ሕንድ ውስጥ አካል ጉዳተኛው ታዳጊ ወደ አውሮፕላን እንዳይገባ መከልከሉ ቁጣን አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, MANISHA GUPTA VIA FACEBOOK
ሕንድ ውስጥ አንድ አካል ጉዳተኛ ታዳጊ ወደ አውሮፕላን እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ የአገሪቱ አቪዬሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጉዳዩን እየመረመረው እንደሆነ አስታውቋል።
በአገር ውስጥ ብቻ በረራዎችን የሚያደርገው አየር መንገዱ ታዳጊው ለራሱና ለሌሎች ተሳፋሪዎች ስጋት ስለሚፈጥር ወደ አውሮፕላኑ መግባት እንደማይችል ለቤተሰቦቹ ገልጾ ነበር።
ይህ ክስተት ታዲያ ሕንድ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ መሆን ብቻ ሳይሆን በርካቶችን ያስቆቀጣ ሆኗል።
የህንድ ዜጎችም በአገራቸው ያለውን መሰል የማግለልና መድልኦ ስርአት በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
ኢንዲጎ የተሰኘው አየር መንገድ የቀረበበትን ክስ በማስተባበል እንዲያውም ሁሉንም አካታች የሆነ ስርአት የሚከተል ድርጅት እንደሆነ ገልጿል።
የሕንድ ኤቪዬሽን ሚኒስትሩ ጆይቲራዲትያ ሲንዲያ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ''ጉዳዩን በደንብ እየመረመርነው ነው፤ ተገቢውም እርምጃ ይወሰዳል'' ብለዋል።
''መሰል ተግባራትን የሚታገስ ህግ የለንም። ማንኛውም አይነት የሰው ልጅ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሊያልፍ አይገባም'' ብለዋል በትቀዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት
በተጨማሪም አየር መንገዱ በዕለቱ ምን እንደተከሰተ የሚገልጽ ሪፖርት እንዲያስገባም ጠይቀዋል።
ታዳጊው አወደ አውሮፕላኑ እንዳይገባ የተከለከለው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሲሆን በቦታው የነበረች ማኒሻ ጉፕታ የተባለች ተሳፋሪ ሁኔታውን በማስመልከት በፌስኑክ ገጿ ላይ ጉዳዩን በተመለከተ መጻፏን ተከትሎ ነው ለህዝብ ይፋ የሆነው።
ሚኒሻ ጉፕታ አንዳለችው ታዳጊው በተፈጠረው ነገር ተደናግጦና አዝኖ ነበር ነበር ብላለች። ''የአየር መንገዱን ፍተሻ አልፎ ወደ አውሮፕላን ለመግባት በተቃረበበት ወቅት አትገባም ሲባል በጣም ደንግጦ፣ ተጨንቆና ግራ ተጋብቶ ነበር። አጠገቡ የነበሩት ቤተሰቦቹ በተቻላቸው መጠን ለማረጋጋት ሲሞክሩና ሲያጽናኑት ነበር''
''የአየር መንገዱ ሰራተኞች ስልጣናቸውን ለማሳየት እየሞከሩ ይመስል ነበር። የበረራ አስተናጋጆቹ ሁሉም ታዳጊው መግባት እንደማይችል በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር። ለተጓዦች ስጋት እንደሆነ በመግለጽ ነበር ታዳጊውና ቤተሰቦቹን ሲከለክሏቸው የነበረው''
ሌሎች ተሳፋሪዎችም አካል ጉዳተኛው ታዳጊም ሆነ ቤተሰቦቹ ወደ አውሮፕላኑ ቢገቡ ቅር እንደማይላቸው ገልጸውም ነበር። እንደውም በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርጉለትና ምንም ችግር እንደማይፈጠር ቢገልጹም የአየር መንገዱ ሰራተኞች ግን በአቋማቸው ጸንተዋል።
ማኒሻ ጉፕታ ክስተቱን ተከትሎ በፌስቡክ ገጿ ላይ ያሰፈረችው መልዕክትም በመላው ህንድ ትልቅ መነጋገሪያ መሆን ችሏል። በርካቶችም አየር መንገዱ ላይ ተቃውሟቸውንና ቁጣቸውን እየገለጹ ነው። መንግሥትም ተገቢውን ምርመራ አድርጎ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
ኢንዲጎ አየር መንገድ በበኩሉ የተሳፋሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግና በዚህ አጋጣሚ እንግልት የደረሰበትን ቤተሰብ ለአንድ ቀን በሆቴል እንዲቆዩ ማድረጉን ገልጿል። አክሎም ታዳጊውና ቤተሰቦቹ በቀጣዩ ጠዋት ወደሚፈልጉበት ቦታ እንዲሄዱ ማድረጉንም አስታውቋል።
''በተፈጠረው ነገር በጣም አዝነናል። ኢንዲጎ አየር መንገድ ሁሉንም አካታች ድርጅት እንደሆነ ያምናል። ለሰራተኞቹም ሆነ ለተሳፋሪዎቹ ምቹ አካባቢ ነው'' ብሏል።
ሕንድ ውስጥ 26 ሚሊዮን አካላዊና ጉዳትና ነገሮችን በቀላሉ የመረዳት ችግር (learning disabilities)ያለባቸው ዜጎች የሚገኙ ሲሆን ስለ ችግሮቹ ያለው ግንዛቤና ለነሱ የሚሆን መሰረተ ልማት ግን በጣም ዝቅተኛ ነው።
በሌላ በኩል እነዚህ ሰዎች የተለያዩ አይነት መገለልና መድሎ እንደሚደርስባቸው በጉዳዩ ላይ ማህበረሰብ የማንቃት ስራ የሚያከናውኑ ሰዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።












