በራስ ተፈሪያንነቱ የሚኮራው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ኮማንዶ ኪዳኔ

ካፒቴን ኪዳኔ ኩስላንድ በእንግሊዝ ውስጥ የመጀመሪያው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ የሆነ የጦር ኮማንዶ ነው።

በሠራዊቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮችን ለመርዳት የመከላከያ 'ራስ ተፈሪ ኔትወርክ' የተባለ ማኅበርም አቋቁሟል።

"የሠራዊቱ አባል መሆን ያልፈለግኩበትን ጊዜ አላስታውስም። የሁልጊዜም ህልሜ ነበር" በማለት በጓዶቹ ዘንድ ዳኒ በመባል የሚታወቀው የ30 ዓመቱ ካፒቴን ኪዳኔ ኩንስላንድ ይናገራል።

"ህፃን እያለሁ የነበሩኝ መጫወቻዎች ሁሉ የኮማንዶዎች አሻንጉሊቶች ነበሩ። ማስታወስ እስከምችልበት ድረስ በሙሉ የጦር መኮንን መሆን ውስጤ ያለ ነገር ነበረ" ይላል።

የልጅነት ህልሙን እውን ያደረገው ዳኒ አድጎም ኮማንዶ ለመሆን በቃ።

በአውሮፓውያኑ 2008 መሠረታዊ ሥልጠናውን በማጠናቀቅ የጦር ሠራዊቱን ተቀላቀለ፣ ለእሱም መለያ የሆነውን አረንጓዴውን የሠራዊቱን ቆብ አጠለቀ።

አረንጓዴውን ቆብ ሁሉም አያጠልቀውም ይልቁንም ብሔራዊ የባሕር ኃይል፣ የአየር ኃይል ወይንም ክፉኛ ፈታኝ የሚባለውን የኮማንዶ ሥልጠና ያጠናቀቁት ብቻ ናቸው።

ዳኒ የኮማንዶ ሥልጠናውን ሲወስድ ገና 18 ዓመቱ ነበር፣ ይህም ትልቅ ስኬት ነው ተብሏል። ነገር ግን እናቱ ማርያም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ቦታ ላያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም ላይቀበሉት ይችላሉ በሚል ወደ ሠራዊቱ መግባቱ አላስደሰታትም ነበር።

"ቤተሰቦቼ ደስተኛ አልነበሩም። መገለል እንደሚደርስብኝና ጥላቻም ያጋጥመኛል በሚል ሰግተው ነበር። ፈታኝ ጊዜ ሊኖረኝ እንደሚችልና ከጦሩ ጋር እንደማልጣጣም እንዲሁም ፍጹም የኔ ቦታ እንዳልሆነ ነበር ያሰቡት" ብሏል ዳኒ።

"እኔ ራስታ ነኝ፣ እኔ እንግሊዛዊ ነኝ፣ ከለንደን ነኝ። ነገር ግን እነዚህ ማንነቶች ለብዙዎች አይጣጣሙም። ሰዎች ራስታ ሆነህ የብሪታንያን ጦር መቀላቀል የሚጠብቁት ጉዳይ አይደለም" በማለት ዳኒ ያስረዳል።

ዳኒ በልጅነቱ በትምህርት ቤት ቆይታው ጥሩ እንዳልነበረ ይናገራል። የልጅነት ጊዜውንም ያሳለፈው ከትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት በመቀየር ሲሆን፣ በርካታ ጊዜም ከርዕሰ መምህሩ ቢሮ ውጪ ይቀመጥ እንደበር ያስታውሳል።

"በመምህራኖቼ ያልተለዩ የመማር ችግሮች ነበሩብኝ፤ ስለዚህ በጣም ተስፋ ቆርጬ ነበር" ብሏል።

"መግለጽ ከተፈቀደልኝ በላይ አስተዋይ መሆኔን አውቅ ነበር፤ ነገር ግን ድጋፍ አልተሰጠኝም። ስለዚህ 11 ዓመት ገደማ እስኪሆነኝ ድረስ ማንበብ አልቻልኩም። ይህም ለእኔ ትልቅ ፈተና ነበር ብዬ አስባለሁ።"

ነገር ግን እሱ ጎበዝ የሆነባቸው እና ማንም ያላወቃቸው ሌሎች ጉዳዮች ነበሩ "ሠራዊቱን ስቀላቀል በድንገት ሁሉ ነገር ቦታውን አገኘ" ይላል።

