ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ከምታደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ምን ያህል ተጠቃሚ ናት?
በያዝነው ወር ግንቦት 2003 ዓ.ም ነበር ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገር ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የጀመረችው።
በአፍሪካ የልማት ባንክ በ95 ሚሊዮን ዶላር የብድር ድጋፍ በተገነባው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር የመጀመሪያው ዓመታዊ 22 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለጅቡቲ በመሸጥም የኃይል ወጪ ንግድ ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት ተበሰረ።
የግልገል ጊቤ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት በመዘጋቱ ከታቀደው አንድ አመት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው።
በወቅቱ የነበረው የኃይል ሽያጭም ለአገሪቱ በአማካኝ በዓመቱ 10 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝላት የአገራትን ምጣኔ ኃብት ትንበያዎችን እንዲሁም ጥልቅ ዳሰሳዎችን የሚያዘጋጀው ኢኮኖሚክ ኢንተለጀንስ ዩኒት በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት አስነብቧል።
በሪፖርቱ መሰረት ከጂቡቲ ከሚገኘው ገቢም የተወሰነውን በገጠር ያሉ ህዝቦቿ መብራት እንዲያገኙ፣ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ያለውንም የኃይል ተደራሽነት ለማሳደግ እቅድ ተይዞ ነበር።
ከአስር ዓመት በኋላ በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 90 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ችላለች።
ለጂቡቲ በ22 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የጀመረችው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን የአስር አመት ፍኖተ ካርታን አዘጋጅታለች።
በዚህ የቀጣይ አስር ዓመታት ይተገበራል በተባለው የኢነርጂ ልማት መሰረት አገሪቷ በ2022 የምታመነጨውን የኃይል መጠን ወደ 20 ሺህ ማሳደግ እንዲሁም ለጎረቤት አገራት የምትሸጠውን የኃይል መጠንም ወደ 7 ሺህ 184 ጊዋስ (GWH) ለማድረስ ታቅዷል።
በአሁኑ ወቅት ለጎረቤት አገራቱ ሱዳንና ጂቡቲ አመታዊ የኃይል ሽያጭ የምታቀርብ ሲሆን ለኬንያም የኃይል ሽያጭ ለመጀመር የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታን ግንባታን ካጠናቀቀች አንድ አመት ሆኗታል፤ ፍተሻውም የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ እንደሚጀመርም ይጠበቃል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የወጪ ንግድ
ከውሃ ሃይል፣ ነፋስ፣ እንፋሎት፣ የጸሃይ ብርሃንንን በመጠቀም የንጹህ ኃይል አምራች ለመሆን እቅድ ይዛ ያለችው ኢትዮጵያ በዚህም ማሳካት የምትፈልገው ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ማዕከል መሆንን ነው።
ከጎረቤት አገራት ጋር የኃይል ትስስር በመፍጠርም ለጂቡቲና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ በአማካኝ በየአመቱ 70 ሚሊዮን ዶላር ገቢን ለማግኘት እየሰራች ትገኛለች።
ለሁለቱ አገራት የምትልከው የኃይል መጠን ባለው ስምምነት መሰረት በ100 ሜጋ ዋት የሽያጭ ማዕቀፍ ሲሆን የተወሰነ ከፍና ዝቅ ማለት እንዳለም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ያስረዳሉ።
ከ100 ሜጋ ዋት በላይም ይሁን በታች እንደቆጠረው ሁኔታ አገራቱ ክፍያቸውን ይፈጽማሉ።
በባለፉት ዘጠኝ ወራት ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ መረጃ በምናይበት ወቅት ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኩባንያ ወደ 746.9 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የመሸጥ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከእቅዱ በ4 በመቶ ብልጫ ያለው 774.2 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ወጪ ንግድ ተካሂዷል።
በተጨማሪ ወደ ጂቡቲ 385 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም 427.1 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ሽያጭ በመደረጉ ከእቅዱም 11 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
በዚህም ለሱዳን ከተሸጠው ኃይል 38.7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለጂቡቲ ከተሸጠው ደግሞ 27.8 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይም በዘጠኝ ወራት ከኃይል ሽያጭ 67 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተገኝቷል።
