ባይደን የስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄን አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ ትደግፋለች አሉ

ስዊድን እና ፊንላንድ ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) አባልነት ያቀረቡት ማመልከቻ በአሜሪካ "ሙሉ ድጋፍ" ይሰጠዋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ገለጹ።

የአውሮፓን ጂኦፖለቲካ በሚቀይር መልኩ ሁለቱ ሃገራት በዚህ ሳምንት ነበር የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡት።

ሁለቱ ሃገራት የጥምረቱ አባል ለመሆን የስላሳውንም የኔቶ አባል አገራት ይሁንታን ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

የሁለቱ የኖርዲክ ሃገራት የአባልነት ጥያቄ ከቱርክ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ከስውድን ጠቅላይ ሚንስትር ማግደሊና አንደርሰን እና ከፊንላንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ሳዉሊ ኒኒስቶ ጋር በኋይት ሃውስ መግለጫ የሰጡት ባይደን የሃገራቱን ጥያቄ "ለአውሮፓ ደህንነት አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"አዳዲስ ሃገራት ኔቶን መቀላቀላቸው ለየትኛውም ሃገር ስጋት አይደለም" ብለዋል። ሁለት ተጨማሪ ሃገራትን "በሰሜን አቅጣጫ" ማግኘት "የአጋሮቻችንን ደህንነት ለማጠናከር እና በአካባቢው ያለንን የደኝንነት ትብብር ለማሳደግ ይጠቅማል" ብለዋል።

የኔቶን መስፋፋት ስጋት መሆኑን በተደጋጋሚ የምትገልጸው ሩሲያ በበኩሏ መስፋፋቱ ከቀጠለ "አጸፋ" እንደሚኖር ዝታለች።

ቱርክ በበኩሏ ስዊድን እና ፊንላንድ የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ታጣቂዎችን በመርዳት ትከሳለች። ቱርክ ፓርቲውን በአሸባሪነት ፈርጃለች።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶለተንበርግ እና የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚስትር ቤን ዋላስ ጉዳዩ እልባት እንደሚያገኝ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የባይደን አስተያየት የተሰማው የሃገሪቱ ሴኔት ለዩክሬን አዲስ የ40 ቢሊዮን ዶላር የመከላከያ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት የቀረበውን ሃሳብ መደገፉን ተከትሎ ነው። ይህም ለዩክሬን የተሰጠ ትልቁ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ሆኗል።

ከቀናት በፊት በህዝብ እንደራሴዎች ድጋፍ አግኝቶ የነበረው ድጋፍ በሳምንቱ መጀመሪያ እንደሚጸድቅ ተጠብቆ ነበር። የኬንተኪው ሪፐብሊካን ራንድ ፖል ወጪውን በመቆጣጠር ጉዳይ ላይ ባነሱት ጥያቄ መጓተቱ ታውቋል።

የሴኔቱ የሪፐብሊካን መሪ ሚች ማክኮኔል ስጋቱን አጣጥለዋል። ለሪፖርተሮችም ኮንግረሱ "ሉዓላዊ ራስን መከላከልን" የመደገፍ "የሞራል ኃላፊነት አለበት" ብለዋል።

"ዩክሬንን አሸናፊ ለማድረግ የሚደረገውን የድጋፍ ዋጋ በተመለከተ ስጋት ያለበት ሁሉ ዩክሬን ብትሸነፍ ያለውን ኪሳራ ማጤን አለበት" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ሚኒስትሩ ልዮድ ኦስቲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ኮንግረሱ ድጋፉን እንዲያጸድቅ እና የአሜሪካ መከላከያ መላክ የሚችለው ለጥቂት ቀናት ብቻ የሚበቃ መሣሪያ ብቻ እንዳለው አስታውቀው ነበር።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ድጋፉን "አሜሪካ ለዩክሬን፣ ለአውሮፓ እና ለዓለም ሠላም መስፈን የምታደርገው ትልቅ እገዛ" ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ለስልጠና፣ መሣሪያዎች እና ድጋፍ የሚደረገውን የስድስት ቢሊዮን ዶላር የደህንነት ድጋፍ ጨምሮ የአሁኑ አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችውን ድጋፍ ከ50 ቢሊዮን ያሳልፈዋል።

እስካሁን ለዩክሬን የተሰጠውን የአሜሪካ የመሣሪያ ድጋፍ ለሟሟላት ደግሞ ተጨማሪ 8.7 ቢሊዮን ዶላር ተመድቧል።