ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመስመጥ ላይ ካለ መርከብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የታደገው የጊታር ተጫዋች
ጊዜው እአአ 1991 ነው። ኦሺኖስ ቅንጡ መርከብ ናት። ደቡብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ላይ ስትደርስ አደጋ ገጠማት። ውሃ ይገባት ጀምር። ሙዚቀኛው ሞስ ሂልስ እና ጓደኞቹ ደግሞ የተሳፋሪዎቹን ሁሉ ህይወት የመታደግ ኃላፊነት ጫንቃቸው ላይ ድንገት አረፈ።
ለእራት ማዕድ ሲሰናዳ ነበር ሞስ ሂልስ አውሎ ነፋሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅ የጀመረው።
የመርከቡ አስተናጋጆች ቆፍጣኖች ናቸው። ምንም ሳይነገዳደገዱ ምንም ጠብ ሳይልባቸው ነበር የሚያስተናግዱት። የዚያን ምሽት ፈተና በዛባቸው።
የዚምባብዌ ተወላጅ የሆነው የጊታር ተጫዋቹ ሞስ የባስ ተጫዋች ከሆነችው ባለቤቱ ትሬሲ ጋር በመርከቡ ላይ ተሳፍረው ነበር። አስተናጋጆቹ ሲቸገሩና ትሪያዎችን ሲጥሉ ፈጽሞ ገጥሞት አያውቅም።
የዚያ ቀን ጉዞ ወደ መናገሻቸው ደርባን ነበር። ኃይለኛ ንፋስ እና ከባድ ዝናብ ጉዟቸውን በተደጋጋሚ አዘግይቶት ነበር። ቢጠበቅ ምንም ለውጥ የለም። ቢጠበቅ የአየር ንበረቱ አይሻሻልም።
በመጨረሻም መርከበኛው መልህቁን ለማንሳት ወሰነ። 581 እንግዶች እና መርከበኞች ተሳፍረዋል። ንፋሱም ማዕበሉም እንዳሉ ነው የተሳፈሩት።
ባልና ሚስት ያኔ ዕድሜያቸው በ30ዎቹ ውስጥ ነበር። መርከቧ ከወደብ መራቅ ስትጀምር ሞስ እና ትሬሲ በመዋኛ ገንዳው አጠገብ የሙዚቃ ድግሶችን ያስናዳሉ። ያን ዕለት ማዕበሉ ዕድል ባለመስጠቱ ድግሱ ወደ መርከብ ውስጥ ተዛወረ።
ሞስ ጊታሩን ሲጫወት ከመርከቧ ወዲያ ወዲህ ስትል ሚዛኑን ለመጠበቅ እየሞከረ ነበር።
"አውሎ ነፋሱ እየተባባሰ ሄደ" ይላል ሞስ።
አይደርስ የለም የእራት ሰዓት ደረሰ። በባሏ ድንጉጥ አይደለችም የምትባለው ትሬሲ ለምናልባት በሚል የድንገተኛ አደጋ ቦርሳዎችን ለማዘጋት ተፍ ተፍ ማለት ጀመረች።
"እሷ እንደሄደች በድንገት ቡም ብሎ ሁሉም መብራቶች ጠፉ" ይላል ሞስ።
ሞስም በተፈጥሮው ድንጉጥ አልነበረም። ከመርከቧ መኮንኖች አንዱ መመሪያዎችን ሲሰጥ ግን ብርክ ያዘው።
"በውቅያኖስ መካከል በመርከብ ነን። ድቅድቅ ጨለማ ነው። በአስፈሪ ማዕበል ሲጨመርበት ሆዴ ሲገላበጥ ተሰማኝ" ይላል።
ደብዛዛ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ መብራቶች ሲበሩ ሞስ በመድረክ ላይ ያሉትን የሙዚቃ መሳሪያዎች ለማየት ወጣ። መሣሪያዎቹ ተበታትነው ነበር።
ቀልቡን ሲሰበስብ የሞተሩን ድምጽ እንደበፊቱ እየሰማ አልነበረም። መርከቧ ጉልበት አጥታለች። ፍጥነቷም ቀንሶ ነበር።
