መስማት የተሳናቸውን ግለሰቦች በመቅጠር መድሎን የሚታገለው የኬንያው ካፌ

የፓሌ ካፌ መስማት የተሳናት አስተናጋጅ

የፎቶው ባለመብት, Peter Njoroge/BBC

የምስሉ መግለጫ, የፓሌ ካፌ መስማት የተሳናት አስተናጋጅ

በተከታታይ ከአፍሪካ ጋዜጠኞች በሚጽፏቸው ደብደባቤዎች ፕሮግራማችን እስማኤል ኤይናሼ በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ የሚገኘውንና አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ያለውን አሉታዊ እሳቤ ለመቀየር እየታገለ ስላለው ካፌ ደብዳቤ ጻፈልን።

Short presentational grey line

በናይሮቢ የበለጸገ ስፍራ ከሚባሉት መካከል ላቪንግተን በሚባለው ሰፈር የሚገኘው ፓሌ ካፌ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ተስፋ እንዴት እንደሚለመልም መንገዱን ያመላከተ ማህበራዊ ሙከራ ነው።

በሁሉም የህይወታቸው ዘርፍ ማለት ይቻላል በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ መገለልና መድሎ ያዩ መስማት የተሳናቸው ሰራተኞችን በመቅጠር ከማህበረሰቡ ጋር እንዴት አይነት ውህደት መፍጠር ይቻላል የሚለውንም ያሳየ ነው።

ፓሌ ካፌ ልብን የሚሰርቅ እይታ አለው፤ ሰፊ መናፈሻ፣ የአትክልት ስፍራ፣ የዮጋ መስሪያ ቦታ፣ የጌጣጌጥ መሸጫ ቦታ ያለው ሲሆን ስፍራው በጸጥታ የተሞላ ነው። አስተናጋጆቹ ማስታወሻቸውን ይዘው በየደንበኞቹ ፊት የሚቆሙ ሲሆን የምልክት ቋንቋ ከቻሉ በምልክት፣ ወይም ከምግብ ዝርዝሩ ላይ በመጠቆም እንዲሁም በማስታወሻው ላይ በመጻፍ ይስተናገዳሉ።

ካፌውም ውስጥ መሰረታዊ የሚባሉ የምልክት ቋንቋዎች ፖስተር ተለጥፏል። አስተናጋጆቹ ቀዝቃዛ ከሆነ ምርጫዎ ሰውነታቸውን እንደበረደው አድርገው ያሳዩዎታል እርስዎም ምርጫዎ ቀዝቃዛ ከሆነ አዎ ለማለት አውራ ጣትዎን ወይም ግንባርዎን በመነቅነቅ ማሳየት ብቻ ነው።

የተቀቀለ እንቁላል፣ በደንብ ወይስ በመካከለኛ ሁኔታ ነው የተቀቀለው ለማለትም ጣቶችዎን በማንቀሳቀስ ማሳየት ነው። አስተናጋጆቹ የደንበኞቹን ሁኔታ በቅርብ ርቀት ሆነው የሚከታተሉ ሲሆን መሃል ላይም እየተስተናገዱ ያለበትን ሁኔታ ለመጠየቅ በመምጣት ፈገግ ብለው ያዩዎታል ወይም በምልክት የሚፈልጉት ነገር ካለ ይጠይቁዎታል።

የፓሌ ካፌ መስማት የተሳናት አስተናጋጅ

የፎቶው ባለመብት, Peter Njoroge/BBC

የምስሉ መግለጫ, የፓሌ ካፌ መስማት የተሳናት አስተናጋጅ

ከሶስት አመታት በፊት ፓሌ ሲከፈት በአስተናጋጅነት የተቀጠረው ኤድዋርድ ካማንዱ በአሁኑ ወቅት የካፌው ስራ አስኪያጅ ሆኗል።

የ26 አመቱ ወጣት ኤድዋርድ የካፌው ባለቤት ፈይሰል ሁሴን "አንድ ነገር እንዳለኝ ስላዬ ዕድሉን ሰጠኝ" ብሏል

ሥራ ፈጣሪና የቀድሞ የረድኤት ሠራተኛ ፈይሰል እንደ እንቁላል ቤኔዲክት እና በቅመም የተለወሰውን የሰሜን አፍሪካ እንቁላል ሻክሹካ ምግብ የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን አካል ጉዳተኞችን ወደ ስራ የሚያስገባና የሚደግፍ ቦታን ለመክፈት ነበር አላማው።

"ራዕዬ መስማት የተሳናቸውን የማህበረሰቡ አካል መደገፍ ነበር" ሲል በአሁኑ ወቅት ሶስት ቅርንጫፎች ስላሉት ፓሌ ካፌ ያስረዳል።

በዚህ በላቪንግተን ቅርንጫፍ ከ 40 ሰራተኞች ውስጥ ከ 30 በላይ የሚሆኑት የመስማት እክል ያለባቸው ወይም ሙሉ በሙሉ መስማት የተሳናቸው ናቸው.

