ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ ኮሪያውያን ዕድሜ ከሌላው ዓለም በተለየ ለምን የአንድ ዓመት ጭማሪ ኖረው?
"ዕድሜህ/ ሽ ስንት ነው?" ቀጥተኛና ግልጽ መልስ ያለው ቀላል ጥያቄ ነው። ለደቡብ ኮሪያውያን ግን ይህ ቀላል አይደለም።
መልሳቸው እንደጠያቂው ሊለያይ ይችላል። መልሱን ቶሎ ላታገኙም ትችላላችሁ። አሊያም ሦስት መልስ ሊሰጣችሁ ይችላል ወይም ደግሞ ጥያቄው ለምን እንዳስፈለገ መልሰው እናንተኑ ሊጠይቋችሁ ይችላሉ።
ለምሳሌ አንዲት ደቡብ ኮሪያዊት ጋር ተዋውቃችሁ ፓስፖርቷን ብታዩት ዕድሜዋ 26 ሆኖ ልታገኙት ትችላላችሁ። ምን አልባት እርሷን ብትጠይቋት ደግሞ 27 ልትላችሁ ትችላለች። እንደ ተወለደችበት ወር ሁኔታም 28 የሚል ቁጥር ልትሰሙ ትችላላችሁ።
ለመሆኑ የደቡብ ኮሪያውያን ዕድሜ ለምን እንደዚህ ተለያየ?
በደቡብ ኮሪያ አንድ ህጻን ገና ሲወለድ አንድ ዓመቱን እንዳከበረ ይቆጠራል። ይህ ብቻ ሳይሆን ይህ ህጻን በፈረንጆቹ ታኅሳስ ወር [የአሮጌው ዓመት መጠናቀቂያ ወር] ላይ ከሆነ የተወለደው አዲስ ዓመት ሲገባ ሌላ አንድ ዓመት ይጨመርለታል።
በመሆኑም በዚህ ስሌት ታኅሳስ መጨረሻ የተወለደ ህጻን በቀናት ውስጥ የሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ህጻን ይሆናል ማለት ነው።
የአገሪቷ ተመራጭ ፕሬዚደንት ዮን ሴክ-ዮል ይህን ለዘመናት የነበረውን የዕድሜ አቆጣጠር ዘዴ እንዲቀር ግፊት እያደረጉ በመሆኑ በቅርቡ ሊቀየር የሚችል ይመስላል።
የተመራጩ ፕሬዚደንት የሽግግር ኮሚቴ ኃላፊ ሊ ዮንግ ሆ እንዳሉት የሚመጣው አስተዳደር ደቡብ ኮሪያን ከቀሪው ዓለም ጋር ለማስማማት ዕድሜ የሚቆጠርበትን መንገድ ወጥ የማድረግ ፍላጎት አለው።
ሊ አክለውም የተለያየው የዕድሜ ስሌት መደናገርን የፈጠረ ሲሆን አላስፈላጊ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዋጋዎችንም እያስከፈለ ነው ብለዋል።
ይህንኑ ለመለወጥ በቅርቡ የቀረበው ረቂቅ ሕግም በአንዳንዶች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ይመስላል። ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ሕጉ በትክክል ተግባራዊ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።
አንድ ጥያቄ፣ ሦስት መልሶች
በኮሪያ የአንድን ሰው ዕድሜ ለመቁጠር ሦስት መንገዶች አሉ።
አገሪቷ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1962 ጀምሮ በሕግ ትርጓሜዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የአንድን ሰው የውልደት ቀን መሠረት ያደረገውን ዓለም አቀፍ የዕድሜ አቆጣጠር በይፋ ትጠቀማለች። ይህ አንደኛው መንገድ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ግን ሌላም የዕድሜ አቆጣጠር አላት።
ይህም አንድ ሰው ሲወለድ ዕድሜው ዜሮ ሆኖ በፈረንጆቹ ጥር አንድ ቀን ሲደርስ አንድ ዓመት ተብሎ መቆጠር ይጀመራል። በዚህ አቆጣጠር መሠረት አንድ ህጻን ታኅሳስ 2020 ቢወለድ በጥር 2022 ሁለት ዓመት ይሆነዋል ማለት ነው። ይህም በዕድሜው ላይ የአንድ ዓመት ጭማሬን ያመጣል።
ይህ የዕድሜ አቆጣጠር በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው የውትድርና አገልግሎት ምዝገባንና ታዳጊዎች ከጥቃት መጠበቅ ያለባቸውን ዕድሜ መወሰንን ጨምሮ በርካታ ሕዝቦች ላይ ተፅዕኖ ለሚያሳድሩ ሕጋዊ ጉዳዮች 'ሕጋዊ ዕድሜን' ለመወሰን ነው።
ሌላኛው የኮሪያውያን የዕድሜ ስሌት ደግሞ ማንኛውም ማኅበረሰብ የሚጠቀምበት ነው። በዚህ ስሌት መሠረት ማንም ሰው ሲወለድ ዕድሜው አንድ ተብሎ ይጀመራል። ከዚያም በየትኛውም ወር እና ቀን ቢወለድም የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በገባ ቁጥር አንድ ዓመት ይጨመራል። ታኅሳስ 30 የተወለደ ህጻን ጥር ላይ የሁለት ዓመት ህጻን ይሆናል ማለት ነው።
የኮሪያ የዕድሜ አቆጣጠር መንገዶች በሰዎች ዕድሜ ላይ የሚፈጥሩትን ልዩነት በግልጽ ለማስረዳት ሌላ ምሳሌ እናንሳ።
አንድ ሰው በታኅሳስ 30፣ 1995 ቢወለድ በኮሪያውያን ዕድሜ አቆጣጠር 28 ዓመቱ ይሆናል። በዓለም አቀፉ አቆጣጠር 26 ዓመት አሊያም በሌላኛው ለሕጋዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በሚውለው የኮሪያ የዕድሜ አቆጣጠር ደግሞ 27 ዓመት ይሆነዋል ማለት ነው።
