱ ባቡሮች ይተላለፉበት የነበረ ሲሆን የማዕድን ማምረቻው ከአሥር ዓመታት በፊት ከስሮ በመዘጋቱ ብዙም እንቅስቃሴ አይደረግበትም ነበረ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ድልድዩ ከነበረበት ቦታ እንደሌለ ያወቁት ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ነው።

በማሕበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚዘዋወሩት ምስሎች እንደሚያሳዩት የድልድዩ ዋነኛ ክፍል ከቦታው የለም። የተወሰነው አካሉ ግን በወንዙ መሃል ላይ ይታያል። ይህም ዘራፊዎቹ መጀመሪያ ድልድዩን አፍርሰው ወንዙ ውስጥ እንዲወድቅ ካደረጉ በኋላ ብረቱን እየለያዩ አንድ በአንድ ሳይወስዱት እንዳልቀረ ተገምቷል።

ምንም እንኳን በድልድዩ ላይ የተፈፀመው ዝርፊያ ለየት ያለና ግዙፍ ቢሆንም ያስከተለው ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ ከዘጠኝ ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደማይበልጥ በመጥቀስ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ አንድ ድረ-ገጽ ዘግቧል።

በማቅለጥ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ሲባል ሩሲያ ውስጥ ከብረት የተሠሩ ነገሮች ላይ የሚፈፀም ዝርፊያ ከረዥም ጊዜ አንስቶ ችግር ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት 10 ሜትር ርዝመት ያለው የሶቪየት ዘመን ፀረ-አውሮፕላን ሚሳዔል ከወዳደቁ ብረቶች ጋር ተሽጦ ማቅለጫ ውስጥ መፈንዳቱ ይታወሳል።