ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የኒውክሌር የጦር መሳሪያ የመጠቀም እቅድ የላትም- የዩኬ አምባሳደር
በብሪታንያ የሩሲያ አምባሳደር ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አገራቸው ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ስልታዊ (ታክቲካል) የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ትጠቀማለች ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
አምባሳደር አንድሬ ኬሊን እንደገለጹት በሩሲያ ወታደራዊ ሕጎች መሰረት እንደዚህ ባሉ ግጭቶች ውስጥ እንደ ኒውክሌር ያሉ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ አይውሉም።
ሩሲያ የኒውክሌር የጦር መሳሪያን አጠቃቀምን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ እንዳላት የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ በዋነኝነት የግዛቲቱ ህልውና አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስረድተዋል።
"ከአሁኑ ዘመቻ ጋር ግን ምንም ግንኙነት የለውም" ሲሉ አምባሳዳሩ በዛሬው ዕለት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ብዙም ሳይቆይ በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ የኒውክሌር ኃይላቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም ሲያዙ ብዙዎች ማስጠንቀቂያ ነው በሚል ነበር ያዩት።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ጦርነቱ ለደረሰበት ደረጃ ተጠያቂው የምዕራቡ አለም እንዲሁም የኔቶ ጸብ አጫሪነት ነው ይላሉ።
ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በበኩላቸው "በዩክሬን ውስጥ እየተከሰተ ካለው ችግር" አለምን ለማዘናጋት የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ስልታዊ (ታክቲካል) የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች "ስትራቴጂካዊ" ከሚባሉት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በተቃራኒ በአጭር ርቀት ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
'ስትራቴጂክ' የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እጅግ በጣም ረጅም ርቀት ላይ የሚተኮሱ እና አጠቃላይ የኒውክሌር ጦርነትን የሚያስነሱ ናቸው።
ነገር ግን 'ታክቲካል' ኒውክሌር ሲባል በጦር ሜዳ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ትናንሽ ቦምቦችን እና ሚሳኤሎችን ጨምሮ ብዙ አይነት መሳሪያዎችን ያካትታል።
ሩሲያ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳላት ይታሰባል።
አምባሳደሩ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ከረር ያለ ንግግር የሩሲያ ጦር በቡቻ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት አድርሷል ተብሎ የተከሰሰበት "የጦር ወንጀሎች" "ፈጠራ" ነው ብለዋል።