ይህ ለአንዳንዶች ቁጥር ብቻ ሊሆን ይችላል። በደቡብ ኮሪያውያን ዘንድ ግን የዕድሜ ጉዳይ በቁም ነገር ነው የሚታየው።
በኮሪያ ዩኒቨርሲቲ የኮሪያ ቋንቋ እና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ሺን ጂ ያንግ " በማኅበራዊ አውድ ሲታይ ለደቡብ ኮሪያውያን አንድ ሰው በዕድሜ ከእነርሱ እንደሚበልጥ አሊያም እንደሚያንስ ማወቅ የአንድን ሰው ስም ከማወቅ የበለጠ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ያንን ሰው እንዴት ማናገር እና መቀበል እንዳለባቸው እንዲሁም የክብር መጠሪያ አሊያም ማዕረግ ያስፈልገው እንደሆነ ለመለየት ወሳኝ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኮሪያ የዕድሜ አቆጣጠር ባህል መነሻው ቻይና እና የተለያዩ የእስያ አካባቢዎች እንደሆኑ ይነገራል።
ይሁን እንጂ ደቡብ ኮሪያ በእነዚህ መንገዶች ዕድሜን የምታሰላ ብቸኛዋ አገር እንደሆነች ይታመናል።
በሃንሱንግ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ፖሊሲ ፕሮፌሰር ኪም ኡን ጁ እንደሚሉት ሉላዊነት [ግሎባላይዜሽን ] ኮሪያውያን ዓለም አቀፋዊ የሆነውን የዕድሜ አቆጣጠር ይበልጥ እንዲያውቁ አድርጓቸዋል።
በዚህ የዕድሜ አቆጣጠር ደቡብ ኮሪያውያን መሳቂያና መሳላቂያ እንደሆኑ ማሰባቸው በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ይላሉ ፕሮፌሰር ኪም።
ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ተፅዕኖ ነበራቸው።
ለምሳሌ አንዳንድ ወላጆች ታኅሳስ ወር ላይ የተወለዱ ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ውስጥ እና በቀጣይ ሕይወታቸው ችግር ይገጥማቸዋል በሚል የልደት ምዝገባ ሥርዓቱን ለማጭበርበር ሞክረዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የጤና ባለሥልጣናት ክትባት ለመከተብ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ዕድሜ ሲለዩ ዓለም አቀፉን እና የኮሪያውያንን የዕድሜ አቆጣጠር በመለዋወጥ ከተጠቀሙ በኋላ በሕዝቡ ዘንድ መደናገር በመፍጠሩ የተወሰነና ወጥ የሆነ የዕድሜ አቆጣጠር እንዲኖር ጥሪ ሲቀርብ ነበር።
የተመራጩ ፕሬዚደንት የሽግግር ኮሚቴ ኃላፊ ሊም ተጨማሪ ደመወዝ ለመጠየቅ እና ጡረታ ለማስከበር በሚደረግ ሂደት ባለው 'የዕድሜ ትርጓሜ' መምታታት ምክንያት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያመሩ የሕግ ጉዳዮች መኖራቸውን በመጥቀስ "በኮሪያውያን የዕድሜ አቆጣጠር ምክንያት የሚፈጠር መደናገር አላስፈላጊ የሆነ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዋጋ" እያስከፈለ ነው ብለዋል።
ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው?
የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት በአገሪቱ ወጥ የሆነ የዕድሜ አቆጣጠር ዘዴን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በ2019 እና 2021 ሁለት ሕግ አውጪዎች በተመሳሳይ መንገድ ረቂቅ ሕጎች ያቀረቡ ቢሆንም በኮሪያ ምክር ቤት ሊጸድቅ አልቻለም።
ባለሙያዎችም ከአስተዳደራዊ ሁኔታ አንጻር በረቂቅ ሕጉ ላይ ቢስማሙም አዲሱ የዕድሜ አቆጣጠር ለኮሪያውያን ምን ትርጉም ይሰጣል? በሚል አንድ አቋም ሳይኖራቸው ቀርቷል።
በዳንኩክ ዩኒቨርሲቲ በኦሬንታል የጥናትና የምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጃንግ ዮ ሱንግ የኮሪያውያን ዕድሜ የማኅበረሰቡ ባህል መገለጫ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን " የእኛ ማኅበረሰብ ለወግና ባህሉ ግድ ያለው አይመስልም። የራሳችንን መለያ እና ባህላችንን ትተን ተመሳሳይ የመሆን አደጋ ውስጥ ነን?" ሲሉም ይጠይቃሉ።
እዚህ ላይ ግን ሁሉንም የሚያስማማው ሃሳብ ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊው የዕድሜ አቆጣጠር ተቀባይነት ቢኖረውም ኦፊሴላዊውም ሆነ ኦፊሴላዊ ያልሆነውን የኮሪያውያን ዕድሜ አቆጣጠር ኮሪያውያን በቅርቡ መጠቀም ያቆማሉ ተብሎ አለመታሰቡ ነው።