ሩሲያዊው ኩባንያ ሴት ሰራተኞቹ ቀሚስ እንዲለብሱ በመክፈሉ እየተወቀሰ ነው

የፎቶው ባለመብት, Tatprof
አንድ የሩሲያ ኩባንያ ሴት ሰራተኞቹ ቀሚስ እንዲለብሱ ተጨማሪ መክፈሉ ከፍተኛ ወቀሳ እየቀረበበት ነው።
ታት ፐሮፍ የተባለው የአሉሙኒየም አምራች ኩባንያ "የሴትነት ማራቶን" (ውድድር) በሚል ባዘጋጀው ዘመቻ ነው ይህንንም እያካሄደ ያለው
ከጉልበታቸው በታች አምስት ሳንቲሜትር ቁመት የማይረዝም አጭር ቀሚስ የለበሱ ሴቶች ከደመወዛቸው በተጨማሪ መቶ ሩብል ወይም አርባ አምስት ብር ይከፈላቸዋል።
ገንዘቡንም ለማግኘት ፎቷቸውን ለኩባንያው መላክ ይጠበቅባቸዋል።
በብዙ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ወቀሳን እያስተናገደ ያለው የኩባንያው አሰራር የሴቶችን አስከፊ አያያዝ ያሳየ ነው ተብሏል።
ታዋቂዋ የፌሚኒስት ጦማሪና ጋዜጠኛዋ ዛሊና ማርሽንኩሎቫ ይህንን ጅማሮም "ያረጀ ያፈጀ" በማለት ወርፋዋለች።
ኩባንያው በበኩሉ በፆተኝነት ሊወቀስ እንደማይገባና ስልሳ ሴቶችንም ያሳተፈ እንደሆነ ለኃገሪቱ ሚዲያ ገልጿል።
"የስራ አካባቢያችንን ብሩህ ለማድረግ የተጠቀምንበት ዘዴ ነው" በማለት የኩባንያው ቃል አቀባይ ጎቮሪት ሞስክቫ ለተባለ የሬድዮ ጣቢያ ገልፀዋል።
"ሰባ ፐርሰንት ሰራተኞቻችን ወንዶች ናቸው፤ እንዲህ አይነት ዘመቻዎች ህብረትን ለመፍጠር ይጠቅማሉ" ብለዋል።
አክለውም " ሴት ሰራተኞቻችን አብዛኛውን ጊዜ ወደ ስራ ቦታ የሚመጡት ሱሪ ለብሰው ነው፤ ለዚህም ነው የሴት ሰራተኞቻችንን ግንዛቤ በመጨመር ሴትነታቸውንና ማራኪነታቸው እንዲሰማቸው ቀሚስ እንዲለብሱ የምናበረታታው"
ሩሲያዊያን የትዊተር ተጠቃሚዎች ግን የኩባንያውን ዘመቻ በቀላል አላዩትም "ፆተኛ" የሚሉና እንዲሁም ሌሎችን ትችቶች አስተናግዷል።
" ወንዶች በሚበዙበት መስሪያ ቤት ውስጥ አጭር ቀሚስ ለለበሰችና ሜካፕ ለተቀባች ሴት አርባ አምስት ብር ተጨማሪ መስጠት ምን ማለት ነው? ፌሚኒዝም ምን ያደርግልናል ሴቶች ገንዘብ ተከፍሏቸው ወንዶችን ማስደሰት እየቻሉ" በማለትም በምፀት የወቀሷቸውም አልታጡም።