ዳኒ የሁለት ዘሮች፣ ማንነቶች ውጤት ነው። ጥቁርና ነጭ። ባደገባቸው የእንግሊዝ ከተሞች ቶተንሃም እና ለንደን ዘረኝነት "የዕለት ተዕለት የህይወቴ አካል" ነበር ብሏል። ነገር ግን ሠራዊቱን ሲቀላቀል ዘረኝነቱ አልተንጸባረቀም።

"መንገድ ላይ እየተራመድኩ አንድ ሰው በጥቁርነቴ ተፍቶብኝ ወደ አገሬ እንድመለስ ቢሰድበኝ ይህ ሰው አዋርዶኛል ብዬ የምለው ነገር የለም። በሠራዊቱ ውስጥ ግን በማንነቴ ምክንያት የማይሆን መስመር ካለፉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይባረራሉ። ጦሩ ለእንደዚህ አይነት ሁኔታ ቦታ የለውም። እንዲህ አይነት ጉዳይ ካጋጠመኝ ወደ ማን ማመልከት እንዳለብኝ አውቃለሁ" በማለት ያስረዳል።

ዳኒ ይህንን ይበል እንጂ ከነጭ ውጪ ዝርያ ላላቸው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወታደራዊ ምልምሎች እውነታው በጣም የራቀ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2019 የጦር ሠራዊትን አገልግሎት በበላይነት የሚቆጣጠረው ገለልተኛ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በጦሩ ውስጥ "ዘረኝነት በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋ ነው" ብሏል።

በወቅቱም ኒኮላ ዊሊያምስ ዘረኝነትን ከስር መሰረቱ ለማጥፋት የመከላከያ ሚኒስቴር የበለጠ እንዲሰራ አሳስበዋል።

እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2020፣ የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊ ጄኔራል ሰር ኒክ ካርተር በሠራዊቱ ውስጥ የሚደርሰውን የዘር መድልዎ ለመቅረፍ ብዙ መደረግ አለበት ብለዋል።

ዳኒ በአውሮፓውያኑ 2010 አፍጋኒስታንን ጎብኝቷል።

በወቅቱ አስፈላጊውን ብቃት ባያሟላም በሳንድኸረስት የመኮንኖች ሥልጠናን ወስዷል።

እዚያም ባሳየው ብቃት በኮርሱ ላይ ምርጥ መኮንን በሚል በአውሮፓውያኑ 2016 የክብር ሰይፍ ተሸልሟል።

በማዕረግም ከፍ በማለት በ29 ኮማንዶ ሬጅመንት ውስጥ ከ400 በላይ ኮማንዶዎችን ለመምራት በቃ።

በአውሮፓውያኑ 2021 የመከላከያ የራስ ተፈሪያን ኔትወርክን በማቋቋም እና በመገንባት ሥራው የእንግሊዝ መንግሥት ሽልማት ሰጥቶታል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የተፈጠረው ይህ ኔትወርክ በሠራዊቱ ውስጥ ላሉ የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች ድጋፍ ይሰጣል።

ዳኒ በእምነትና እና በብሔራዊ አገልግሎት መካከል ተቃርኖ መኖር የለበትም የሚል እምነት አለው።

የራስተፈሪያን እምነት ምንጩ የኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ ወይም በቀድሞ ስማቸው ራስ ተፈሪ መኮንን ነው።

አፄ ኃይለሥላሴን እንደ አምላክ ወይንም እንደ ነብይ የሚያዩት ራስ ተፈሪያን እምነት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1930ዎቹ በጃማይካ ነው።

ለጥቁሮች ህይወት መሻሻል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከነበረውና ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው በሚለው አስተምህሮው ከሚታወቀው ጃማይካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማርከስ ጋርቬይን ጋር ራስ ተፈሪያኒዝም ጥብቅ ቁርኝት አለው።

ራስ ተፈሪያኒዝም "ጥቁሮች የበታች ናቸው የሚለውን በተለምዶ የሚነገረውን አባባል በከፍተኛ ተቃርኖም መጋፈጥ ችሏል" ሲል ዳኒ ገልጿል።

