በገዛ አገሩ ኤምባሲ ውስጥ የተገደለው ጋዜጠኛ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጀማል ባለፈው ማክሰኞ በቱርክ ኢንስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ ቀጠሮ ነበረው። የጋብቻ ጉዳዮችን ለመጨራረስ፤ የቀድሞው ባለቤቱን የፍቺ ጉዳይ ለመዝጋት አዲሷን ቱርካዊት ባለቤቱን አስከትሎ ወደዚያ ሄደ። "ደጅ ጠብቂኝ መጣሁ" አላት። በዚያው አልተመለሰም።
የመጀመርያው ጥርጣሬ ሳዑዲ አፍና ወደ አገሯ ልካዋለች የሚል ነበር። አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን እዚያው ቆንስላው ውስጥ በምስጢር እንደተገደለ ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው።
ሳዑዲያዊው ጀማል ካሹጊ ቀደም ባሉት ዘመናት የንጉሣዊው ቤተሰብን እስከማማከር የደረሰ ሰው ነበር። የኋላ ኋላ ግን የመብት ጥያቄዎችን በማንሳቱ ጥርስ ውስጥ ገባ። ነገሩ አላምር ሲለው ወደ ቱርክ ሸሸ። ላለፉት ዓመታት የሳዑዲን አፋኝ አስተዳደር ሲነቅፍ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቱርክ ባለሥልጣናት ከሳዑዲ ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላለማቆርፈድ ዝምታን መርጠው የነበረ ሲሆን ትናንት ግን ዝምታውን ሰብረውታል። ጀማል በቆንስላው ሳለ ተገድሏል ብለዋል ለቢቢሲ። ሳዑዲ ግን "ዜጋዬን እየፈለኩት ነውና አፋልጉኝ" ስትል ፌዝ የሚመስል መግለጫን አውጥታለች።
አቶ ጀማል ካሹጊ ስመ ጥር ጸሐፊ ሲሆን በተለይም ለዋሺንግተን ፖስት አምደኛ በመሆን ይታወቃል።
አብራው ወደ ሳኡዲ ቆንስላ ሄዳ የነበረችውን ባለቤቱ "ምናልባት ካልተመለስኩ በዚህ ስልክ ቁጥር የረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ረዳት ለሆነ ሰው ደውለሽ ተናገሪ" ብሏት እንደነበር ገልጻለች።