ገቢው ከእቅዱ አንፃር ሲታይ የሱዳን ኤሌክትሪክ ኩባንያ የተጠቀመው 4 በመቶ ጭማሪ፣ የጅቡቲ ደግሞ 15 በመቶ ገደማ ጭማሪ ማሳየቱን አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
በየዓመቱ ለጎረቤት አገራት በጅምላ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 70 ሚሊዮን ዶላር ቢታቀድም በአመታት ውስጥ ጭማሬ እያሳየ መምጣቱንም የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሞገስ መረጃዎችን በማጣቀስ ያስረዳሉ።
እስካሁን ድረስ ባለው ከፍተኛ የተመዘገበው በባለፈው ዓመት ሲሆን በ2013 ዓ.ም ሲሆን ከነበረው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ወደ 90 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተገኝቷል።
በአመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም እንዲሁም ገቢውም ጨምሯል።
ሆኖም ከሁለት አመታት በፊት የአገሪቱ የኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውሃ ባለመያዛቸው ምክንያት በተፈጠረው ዕጥረት ለወራት ያህል ለሱዳን አቅርቦት ከማቋረጥ በተጨማሪ ኤሌክትሪክ በፈረቃ መከፋፈል ተጀምሮ ነበር።
በዝናብ እጥረት ምክንያት በተፈጠረው ችግር በደቡብ እና በምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት ሦስት ግድቦች ቆቃ፣ መልካ ዋከናና ጊቤ ሶስት በቂ ውሃ እንዳይዙ አድርጓቸዋል።
በወቅቱ ሱዳን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እንደነበራት የሚያወሱት አቶ ሞገስ፣ የአገር ውስጥ ፍላጎት ባለመሟላቱና ወደ ፈረቃ በመገባቱም ወጪ ንግድ ለአምስት ወራት ያህል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በዚህም ዓመታዊ ገቢውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር በታች አድርጎታል።
በተያያዘ ዜና በዘንድሮው ዓመት ሱዳን ያልከፈለችው ውዝፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ያለ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳን ኤሌክትሪክ ኃይል ይከፈለኝ የሚል ደብዳቤ ጽፏል።
ተቋሙም በጻፈው ምላሽ አገሪቱ ያለችበትን ፈታኝ ሁኔታ ጠቅሶ ታገሱኝ፣ አገልግሎቱም አይቋረጥ የሚል ጥያቄ መቅረቡንም አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም ለሁለት ወይም ሶስት ወራት ሳይከፈል የሚዘልበት ጊዜ ቢኖርም በአሁኑ ወቅት ግን ከተለመደው ውጭ ስድስት ወራት በላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሞገስ መጠኑን ግን መጥቀስ አልፈለጉም።
የኬንያ ኃይል ሽያጭ ለምን ዘገየ?
የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭን ከጂቡቲ በመቀጠል ለሱዳን ከዓመታት በፊት ማቅረብ የጀመረችው ኢትዮጵያ ለሌላኛዋ ጎረቤት አገር ኬንያም ኃይል ለማቅረብ የወጠነችው ከአመታት በፊት ነበር።
ኢትዮጵያና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመገበያየት የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት ከአስር ዓመት በፊት ነበር።
በወቅቱም የነበሩ የአገሪቱ ሚዲያዎችን ስናገላብጥ እንዳገኘነው በወቅቱ የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑና በኬንያው የኢነርጂ ሚኒስትር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ከአራት አመት በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እንዲጀመር ነበር።
ለምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከፍተኛ ስፍራ ያለውና 1.3 ቢሊዮን ዶላር የፈጀው የዚህ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን ኢትዮጵያ በባለፈው ዓመት ገንብታ ጨርሳለች።
አገራቱን የሚያገናኘው የኤሌክትሪክ መስመር 500 ኪሎ ቮልትና ከኢትዮጵያ በኩል 412 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው እንደሆነ አቶ ሞገስ ይናገራሉ።
ወጪውም ከዓለም ባንክ ከተገኘው ብድር 684 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኢትዮጵያ 441 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለኬንያ 27.4 ቢሊዮን ዶላር የሚሸፈን ነው።
የአፍሪካ ልማት ባንክም ይህንኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ ጋር የሚያገናኘውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ድጋፍ ለኢትዮጵያ 232 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለኬንያ 116 ሚሊዮን ዶላር አጽድቋል።
ለኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታና ለሌሎች ስራዎች ከለጋሽ ተቋማት በብድር ከተገኘው በተጨማሪ አገራቱም ይህንን ትልቅ ፕሮጀክት ለመስራት የራሳቸውን ወጪ አድርገዋል።
በባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በኩል የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ግንባታና የፍተሻ እንዲሁም የሙከራ ስራዎች ቢጠናቀቅም ከኬንያ በኩል ቀሪ የዝርጋታና የፓወር ተከላ ስራዎች እንዳሉ እየተነገረ መጀመር ከነበረበት ወቅት እየተጓተተ ረዘም ያሉ ወራት ተቆጥረዋል።
በያዝነው አመት መስከረም ላይ በኬንያ ኢነርጂ ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረ ሲሆን በቀሪ ጉዳዮች ላይ ስምምነቱን ለማጠናቀቅና ቀሪው የፕሮጀክቱ አካልም እንዲጠናቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ሞገስ ያወሳሉ ።
ከወራት በኋላ እንዲሁ ጥር ወር መጨረሻ ላይ የዘገየውን የ1.3 ቢሊዮን ዶላር 400 ሜጋ ዋት የሃይል ሽያጭ ለማፋጠን ኢትዮጵያና ኬንያ አዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር እዮብ ተካልኝ የተመራ የልዑካን ቡድን ናይሮቢ ጥር መጨረሻ ላይ መጥቶ ከኬንያ ኤነርጂ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ ጋር ተገናኝተው ነበር።
አገራቱ ቀደም ሲል በተፈረሙ የኃይል ስምምነቶች፣ የማጠናቀቂያ ስራዎች፣ የአሰራር መመሪያዎችንም በተመለከተ ተወያይተው መከለሳቸውም ተዘግቧል።
የኬንያ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ለኬንያ ከኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የምትገዛው ኃይል ርካሽ መሆኑን ነው።
ከኬንያ በኩል ከመስመር ዝርጋታ ግንባታ መጓተት በተጨማሪ ስምምነት የተደረሰበት የ400 ሜጋ ዋት ኃይልን በተመለከተ እንዲሁም ከተወሰነው ታሪፍ ጋር ተያይዞ ጥያቄ መነሳቱንም ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ሆኖም አገራቱ ያላቸውን ልዩነት በመፍታት የያዝነው አመት ከመጠናቀቁ በፊት ኃይል የማስተላለፍ ስራው ይጀመራል የሚል እቅድ ተይዞም እየተጠበቀ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት መካከል ድንበር ዘለል የሃይል ንግድ እንዲሁም ትስስርን ለማስተባበር በአውሮፓውያኑ 2005 የተቋቋመው ቀጠናዊ ተቋም የሆነው ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል አካል ነው።
በአጠቃላይ የኃይል ልማት እና ተግባር የማስተባበር ስልጣን የተሰጠው የተቋሙ ዋና ፅህፈት በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን አስራ አንድ አባል አገራት አሉት። አገራቱም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ሊብያ። ኮንጎ (ዲአርሲ)፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ናቸው።
ፕሮጀክቱ እነዚህንም ሃገራት በኃይል የማስተሳሰርና የማዋሃድ አቅም እንዳለው ይነገራል።
በሁለቱ አገራት የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርም እስከ 2000 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው ነው።
እንደ አቶ ሞገስ ይህ የኤሌክትሪክ መስመር ኢትዮጵያና ኬንያን ከማገናኘት በተጨማሪ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የምስራቅ አፍሪካና ሌሎች የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራትንም ተደራሽ ያደርጋል በሚል እሳቤ የማስተላለፍ አቅሙ ከፍ ተብሎ የተሰራ ነው።
ለሌሎቹም አገራት ኤክስፖርት የሚደረግበት የኤሌክትሪክ መስመር በአብዛኛው ጤናማ የሆነ መስመር ያለው ሲሆን እንደ የአገር ውስጥ ማስተላለፊያ መስመሮች አሮጌ አለመሆኑንና ኤሌክትሪክ በመሸከም በኩል ችግር እንደማይጠቀስም አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
ለደቡብ ሱዳን ኃይል ለመሸጥ የተደረሰው ስምምነት
ከሰሞኑ ደግሞ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ የተመራው የልዑካን ቡድን፣ ኢትዮጵያ መጥቶ የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከልን እና የኮተቤ የኃይል ማከፋፋያ ጣቢያን ከጎበኙ በኋላም ከሶስት ዓመት በኋላ የኃይል ሽያጭ እንዲጀመር የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምምነቱ ከሶስት ዓመት በኋላ ሽያጭ እንደሚጀመር የጊዜ ገደብ የተቀመመጠለት ሲሆን ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከመጀመሩ በፊት መሰራት ያለባቸው ተግባራት ስላሉ እንደሆነ አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