ኤድዋርድ በዚህ ካፌ ለችሎታው ዋጋና ክብር እንደሚሰጠው ያምናል ""በኩባንያችን ውስጥ መድልዎ የለም፣ እዚህ ነፃነት አለ" ይላል።

ኤድዋርድ ከሶስት አመት በፊት በዚህ ካፌ ሲቀጠር ዓይናፋርና ይፈራ ነበር የሚለው አለቃው በአሁኑ ወቅት ግን እሱን ከካፌው ነጥሎ ማሰብ የማይቻል ሆኗልም ይላል።

ኤድዋርድ ባለው የስራ ኃላፊነት ሰራተኞቹን ብቻ ሳይሆን የፋይናንሱን ሁኔታ ይቆጣጠራል እንዲሁም አቅርቦቶችን ይከታተላል።

ስራውን አጥብቆ እንደሚወድ የሚመሰክርለት አለቃው በተለይም ሰራተኞቹ በአገልግሎታቸውና በሙያቸው ሲመሰገኑ ኩራት ይሰማዋል ይላል።

አብዛኛዎቹ የካፌው ሰራተኞች ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠሩበት እንደመሆኑ መጠን ህይወታቸውንም ለውጦታል።

አስተናጋጆች በካፌ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Peter Njoroge/BBC

ለፈይሰል ካፌው በጀመረበት ወቅት መስማት የተሳናቸውን ሰራተኞች ማግኘት ፈታኝ ነበር በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ መስማት የተሳናቸው ኬንያውን ለመቀጠር ሲቪያቸውን ያመጣሉ።

እንዲያውም ካፌው በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ሌሎች የንግድ ተቋማትም መስማት የተሳናቸው ሠራተኞችን መቅጠር ይችሉ ዘንድ እንዲረዳቸው ጠይቀውታል።

ኤድዋርድ እንደሚናገረው በኬንያ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ትልቁ እንቅፋት በመጀመሪያ ደረጃ የስራ እድል ማጣት ነው።"የስራ እድል የሌላቸው በጣም ብዙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሉ" ይላል።

በአገሪቱ ከ600 ሺህ የማያንሱ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዳሉ ይታሰባል፣ ምንም እንኳን በአካል ጉዳተኝነት ምክንያት የሚደረግ አድሎ በሕገ መንግሥቱ የተከለከለ ቢሆንም፣ በጤና፣ በትምህርትና በሥራ ዕድል ዙሪያ ትልቅ እንቅፋት እየገጠማቸው ነው።

የካፌው ባለቤት ፈይሰል ሁሴን

የፎቶው ባለመብት, Peter Njoroge/BBC

የምስሉ መግለጫ, የካፌው ባለቤት ፈይሰል ሁሴን

የኬንያ የምልክት ቋንቋ በሰፊው ህዝብ ዘንድ አልተስፋፋም እንዲሁም በባለሥልጣናት ዘንድም ቢሆን እምብዛም አይታወቅም።

እንዲሁም በኬንያ ውስጥ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች በጣም ጥቂት ሲሆን ብቃት ያላቸውን ሙያተኞችን ለመመዝገብም ሆነ ለመፈተሽ በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ስርዓት የለም።

ምንም እንኳን የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች የምልክት ቋንቋን በፕሮግራሞቻቸው ውስጥ ማካተት አለባቸው ቢባልም እንኳ ይህንኑ የሚያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

ኤድዋርድ ራሱን ለመግለፅ መናገር ይችላል ነገር ግን በርካታ ባልደረቦቹ መናገር አይችሉም።

"በአገራችን ስለ መስማት የተሳናቸው ግንዛቤ ይፈጠር ዘንድ ትምህርት ያስፈልጋል" ይላል።

አንድ መስማት የተሳነው ጓደኛው ናይሮቢ ውስጥ ፖሊስ አስቁሞት መታወቂያውን እንዲያሳየው ስለተጠየቀበት የቅርብ ጊዜ ገጠመኙ ነገረኝ።

"ወደ እስር ቤት ሊወስዱት ዛቱበት። እሱ ግን ሊመልስላቸው አልቻለም።" ይላል።

ኤድዋርድ ጓደኛው ወዳለበት መጥቶ መስማትም ሆነ መናገር የተሳነው መሆኑን ለፖሊስ ማስረዳት ነበረበት።

እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች መስማት የተሳናቸው ሰዎች በመጥፎ አጋጣሚዎች ብዙውን ጊዜ መደጋገፍ እንዳለባቸው አስተምረውታል።

ፓሌ ካፌ ኤድዋርድ በሙያው እንዲበለጽግ የረዳው ስፍራ ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም ያገኘበት ቦታ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሚስቱ የሆነችውን ጃክሊንን የተዋወቃት በዚሁ ስፍራ ነው። መስማት የተሳናት ሚስቱ በፓሌ ካፌ በአስተናጋጅነት ትሰራለች።

በአሁኑ ወቅትም ጎድዊል የሚባል የ11 ወር ጨቅላ ህፃን ያላቸው ሲሆን መስማት ይችላል። ኤድዋርድ የልጁንም ፎቶ ከስልኩ ላይ በኩራት ያሳያል።

"በዚህ ካፌ ምክንያት ወደሚቀጥለው የህይወት ምዕራፍ ተሻገርኩ" ይላል።