153 ሜትር የምትረዝመው ኦሺኖስ በማዕበሉ ወደ ጎን ትንሳፈፍ ያዘች።
ሞስ እንደሚለው መርከቧ እየተመታች ነበር።
ጭንቅ የወጠራቸው እንግዶች ወደ ሳሎን ይጎረፉ ጀመር። ወንበር፣ ጠረጴዛ እና ሌሎችም እቃዎች ወደ አንዱ ጥግ ይወረወራሉ። እንግዶች ከመቀመጫቸው እየተነሱ ወለሉ ላይ ተቀመጡ። መርከቧ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ትወዛወዛለች።
ሰዓቱ ሲነጉድ በሳሎን ያለው ውጥረት ጨመረ። ሞስ አኮስቲክ ጊታሩን አንስቶ ከሌሎቸ ሙዚቀኞች ጋር ሰዎችን ለማረጋጋት መጫወት ጀመረ። ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ግን መርከቧ በማዕበሉ ይበልጥ መወዛወዝ እንጂ መስተካከል የቻለች አልመሰለችም።
"አንድ መጥፎ ነገር እየተፈጠረ ነው። ምን እየተፈጠረ እንዳለ ለማወቅ እሞክራለሁ" አሲል ሞስ ለትሬስ ነገራት።
ሞስ እና ጁሊያን የተባለው ከዮክሻየር የመጣ አስማተኛ ብረት እየያዙ ወደ ታችኛው ክፍል አመሩ። የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ አስደሳች ድምጾች እየሰሙ ነው።
የመርከቧ ሠራተኞች እየተሯሯጡ ነበር። አንዳንዶቹ ቦርሳ ይዘዋል፤ ሌሎቹ ደደግሞ የአደጋ ጊዜ ጃኬቶችን ደርበዋል። በውሃ የተነከሩም ነበሩበት።
"ሁሉም ሰው የተደናገጠ ይመስል ነበር። 'ምን እየተፈጠረ ነው?' ብለን ለመጠየቅ እየሞከርን ነበር። ማንም ግን ስለመኖራችንም የታዘበ ያለ አይመስልም" ይላል ሞስ።
ጁሊያን እና ሞስ ወደ ታችችኛው የሞተሩ ክፍል አቀኑ።
"ከውኃው መስመር በታች ነበርን። ክፍሉ በጨለማ ተውጧል። ማንም ሰው አልነበረም። እንደዚህ አይነት ነገር መቼም የሚከሰት አይደለም" ይላል ሞስ።
የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ውሃ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላኛው እንዳይገባ የሚከላከሉት ወፍራም የብረት በሮች በደንብ ተከርችመዋል።
"ከበሮች ጀርባ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ የሚንቀሳቀስ ይመስላል" ብሏል።
ኦሺኖስ እየሰመጠች ነበር።
ለመንገደኞች ምን እንደተፈጠረ እስካሁን ምንም አልተነገረም። ካፒቴኑ መርከቧን ጥለው መሄድ እንዳለባቸው እንደነገራቸው የመርከቧ ዳይሬክተር ለሞስ ነገሩት።
"አንድ የነፍስ አድን ጀልባ ብዙ መርከበኞች እና ከፍተኛ መኮንኖች ይዞ መሄዱን አወቅን" ብሏል።
ሞስም ሆኑ ሌሎቹ ከመርከቧ እንዴት እንደሚወጡ አያውቁም። መርከቧ በጎኗ ያዘለቻቸውን ጀልባው እንዴት እንደደሚጠቀሙም አያውቁም። ይህንን ለማድረግ ዕውቀቱ ያለው ሰውም አልነበረም ።
የነፍስ አድን ጀልባዎቹን አንድ በአንድ ማውረድ ጀመሩ። ጀልባዎቹን አስተካከለው እንዴት እንደሚያመልጡ አያውቁም ነበር። ሞስ አንድ እግሩን መርከብ ላይ ሌላኛውን ደግሞ ጀልባው ላይ በማድረግ ጀልባዎቹ እንዲስተካከሉ ማድረግ ጀመረ።
