ክለባቸውን ሊለቁ የሚችሉ ዘጠኝ የፕሪምየር ሊጉ ተጫዋቾች

የዘንድሮው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የፊታችን ሃሙስ በይፋ ይዘጋል። ብዙ የእንግሊዝ ክለቦች የመጨረሻው ቀን ከመድረሱ በፊት ይጠቅሙኛል ያሏቸውን ተጨዋቾችን ለማስፈረም እየተሯሯጡ ነው።

ቶተንሃም በመጨረሻም ተጫዋች ያስፈርም ይሆን? የማንቸስተሩ አንቶኒ ማርሻል ወደ ሌላ ክለብ ይዘዋወር ይሆን?

በዚህኛው የዝውውር መስኮት ክለቦቻቸውን ሊለቁ የሚችሉ ዘጠኝ የፕሪምየር ሊጉ ተጫዋቾችን እንመልከት።

ቶቢ አልደርዌረልድ (ቶተንሃም)

ቤልጂየማዊው ተከላካይ ባለፈው ዓመት ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በቶተንሃም የቋሚ አሰላለፍ ቦታ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። ኮንትራቱ በዚህ ዓመት የሚጠናቀቀው አልደርዌረልድ፤ ስሙ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እየተያያዘ ነው። ለተጫዋቹ የቀረበው የመግዣ ዋጋ ደግሞ 75 ሚሊዮን ፓውንድ ነው።

ጃክ ግሬሊሽ (አስቶን ቪላ)

የ21 ዓመቱ እንግሊዛዊ ግሬሊሽ በቻምፒዮንሺፑ አስቶን ቪላ ላደረገው ግስጋሴ ከፍተኛ አስተዋጸኦ አድርጓል። ክለቡ በአሁኑ ሰአት የገንዘብ እጥረት ያጋጠመው ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ ቶተንሃሞች ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ተዘጋጅተዋል። አስቶን ቪላ ግን ቶተንሃሞች ያቀረቡትን ዋጋ እጥፍ እየጠየቁ ነው።

ዳኒ ኢንግስ (ሊቨርፑል)

በአንድ ወቅት እንግሊዝ ካፈራቻቸው ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ ተብሎ ሲወደስ ነበረው ዳኒ ኢንግስ ሊቨርፑል ባሳለፋቸው ሶስት ዓመታት እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል። በባለፈው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም አንድ ጊዜ ብቻ ነው ግብ ማስቆጠር የቻለው።

ሊቨርፑሎችም ለተጫዋቹ የ20 ሚሊዮን ፓውንድ መሸጫ ዋጋ ለጥፈውበታል። ተጫዋቹን በጥብቅ ከሚፈልጉት ክለቦች መካከል ደግሞ ክሪስታል ፓላስ የመጀመሪያውን ስፍራ ይዟል።

ሃሪ መጓየር (ሌስተር ሲቲ)

በተለይ በአለም ዋንጫው ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ያሳየው ወጥና አስገራሚ አቋም በአሁኑ ሰአት ይህን ተከላካይ ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል።

የሃሪ መጓየር ዋነኛ ፈላጊ ደግሞ የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪንሆ ናቸው። ለተጫዋቹም እስከ 56 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተጫዋቹ ባለቤት ሌስተር ሲቲ ደግሞ ለተከላካዮች ሪከርድ የሆነ 80 ሚሊዮን ፓውንድ ጠይቀዋል።

አንቶኒ ማርሻል (ማንቸስተር ዩናይትድ)

ከአሌክሲስ ሳንቼዝ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ መምጣት በኋላ አንቶኒ ማርሻል የቋሚ አሰላፍ ቦታ ለማግነት ተቸግሮ የቆየ ሲሆን፤ ለአለም ዋንጫው በብሄራዊ ቡድኑ አለመካተቱ ደግሞ ክለቡን እንዲለቅ ምክንያት ሊሆነው እንደሚችል ተገልጿል።

በሌላ በኩል ተጫዋቹ ሁለተኛ ልጅ ሲወለድለት የቅድመ ውድድር ጨዋታውን ጥሎ ወደ ፈረንሳይ መመለሱ የማንቸስተሩ አሰልጣን ሆዜ ሞሪንሆን ያስደሰታቸው አይመስልም። መሸጫ ዋጋውም እስከ 80 ሚሊዮን ፓውንድ ይደርሳል ተብሏል።

ሲሞን ሚኞሌ (ሊቨርፑል)

ቤልጂየማዊው ግብ ጠባቂ በሊቨርፑል ቤት የቋሚ አሰላለፍ ቦታውን በካሪየስ ተነጥቆ ነው የቆየው። አሁን ደግሞ ብራዚላዊውን ግብ ጠባቂ አሊሰን ከሮማ ማስፈረማቸው ደግሞ የተጠባባቂውን ቦታ እንኳን እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል።

በአስገራሚ ሁኔታ የላሊጋው አሸናፊ ባርሴሎናዎች በግብ ጠባቂው ላይ ፍላጎት አሳይተዋል።

አሮን ራምሴ (አርሰናል)

ዌልሳዊው አማካይ ራምሴ በአርሰናል ቤት 10 ዓመት የቆየ ሲሆን፤ 300 ጨዋታዎችን ደግሞ ለክለቡ አድርጓል። አዲሱ የአርሰናል አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሪ ራምሴን ጠቃሚ ተጫዋች ነው ብለው ቢገልጹትም፤ ከቼልሲ የቀረበላቸው የ35 ሚሊዮን ፓውንድ መገዣ ዋጋ እና የሊቨርፑል ፍላጎት ሃሳባቸውን ሊያስቀይራቸው እንደሚችል ይገመታል።

ዊሊያን (ቼልሲ)

ይህ የማይደክመው የሚባልለት የክንፍ ተጫዋች በአለም ዋንጫው ለሃገሩ ብራዚል በአምስቱም ጨዋታዎች በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ችሏል። ባለፈው ዓመት ቼልሲ በኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ከማንቸስተር ይናይትድ ጋር ሲጫወቱ በቀድሞው አሰላጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ተጠባባቂ ቦታ ላይ መቀመጡ ደግሞ ልቡን እንዳስሸፈተው ይገመታል።

የተጫዋቹ ዋነኛ ፈላጊ ሆነው እየተፎካከሩ ያሉት ደግሞ ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎና እና ማንቸስተር ዩናይትድ ሲሆኑ፤ 65 ሚሊዮን እንዲፍሉ ተጠይቀዋል።

ዊልፍሬድ ዛሃ (ክሪስታል ፓላስ)

ምንም እንኳን የባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹን ስድስት ጨዋታዎች ለቡድኑ መሰለፍ ባይችልም፤ ከዚያ በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ግን ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥሮ ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ አቀብሏል።

አሰልጣኝ ሮይ ሆድሰን ኮትዲቯራዊውን ተጫዋች በቡድናቸው ለማስቀረት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ ከተለያዩ ክለቦች እየቀረበላቸው ያለው ከፍተኛ ገንዘብ ሃሳባቸውን ሊያስቀይራቸው እንደሚችል ይገመታል።