በዚህም መስረት በመጀመሪያው ዓመት ሁለቱም አገራት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በተመለከተና ከአቅርቦቱ ጋር የተያያዘ የአዋጭነት ጥናቶችን የሚያካሂድ ቴክኒካል ቡድን ያቋቁማሉ።
ይሄንን የአዋጭነት ጥናትም ተከትሎም ባሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የሚከናወነው።
ግንባታው ሁለት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችልም ታሳቢ ተደርጓል።
የሁለቱ አገራት የመግባቢያ ስምምነት በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው 357 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ከጋምቤላ 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ ወደ ደቡብ ሱዳኗ ማላካል ግዛት የሚዘልቀው ነው።
ሁለተኛውና ረዘም ባለ ጊዜ ይከናወናል ተብሎ የታቀደው ደግሞ ከ700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ባለ 400 ወይም 500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከቴፒ ወደ ቦር ጁባ የሚዘረጋው ነው።
ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በመጀመሪያው ዓመት ላይ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሽያጭ እንዲኖር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሆኖም በ100 ሜጋ ዋት ብቻ እንደማይወሰን የሚናገሩት አቶ ሞገስ የደቡብ ሱዳንን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎችን እንዲሁም የአገሪቱን መሰረተ ልማት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በየጊዜው ሊያድግ የሚችል የኃይል ፍላጎት አቅርቦት ይደረጋል።
በዚህም መሰረት ከፍተኛውና ከ400 ሜጋ ዋት የማይበልጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ነው የመግባቢያ ስምምነቱ የተደረሰው።
የኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ ንግድ የሚታዩ ችግሮች
ረዘም ባለ ጊዜ ዕቅድ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ብሩንዲ የመሸጥ እቅድ አላት።
ነገር ግን ድርድሮች ተካሂደው፣ የመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ እንዲሁም ግንባታው እስኪከናወን ዓመታት እንደሚጠይቅ አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
"በፍላጎት ደረጃ እውነት ነው በተለይ ጎረቤቶቻችን ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል።" የሚሉት አቶ ሞገስ ለምሳሌ ሶማሌላንድ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።
በተጨማሪም የኃይል አቅርቦት በየዓመቱ የሚሸጥላቸው እንደ ሱዳን ያሉ አገራትም ጭማሬ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ሱዳን አሁን ከሚደረገው የኃይል አቅርቦት (ከፍተኛው ወደ ሁለት መቶ ሜጋ ዋት) በተጨማሪ በ1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ጭማሬ ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች።
"ይህንን 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ወደ ሱዳን ለመላክ የሚያስችል አሁን ባለው ሁኔታ እንደ አገር አቅም የለንም ። ያንን ማስተናገድ አንችልም። አሁን ባለው መሰረተ ልማት ደግሞ ሊሆን የሚችል አይደለም። ስለዚህ እሱ ለወደፊት ምላሽ ማግኘት የሚችል ጉዳይ ነው" ይላሉ።
አገሪቷ አሁን ባላት ሃይል የማመንጨት አቅም ለሱዳን የሚላከው መጠን እስከ 300 ሜጋ ዋት ድረስ ቢሆን ብዙ ችግር ባይኖረውም የሱዳን ፍላጎት ግን በጣም ከፍተኛና ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ማሟላት የማትችለው ነው ይላሉ።
ከኤሌክትሪክ ወጪ ንግድ ጋር ተያይዞ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ኤክስፖርት ወደሚደረግባቸው ሃገራት የሚጠይቁትን ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉ እንደሆነ አቶ ሞገስ ይጠቅሳሉ።
በዋነኝነት ተቋሙ ትኩረት የሚሰጠው የአገር ውስጥ ፍላጎት ስለሆነ፣ ስምምነቶቹ ላይ የአገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት ካልተቻለ ሙሉ በሙሉ የማቆም እርምጃ እንደሚወሰድ የሚጠቅስ አለ።
ለምሳሌም የሚጠቅሱት በ2011 የተከሰተውን የኃይል እጥረት ነው፤ በዚህም ወቅት ኢትዮጵያ ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከማቋረጥ በተጨማሪ ለጂቡቲ የቀረበው ኃይልም በግማሽ ገደማ ቀንሶ ነበር።
ይህ አሰራር ለኃይል ጠያቂዎቹ አገራት ብዙም እንደማይስማማቸው አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
የአገር ውስጥ የኃይል መቆራረጥ ባለበት ወጪ ንግድ እንዴት ይጣጣማል?
የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣የተዛባ የንግድ ስርዓት በተለይም የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ለአገሪቷ ለአመታት ከፍተኛ ማነቆ የሆነባት ጉዳይ ነው።
በገቢና በወጪ ንግድ ሚዛን መጓደልም ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት አገሪቱ ከወጪ ንግድ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ በገቢ ንግድ ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንዳደረገች መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንንም ከፍተኛ ልዩነት ለማመጣጠን አገሪቱ የወጪ ንግዷን ማሻሻል የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እንደ መፍትሄ የሚሰነዝሩት ነው።
የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አገሪቱ ገንዘብ ከምታገኝበት ወጪ ንግድ አንዱ ቢሆንም አገሪቱ ካላት ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ሽፋን እንዲሁም ህዝቧ በኃይል መቆራረጥ በሚሰቃይበት ወቅት ኢትዮጵያ ለውጭ አገራት ኃይል መሸጧ ጥያቄን ማጫሩ አልቀረም።
ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ከግብፅ በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ታሪካዊ ተጠቃሚነት በምታነሳበት ወቅት የምትሰጠው ምላሽ ይህ ታሪካዊ ስህተት መስተካከል እንዳለበት በመጥቀስ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ያለ መብራት እና በድህነት በሚማቅቁበት ሁኔታ ግድቡ ያለውን ጠቀሜታ ስታሳውቅ ቆይታለች።
አገሪቷ ያላት የኤሌክትሪክ ሽፋን ዝቅተኛ እንዲሁም በርካታ መቆራረጥ የሚታይበት ነው።
የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን በምናይበት ወቅት በ2012 ዓ.ም 5.8 ሚሊዮን ደንበኞች እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 33 በመቶ ከብሔራዊ ግሪድ የሚያገኙ እንዲሁም ከግሪድ ውጭ ተጠቃሚ የሆኑ 11 በመቶ መሆኑን ከአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የአገር ውስጥ ሽፋን እንዲህ ዝቅተኛ በሆነበት መጠንና በአገሪቱ የኃይል አቅርቦት እየተቆራረጠ ባለበት ሁኔታ ለጎረቤት ሃገራት ወጪ ንግድ ማድረግስ እንዴት ይጣጣማል?
ቅድሚያ የሚሰጠው የአገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት ላይ እንደሆነ አፅንኦት በመስጠት የሚናገሩት አቶ ሞገስ በአገር ውስጥ እያንዳንዱ ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ፍላጎታቸው ሳይሟላ የወጪ ንግድ የሚደረግበት አሰራር እንደሌለ ያስረዳሉ።
ለዚህም የኃይል ወጪ ንግድ አሰራር የተዘረጋ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጠው ከምታመርተው እስከ 10 በመቶውን መሆኑም አቶ ሞገስ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ 6 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ህዳሴ ግድብን እያጠናቀቀች ከመሆኑ አንፃር የሚመረተውን ኃይል ከፍ የሚያደርገው ሲሆን የአገሪቱንም 10 በመቶ ወጪ ንግድ ድርሻ ከፍ እንደሚያደርግም ያስረዳሉ።
"ከፍተኛ ኃይል አመንጭተናል ብለን ያመነጨነውን ኃይል ኤክስፖርት አናደርግም። አገራችን የኃይል ጥያቄ በየቦታው ነው ያለው። ኤሌክትሪክ የሚፈልገው ህዝብ ብዙ ነው። የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ማስፋፋት ይጠይቃል" እነዚህ ባሉበት ሁኔታ የመነጨውን ሁሉ ኤክስፖርት አይደረግም" ይላሉ።
አቶ ሞገስ እንደሚያስረዱት በተጨማሪም ሽያጩ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ የኃይል አጠቃቀምን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።
ይህ ማለት አገሪቱ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት (ፒክ ሃወር) ውጭ ያለውን ነው ለሽያጭ የምታቀርበው።
በኢትዮጵያ ያለው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ወቅትን አቶ ሞገስ ሲያብራሩ ጠዋት ሰራተኛው ወደ ስራ ከመሄዱ በፊት ምግብ ለማብሰል፣ ሌሎችንም ተግባራት ለማከናወን ከፍ ያለ ነው።
ሆኖም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት በኋላ የተጠቃሚው ቁጥር እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን ወደ ስድስት ሰዓት አካባቢም እንደገና የተወሰነ ጭማሬ እንደሚያሳይም አቶ ሞገስ ይጠቅሳሉ።
በመቀጠልም ምሽት ላይ ከ12 ሰዓት በኋላ አጠቃቀሙ ይጨምርና ወደ 4 ሰዓት ማታ የመቀነስ አዝማሚያ ያሳያል።