ጀልባዋ ከመራቋ በፊት ሞስ ወደ ኦሺኖስ ዘሎ መመለስ ይጠበቅበታል። አንዳንዴ እስከ ሁለት ሜትር ድረስ መዝለል ይኖርበታል።
ወደ 90 የሚጠጉ ሰዎች የሚይዙት ጀልባዎች በገመድ ታግዘው ወደ ባህሩ ይወርዳሉ። አንዳንዶቹ በፍርሀት ይጮሁ ነበር። ሞስ ሞተሮቹን እንዴት ማስነሳት እንዳለበት አያውቅም። ቁልፎቹ የት እንዳሉም አያውቅም ነበር።
"በድቅድቁ ሌሊት እንዲሄዱ እንፈቅድላቸዋለን። ወደሚናወጥ ማዕበል ያቀናሉ። በነፍስ አድን ጀልባው ውስጥ ያሉት ሰዎች የሚያሰቃዩ ጊዜያት እያሳለፉ ነው። የሚረጨው ውሃ፣ ቅዝቃዜው እና ጨለማው ተደማምረው ነበር። ሁሉም ጀልባዎች ጉዞ እስኪጀመሩ ድረስ ይህንኑ መቀጠል ነበረብን" ይላል።
ኦሺኖስ ውሃ በከፍተኛ መጠን እያስገባች ነበር።
ሰዎችን የጫኑት ጀልባዎች ወደ ውሃው ለመውረድ ትልቅ ማዕበል እስኪመጣ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
"የስበት ኃይል ደግሞ በድንገት የነፍስ አድን ጀልባውን ሦስት ወይም አራት ሜትሮች ያወርዳቸዋል። አንዳንዴ ሰዎችን ለመጣል ይሞክራል። በጣም አሰቃቂ ነበር" ይላል ሞስ።
በመጨረሻም በዚህ መልኩ መቀጠል በጣም አደገኛ እንደሆነ ተገነዘበ።
"ሰዎችን እና ለማዳን በምናደርገው ጥረት ልንገድላቸው እንችል ነበር" ብሏል።
ጊዜውም በታቀራኒያናችን ቆሞ ነበር።
ተጨማሪ የነፍስ አድን ጀልባዎችን ማንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግን አሁንም ድጋፍ ስለሚፈልጉ ሞስ እና ጓደኞቹ ወደ መርከቡ ድልድይ አቀኑ። ጉዟቸው ካፒቴኑን እና የተቀሩትን ከፍተኛ መኮንኖች ቀጥሎ ምን እንደሚደረግ ለመጠየቅ ነበር። .
"ወደ ውስጥ ስንመለከትን ማንም አልነበረም። እኛ ብቻ መሆናችንን የተገነዘብነው ያኔ ነው።"
ብርቱካናማ-ቀይ መብራቶች በጨለማ ውስጥ ብልጭ ድርግም ይላሉ። ሞስ ግን አብዛኛው መሳሪያ ምን እንደሆነ አያውቅም ነበር። እንዴት እንደሚሰራም በፍጹም አያውቅም። መረጃ ለመላክ ሬድዮውን ለመጠቀም ተራ በተራ እየሞከሩ ነበር።
"ምላሽ ለማግኘት በማሰብ 'ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ' እያልኩ ነበር" ይላል ሞስ።
አንድ ወፍራም ድምጽ ያለው ሰው "'አቤት! ሜይዴይ ምንድን ነው?'" አለ።
እፎይ ያለው ሞስ ኦሺኖስ የተባለችው መርከብ ላይ መሆናቸውን እና እየሰመጠች እንደሆነ ገለጸ።
"እሺ ለመንሳፈፍ ምን ያህል ጊዜ ቀራችህ?"
"አላውቅም። ወዲያ ወዲህ እየተላተምን ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ገብቷል" ሲል ሞስ ተናገረ። አሁንም በመርከቡ ቢያንስ 200 ሰዎች አሉ።"
"እሺ! የት አካባቢ ናችሁ?"