ነገር ግን፣ አሁንም ቢሆንም ስለ እምነቱ በሌሎች ዘንድ ያለው አረዳድ የተሳሳተ እንደሆነም ዳኒ ይናገራል።

"ማሪዋና ያጨሳሉ፣ ረጅም ፀጉር ያላቸው እና ሁሉም ጃማይካዊ ናቸው" የሚልም ፈጽሞ የተሳሳተ እሳቤ አለ፤ ይህ ትክክል አይደለም።

"ለዚያም ነው ይህ ኔትወርክ አስፈላጊ የሆነው። ምክንያቱም ሁሉም ሰው እምነቱን ያለ አድልዎ የመግለጽ መብት አለው" ይላል።

ዳኒ ወደ ጦሩ ሲቀላቀል ያለ ክፋት ፀጉር ማሳደግ እንደማይቻል ሲነገረው ረጅም ፀጉሩን (ድሬድ ሎኩን) ቆርጦታል።

አንዳንድ ራስ ተፈሪያን ፀጉርን እንደ መንፈሳዊ የጥንካሬ ምልክት አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆን፣ ፀጉራቸውንም በጭራሽ አይቆረጡም።

በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የራስ ተፈሪያን ኔትወርክ ከተቋቋመ ጀምሮ ራስ ተፈሪያን ወታደሮች እምነታቸው በሚፈቅደው መሰረት ድሬድ ፀጉራቸውን እንዲያሳድጉ፣ ፂማቸውን እንዳይቆረጡና አንዳንዶችም ጥምጣም እንዲያጠልቁ በሚያስችል መልኩ የጦሩ አለባበስ መመሪያው ተሻሽሏል።

"አስደናቂ ነበር" ይላል ዳኒ።

የራስ ተፈሪያን እምነት አባላትን ጨምሮ የሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች በሠራዊቱ የመመልመል ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከ150 በመቶ በላይ ጨምሯል። አሃዙንም በአውሮፓውያኑ 2017 ከ500፣ በ2021 ወደ 1,280 ጨምሯል።

ሆኖም አሁንም ቢሆን ገና ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ናቸው። አሃዞች እንደሚያሳዩት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ካሉት መደበኛ የጦር መኮንኖች ውስጥ 2.5 በመቶ የሚሆኑት የሌላ ዘርና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፣ ከመኮንኖች በታች ለሆኑት ደግሞ 8.8 በመቶ የሚሆኑት ከነጭ ውጪ ያሉ ሌሎች ሕዝቦች ናቸው።

ዳኒ በአሁኑ ወቅት ወደ ሳንድኸርስት በአስተማሪነት ተመልሷል፣ ነገርግን ከተለያዩ ማንነቶች፣ አስተዳደግ እና እምነት የመጡ ሰዎችን ወደ ጦሩ ለመሳብ በርካታ ሥራ መሰራት እንዳለበት ያምናል።

"ጦሩ ትልቅ ፈተና ገጥሞታል፣ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የሕብረተሰባችን ተወካይ ስላልሆነ እና ሠራዊቱ ሴቶችን፣ ከተለያየ ዘርና ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ምርጦችን እየተጠቀምንባቸው አይደለም። ከተለያየ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ሰዎች ወደእኛ የማይስባቸው አንዳች ጉዳይ አለ" ይላል ዳኒ።

በአመራር ቦታዎች ላይ የበለጠ ብዝሃነት እንደሚያስፈልግ ያምናል፣ በዚህም በኃላፊነት ላይ ያሉት ሰዎች የበለጠ "የኑሮ ልምድ" ያካበቱ ይሆናሉ።

የዳኒ እናት ማርያም፣ ልጇ ማየት የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት እየረዳው እንደሆነ በከፍተኛ ኩራት ተሞልታ ትናገራለች።

"አዎንታዊ በሆነ መልኩ ቤተሰቤ ስህተት መሆኑን ማሳየት አስደናቂ ነገር ነው" ይላል ዳኒ።

"ወደ ማኅበረሰቤ ተመልሼ እነሱን አበረታትቼ ሠራዊቱ ስኬት የምናገኝበት ስፍራ እንደሆነ ማሳየት፣ እንዲሁም ሁላችንም ወደ አንድ ዓላማ የምንመጣበት ነው ማለት መቻል በእውነት በጣም ከፍተኛ ነገር ነው" ይላል።