አሜሪካዊው ታጣቂ ጥቁሮችን ብቻ ነጥሎ ጥቃት መፈፀሙ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, ERIE CO DA
በኒው ዮርክ ግዛት በፋሎ ከተማ አንድ ነጭ ታጣቂ ጥቁሮች የሚበረክቱበት መገበያያ ሥፍራ ገብቶ ጥቃቱ መፈፀሙ ተሰምቷል።
10 ሰዎችን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው የ18 ዓመቱ ፔይተን ጌንድሮን 320 ኪሎ ሜትር ተጉዞ መጥቶ ጥቃት መፈፀሙን ፖሊስ ገልጧል።
ጥቃቱ በዘረኝነት መንፈስ የተፈፀመ ሊሆን ይችላል በሚል ምርመራ እየተደረገበት ነው።
የበፋሎ ከተማ ከንቲባ ባይረን ብራውን ተጠርጣሪው "የቻለውን ያክል የጥቁር ነብስ ለማጥፋት ነው የመጣው" ብለዋል።
ተጠርጣሪው ጥበቃ በሚደረግለት አካባቢ ሆኖ እንዴት በቀላሉ ጥቃት ሊፈፅም ቻለ ሲሉ ብዙዎች እየጠየቁ ነው።
ግለሰቡ ባለፈው ሰኔ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ጥቃት እፈፅማለሁ ሲል ዛቻ መሰንዘሩን አንድ ፖሊስ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ከዚህ ዛቻ በኋላ የአእምሮ ጤናው ምርመራ እንዲደረግለት መደረጉ ተሰምቷል።
ግለሰቡ ፋሺስትና በነጭ የላይነት አማኝ መሆኑን የሚጠቁም 180 ገፅ ያለው "ማኒፌስቶ" እንዳለው ተሰምቷል።
"ሰዎች ስለግለሰቡ የሚያውቁትን ማወቅ እፈልጋለሁ" ሲሉ የኒው ዮርክ ገዥ ኬቲ ሆቹል ኤቢሲ ለተሰኘው ጣቢያ ተናግረዋል።
ፖሊስ እንደገለጠው ተጠርጣሪው ጥቃት ከመፈፀሙ አንድ ቀን በፊት በሥፍራው ቅኝት ሲያደርግ ነበር።
የኒው ዮርክ አቃቤ ሕግ ሌቲታ ጄምስ ቢሯቸው በይነ መረብ ላይ ያሉ ፅንፈኛ ፅሑፎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
"ይህ በየቀኑ ጥላቻ ሲመገብ የኖረ ሸይጣን የተጠናወተው ግለሰብ ነው ጥቃት የፈፀመው" ብለዋል አቃቤ ሕጓ አክለው።
ጥቃቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ያስደነገጠ ሆኗል።
በጥይት ከተመቱ 13 ግለሰቦች መካከል አስራ አንዱ ጥቁሮች ናቸው።
ከበፋሎ በፊት ክራይስትቸርች፥ ፒተርስበርግና ኤል ፓሶ በተባሉ ሥፍራዎች እንዲሁ በዘር ጥላቻ የተቀሰቀሱ ጥቃቶች ተፈፅመው ነበር።
ከዚህ ቀደም እንደተስተዋሉት ዘር ተኮር ጥቃቶች የበፋሎው ጥቃት አድራሽ ድርጊቱን በበይነ መረብ ቀጥታ አስተላልፏል።
ግለሰቡ የለጠፈው "ማኒፌስቶ" ማስረጃ በሌላቸው ቁጥሮች እንዲሁም የሤራ ትንታኔዎች የተሞላ ነው።
የነጭ የበላይነት አምላኪው ግለሰብ ማኒፌስቶ በዘረኛና ፀረ-ሴማዊ ቃላት የታጨቀ ነው።
የ18 ዓመቱ ተጠርጣሪ በኮቪድ ወቅት ፅንፈኛ ድረ-ገፆችን በመጎብኘት ፅንፍ የረገጠ አቋም ማራመድ እንደጀመረ ተገልጧል።
የወታደር መለዮ ታጥቆ ቶፕስ ፍሬንድሊ ማርኬት ወደተሰኘው ገበያ የመጣው ተጠርጣሪው፤ ጥቃቱን ቀጥታ ማስተላለፍ የጀመረው ቅዳሜ ከሰዓት 8፡30 ገደማ ነበር።
የገበያው ጥበቃ ተጠርጣሪው ላይ ቢተኩስም የታጠቀውን ጥይት መከላከያ መምታት የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ተጠርጣሪው ጥበቃውን ከገደለ በኋላ ወደ መገበያያ ሥፍራው ገብቶ ያገኘው ሰው ላይ ጥይቱን አርከፍክፏል።
ግለሰቡ ከጥቃቱ በኋላ በቁጥጥር ሥር ቢውልም ጥቃቱን አልፈፀምኩም ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ምንም እንኳ ምርመራው ባይጠናቀቅም ይህን ዘረኛ ጥቃት እቃወማለሁ ብለዋል።