"በምስራቅ ለንደን ወደብ እና በደርባን መካከል ላይ ነን።"
"አይደለም! አይደለም! ያላችሁበት አካባቢ መለያ ቁጥር ምንድን ነው?"
ሞስ እነዚህ መለያ ቁጥሮች ምን እንደሆኑ ምንም አያወቅም ነበር።
"ኃላፊነትህ ምንድነው ነው?"
"እሺ እኔ ኃላፊነት ለኝም። ጊታር ተጫዋች ነኝ።"
ለአፍታ ዝምታ ሆነ።
"ታዲያ እሱ ክፍል ምን እየሠራህ ነው?"
"እዚህኮ ማንም የለም።"
"ከአንተ ጋር ላይ ያለው ማነው?"
"'እኔ፣ ባለቤቴ እና አንድ አስማተኛ አብረን አለን'…" አልኩት።
ሞስ ኦሺኖስ አቅራቢያ ከነበሩ ሁለት አነስተኛ መርከቦች ጋር እንዲገናኝ ተደረገ። ካፒቴኑን ፈልጎ መረጃውን ላይ እንዲያደርሰው ለሞስ ነገሩት። ካፕቴኑ የት እንዳለ ሞስ አያውቅም ነበር።
"እየሰመጥን ስለነበር ከታች እንደማይወርድ አውቄ ነበር። የውሃውን መጠን ለማየት በየጊዜው እያጣራሁ ነበር። ከኛ በታች ያለው ፎቅ በጎርፍ ተጥለቅልቋል።"
በመጨረሻም ሞስ ካፒቴኑ ከመርከቧ ጀርባ ሆኖ ሲያጨስ አገኘው። በአስቸኳይ የእሱን እርዳታ እንደሚፈልጉ ሞስ አስረዳው።
ዓይኑን አፍጥጦ እያየው "አስፈላጊ አይደለም! አስፈላጊ አይደለም!" ሲል ነገረው።
"በጥልቅ ድንጋጤ ውስጥ የነበረ ይመስለኛል።"
ኦሽኒዮስ አቅራቢያ ያሉት ሁለቱ መርከቦች እያንዳንዳቸው አንድ ጀልባ ብቻ ስለነበራቸው ለመርዳት የሚችሉት ነገር አልነበረም። የምትሰጥመዋን መርከብ አድራሻ ለደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት በማሳወቃቸው በአውሮፕላን የታገዘ የነፍስ አድን ሥራ ማደራጀት ጀመሩ።
አውሎ ነፋሱ መርከቧን ማወዛወዙን ቀጠለ። ሞስ እና ትሬሲ በድቅድቁ ጨለማ አብረው ተቀምጠዋል። እርዳታ በፍጥነት እንዲደርስም እየጸለዩ ነበር።
"መርከቧ የምትሰምጥ ይመስለኛል። . . .ከመርከቧ ጋር ልንሰምጥ ነው" አላት ሞስ ለሚሰቱ።
እሱ እና ትሬሲ አምበር የምትባል የ15 ዓመት ሴት ልጅ አምበር አላቸው። ለመዝናናት በኦሽኒስ ላይ ተሳፍራ የነበረ ቢሆንም ከቀናት በፊት ወርዳለች። አምበር ደቡብ አፍሪካ ወደሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤቷ ተመለሰች።
"ሁለቱንም ወላጆች ልታጣ አይገባም" ማለቱን ሞስ ያስታውሳል። "ምንም ቢፈጠር ቢያንስ አንዳችን መትረፋችንን ማረጋገጥ አለብን።"
የመጀመሪያው የነፍስ አድን ሄሊኮፕተር ደርሶ ከመርከቧ በላይ ከማንዣበቡ በፊት ከሦስት ሰዓታት በላይ አልፈዋል።
ሁለት የባህር ሃይል ጠላቂ ዋናተኞች ወደ ውቅያኖሱ ተወርውረው ገቡ። መርከቧ ከመስጠሟ በፊት ሁሉንም ሰው ለማውጣት እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገለጹ።
