በዋግ ኽምራ ዞን ያለው የምግብ እጥረትና ሕፃናት ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን አልሚ ምግብ ባለመኖሩ ጥቂት የማይባሉ ሕጻናት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎችና አንድ ኃላፊ ለቢቢሲ ገለጹ።

የአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ ከሚገኘው የትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰንበት የዋግ ኽምራ ዞን የተወሰነ አካባቢ በህወሓት ቁጥጥር በመሆኑ በርካታ ሰዎች እየተፈናቀሉ እየወጡ ነው።

በዚህም ሳቢያ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትን ጤናና ህይወት ለመታደግ የሚያስችል ድጋፍ በአስቸኳይ ማግኘት ካልተቻለ አስከፊ ነገር ሊከሰት እንደሚችል የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"አሁን ሕፃናት አፋቸውና አፍነጫቸው ቆስሏል። እንደተላላፊ በሽታ ይህ እያደገ ይሄድና ከ77ቱም የበለጠ እልቂት ሊኖር ይቸላል። ምግብ የሌላቸው ሕፃናት በሽታ ሲጨመርባቸው የሚከሰተው ችግር ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው" ብለዋል።

ኃላፊው የዞኑ አብዘኛው ቆላማ ወረዳዎች በድርቅ በመጎዳታቸው፣ በቂ የሰብል ምርት ባለመኖሩ እንዲሁም በርካታ አካባቢዎች በህወሓት ቁጥጥር ሥር ስለነበሩ ከ61 ሺህ 600 በላይ ተፈናቃዮች በዞኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከተፈናቃዮቹ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት 18 ሺህ 700ዎቹ ሲሆኑ በመደበኛ መጠለያ የሚገኙት ከ2 ሺህ እንደማይበልጡ ያነሱት ኃላፊው የተቀሩት ተፈናቃዮች ግን ከመጠለያ ውጪ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ለእነዚህ ተፈናቃዮች አስፈላጊውን ማኅበራዊ አገልገሎት በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አለመቻል የዞኑ ዋነኛ ችግር ነው ብለዋል።

ነዋሪዎችና ተፈናቃዮችም ችግሩ እየባሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥትና የእርዳታ ድርጅቶች ለሕጻናት ልጆች እና ለእነሱም ህይወት መቆየት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

"የሕፃናት አልሚ ወይም ተጨማሪ ምግብ በጣም እየተቸገርን ነው። እሱ ነው አንዱ ትልቁ አደጋ የሆነው" የሚሉት አቶ ከፍያለው ለሕፃናት ታስቦ የተዘረጋ በቂ የምግብ አቅርቦት ሥርዓት የለም ብልዋል።

የሕፃናት ምግብ አቅርቦት "ተከታታይነትና ቀጣይነት ያለው ከመሆን ረገድ ችግር ስላለ ሕፃናት በምግብ እጥረት እየተጎዱ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት የምግብ እጥረቱ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት ቁጥር በትክክል ባይታወቅም "ተፈናቃዮችም ይሁኑ ተፈናቃይ ያልሆኑ [በዞኑ ያሉ] ሁሉም ሕፃናት አልሚ ወይም ተጨማሪ ምግብ ይፈልጋሉ።"

በሌላ በኩል በአካባቢው ለአዋቂዎች የሚሆኑ የምግብ ግብአቶች ከተለያዩ ለጋሾች ቢቀርቡም በዞኑ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ባለመኖሩና በሌሎችም ችግሮች ተፈናቃዮች ምግቦቹን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

ችግሩ ምን ያህል የከፋ ነው?

አቶ ከፍያለው ችግሩ እስካሁን የሰው ሕይወት አለመቅጠፉን ገልጸው ነገር ግን በአልሚ ምግብ እጥረት 15 ሕፃናት በበሽታ ተይዘው በጤና ጣቢያ ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግዋል።

አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ሥር ያሉ አካባቢዎች በመኖራቸው ችግሩ ከዚህም ሊከፋ እንደሚችል አመላክተዋል።

የአዋቂዎች የምግብ እጥረት ባለመኖሩ ሙሉ ለሙሉ ረሃብ አለ ለማለት ያስቸግራል የሚሉት የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው "ሆኖም ግን የሕፃናት ምግብ የለም። ምግብ ከሌለ የሕፃናት ረሃብ አለ። ሕፃናት ላይ ችግር ተከስቷል። ስለዚህ ለእነዚህ ሕፃናት አልሚ ወይም ተጨማሪ ምግብ የሚሰጥ፣ የሚደርስልን አካል ያስፈልጋል" ሲሉ አስረድተዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ሰሞኑን በዞኑም ይሁን በሌሎች የማኅበራዊ ትስስር ገጸች የሚዘዋወሩ ፎቶዎች የችግሩን አስከፊነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የፌደራልና የክልል መንግሥታትም ሆነ ለጋሽ ድርጀቶች በሕፃናት ምግብ እጥረት ለተከሰተው ችግር መፍትሄ እንዲሰጡ እና ከመደበኛ መጠለያ ውጪ ያሉ ተፈናቃዮች ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀዋል።

መንግሥት የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ መሆኑን ገልጸው ከችግሩ አኳያ ግን በቂ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

ኃላፊው ተፈናቀዮቹ ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉ ሲሆን በአስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል።

የዞኑ አስተዳደር አካል የሆኑት አበርግሌ፣ ፃግብጅ ወረዳ እና የዝቋላ ወረዳ 6 ቀበሌዎችን ጨምሮ የተለያዩ አከባቢዎች አሁንም ድርስ በህወሓት ቀጥጥር ሥር ናቸው ያሉት ኃላፊው፣ ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻል አሁን ያለውን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ "ትልቁ መፍትሄ" ነው ብለዋል።

በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው እና በርካታ ሕፃናት በመቀንጨር የሚጎዱበት ዞኑ አሁን የደረሰበት ችግር "በእንቅርት ላይ. . ." የሚባል ነው።

አካባቢው በትግራይ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ከ151 ሺህ የሚልቁ ሰዎች በምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የተካተቱበት ነበረ።

ከ182 በላይ የዞኑ ነዋሪዎች ደግሞ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ነበሩ።

ታዲያ አሁን የተከሰተው ድርቅ፣ ጦርነትና መፈናቀል የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ከነበረው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳናረው ይታመናል።