እንደ አቶ ሞገስ ከፍተኛ ፍላጎት ካላበት ሰዓት (ፒክ ሃወርን) ውጭ ያለው አጠቃቀም ዝቅተኛ ሲሆን በተለይም የምሽቱ ሰዓት ላይ ደግሞ የወጪ ንግድ ወደሚደረግባቸው ሱዳንና ጂቡቲ ከፍተኛ ሙቀት ያለበትና ኤይር ኮንዲሽነር ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስገዳጅ የሚሆንበት ነው።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ዝቅ በሚልበት የምሽት ሰዓት የአገራቱ ፍላጎት ከፍ ስለሚል ኢትዮጵያ ይህንን አሰራር በመጠቀም የኃይል ወጪ ንግድ እንደምታደርግ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢነርጂ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ
ኢትዮጵያ ፍላጎት ላሳዩና ለሌሎች ሃገራት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ዘርፎች ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነች እንምትገኝ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል።
ለዚህም የአስር ዓመቱ ፍኖተ ካርታ ተጠቃሽ ነው። በፕላንና ልማት ኮሚሽን የተዘጋጀው የ2013- 2022 የአስር ዓመት የኢነርጂ ልማት ዕቅድ በአገር ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶችን የሚያሟላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረብን በዋነኝነት አቅዷል።
በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በ2012 ዓ.ም 4478 ሜጋ ዋት ከነበረው በ2022 ወደ 19 ሺህ 900 ሜጋ ዋት ማሳደግ እንዲሁም ለጎረቤት አገራት የምትሸጠውን መጠንም ከ2ሺህ 802 ጊዋስ (GWH) ወደ 7 ሺህ 184 ጊዋስ (GWH) ለማድረስ ታቅዷል።
አገሪቷ ከውሃ፣ ንፋስ፣ ጂኦተርማል፣ ጸሃይ፣ ባዮማስ ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት የሚጠቀስ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በቅርቡ ማመንጨት የጀመረውን የህዳሴ ግድብ አንደኛ ዩኒት 375 ሜጋ ዋትን ጨምሮ 4890 ሜጋ ዋት ኃይል ታመርታለች።
በ5ሺህ 150 ሜጋ ዋት ማመንጨት አቅሙ በአፍሪካ ትልቁ እንዲሁም በዓለም ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠውን የህዳሴ ግድብ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት እየተቃረበች ሲሆን ይህም የአገሪቱን የኃይል አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግም የሚጠበቅ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢነርጂ ማዕከል ለመሆን በያዘችው እቅድ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 71 የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የ40 ቢሊዮን ዶላር ፍኖተ ካርታ ይፋ ማድረጓን ዘ አፍሪካ ሪፖርት ባለፈው ዓመት ጳጉሜ መጨረሻ ላይ ባወጣው ሪፖርት ይዟል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ 16ቱ የውሃ ኃይል፣ 24 በነፋስ፣ 17 በእንፋሎት እና 14 የጸሃይ ብርሃንን በመጠቀም ሲሆን ይህም ይላል የዘ አፍሪካ ሪፖርት ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ረገድ በዓለም ላይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥን የሚያሳይ እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ቀዳሚ እንድትሆን ያስችላታል ይላል።
በዚሁ ዘገባ ላይ በአውሮፓውያኑ 2037፣ 35 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጫት አቅም ለመገንባት እቅድም እንደያዘች አስነብቧል።
አገሪቷ ከአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ በተጨማሪ በዘንድሮው ዓመት ይጠናቀቃል የተባለ በኤሌክትሪክ ዘርፍ የ25 ዓመት መሪ እቅድ እያዘጋጀች መሆኑንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ለዚህም አገሪቱ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገችው ላለው ጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል ቀዳሚ ስራ በመሆኑ ዕቅዱን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያሰረዳል።
ዕቅዱ ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ አምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ደብሊው ኤስ ፒ ከተሰኘ የእንግሊዝ አማካሪ ኩባንያ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።