ለዚህም ሞስ በሄሊኮፕተር እንዴት ነፍስ ማዳን እንደሚቻል የአምስት ደቂቃ ስልጠና ተሰጠው።
"ቀበቶው በሰዎች ክንድ ስር በጣም ጥብቅ መሆን እንዳለበት አስታውስ። በትክክል መታሰሩን እርግጠኛ ሆን ምክንያቱም አለበለዚያ እነሱ ተገልብጠው ይወድቃሉ። በዚህም በመርከቧ ላይ ትገድላቸዋለህ። በአንድ ጊዜ ሁለቱን እሰር። ካልሆነ ጊዜያችንን ያልቃል። ተግባባን? ሂድ ጀምር" መባሉን ያስታውሳል።
አንዱ የባህር ሃይል ጠላቂ በመርከቧ ጥግ ሰው የማዳን ሥራውን ለማደራጀት ሄደ። ትሬሲ እና ሞስ በፊት ለፊት በኩል ያደራጁ ነበር። መርከቧ በማዕበሉ ስትሰምጥ ሰዎች በድንጋጤ መዝለል ጀመሩ። እናም እነሱን ለማዳን ጠንከር ያለ ሥራ ውስጥ ተገባ።
በአጠቃላይም አምስት ሄሊኮፕተሮች የነፍስ አድን ተልዕኮውን ተቀላቅሉ። 12 ሰዎችን በአንድ ጊዜ አሳፍረው ማውጣት ጀመሩ።
ፈዘው እና ተዳክመው የነበሩት ሞስ እና ትሬሲ ወደ ኋላ ከቀሩት ውስጥ ሆኑ።
"መርከቧ ላይ ስንሯሯጥ አንድ ነገር ተገነዘብኩ። ኦሺኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች አይቻለሁ። ሰዎችን በማዳን ላይ በነበረበት በኩል ማዕበሉ ሲሰነጠቅ እናያለን" ብሏል ሞስ።
ሞስን የያዘው ሄሊኮፕተር ሣሩ ላይ ሲነካ የመርከቡ ተሳፋሪዎች እየዘፈኑ እና እየጮሁ ወደ እርሱ ሮጡ። ሁሉም በየተራ አቀፉት።
"ማልቀስ ጀመርኩ። ከዚያም ወደቅሁ" ይላል።
እአአ ነሐሴ 4 ቀን 1991 አውሮፕላኗ የመጨረሻው ሰው ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ስፋራ ከወሰደች ከ45 ደቂቃዎች በኋላ ኦሺኖስ ውሃው ውስጥ ሰመጠች። በነፍስ አድን ጀልባዎች የተጫኑት በሙሉ ወደ መርከቦች ተዘዋወሩ። በሚያስደንቅ ሁኔታ የአንድም ሰው ሕይወት አልጠፋም።
አሁን በሊቨርፑል የሚኖሩት ሞስ እና ትሬሲ ለብዙ ዓመታት የክሩዝ መርከብ ሙዚቃ ተጫዋቾች ሆነው መሥራታቸውን ቀጥለዋል። ከሦስት አስርት አመታት በኋላ እንኳን ትሬሲ ስለ መርከቧ መስመጥ ወይም ሁሉም ህይወታቸውን ለማጣት ምን ያህል እንደተቃረቡ ማሰብን አትፈልግም።
ስለ ኦሺኖስ ብዙጊዜ የተጠየቀው ሞስ ግን ስለጉዳዩ ማውራት ከባድ ሆኖ አግኝቶታል። ስላለፈው ነገር በታላቅ እፎይታ ውስጥ ሆኖ ያስታውሳል።
"እኔ የማልበገር አይደለሁም። ነገር ግን ያንን ማለፍ ከቻልኩ ማንኛውንም ነገር ማለፍ እችላለሁ" ይላል ሞስ።
የኦሺኖስ ካፒቴን እና ሌሎች አራት ከፍተኛ መኮንኖች በመርከቧ መስጠም ላይ ቸልተኛ ሆነው በመገኘታቸው ግሪክ ውስጥ ተጠያቂ ሆነዋል።