ባለፈው ሳምንት ወደ መቀለ የተላከው እርዳታ ለምን ሳይደርስ ቀረ?

ባለፈው ሳምንት ምግብና ነዳጅ ጭነው ወደ ትግራይ ተንቀሳቅሰው የነበሩ ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎች በገጠማቸው ችግር ምክንያት መመለሳቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ተናገሩ።

ዶክተር ለገሠ ቱሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የአፋር ወረዳዎች በኩል የእርዳታ አቅርቦት ይዘው ወደ ትግራይ እንቅስቃሴ ጀምረው የነበረ ቢሆንም በህወሓት ኃይሎች ጉዟቸው መደናቀፉን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ መጋቢት 08/2014 ዓ.ም. የእርዳታ ምግብ እና ነዳጅ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሰመራ ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ እየተጓዙ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።

በዚህም ወደ ትግራይ የተንቀሳቀሱት 20 የእርዳታ ምግብ እንዲሁም ሦስት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውንና፣ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላትም በየቀኑ 40 መኪኖች የሰብዓዊ አቅርቦቶችን እንዲያጓጉዙ እንደሚደረግ ጨምሮ ገልጾ ነበር።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከረዥም ጊዜ በኋላ ባለፈው ሣምንት 23ቱ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲጓዙ የተደረገው የህወሓት አማፂያን በአገር መከላከያ ሠራዊትና በአፋር ክልል ኃይሎች ስለተዳከሙ "መንገዱን ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ ስለነበረ" ነው ብለዋል።

ምግብና ነዳጅ የጫኑት ተሽከርካሪዎች ሐሙስ ዕለት ወደ መቀለ ጉዞ ጀምረው እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ለገሠ፣ አብአላ - መቀለ ኮሪደር በሚባለው መስመር ላይ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ከሄዱ በኋላ ተኩስ ስለተከፈተባቸው ለመመለስ መገደዳቸውን ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፉት ቀናት በየብስ ወደ ትግራይ የተላከው የሰብዓዊ እርዳታ አለመኖሩን ለቢቢሲ የገለጸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ነዳጅ እና ምግብ ነክ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከአፋር መዲና ሰመራ ወደ መቀለ እየተጓዙ መሆናቸውን ካሳወቀ በኋላ ነበር።

መንግሥት ወደ ትግራይ እርዳታ እንዲቀርብ ባለው ፍላጎት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እንዲጓዙ የበኩሉን ቢያደርግም "የህወሓት ኃይሎች ከተለያየ ቦታዎች ተሰባስበው መንገዱን በድጋሚ በመዝጋታቸው" መኪኖቹ ወደተነሱበት መመለሳቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።

ዶክተር ለገሠ የህወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ መንገድ በመዝጋት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ ያደርጋሉ በማለት የከሰሱ ሲሆን፣ አክለውም "በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ሕዝብ የእርዳታ አቅርቦት ስላላገኘ በረሃብ አደጋ ላይ ነው በማለት ክስ ያሰማሉ" ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፈው ጨምረውም ለትግራይ ክልል ሕዝብ እርዳታ ለማቅረብ የህወሓት ኃይሎች መንገድ እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል።

"በተጨባጭ የእርዳታ መኪኖች ወደ ክልሉ እንዲገቡ መንገዱን ክፈቱ ሲባል አይከፍቱም" በማለት ለእርዳታ አቅርቦቱ መሠረታዊ ችግር የመንገድ መዘጋት መሆኑን አስረድተዋል።

ቢቢሲ መንግሥት ለእርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎል ምክንያት ነው ካለው ህወሓት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር ለገሠ ቱሉ ለቢቢሲ እንዳስረዱት ወደ መቀለ እንዲሄዱ ጉዞ ጀምረው የነበሩት የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመነጋገር በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት መቅረቡን አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ለገሠ ቱሉ፤ ይህ በህወሓት ኃይሎች ተኩስ ተከፍቶባቸው ከመንገድ የተመለሱት መኪኖች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ አፋር ልኳቸው በተመሳሳይ መዳረሻቸው ሳይደርሱ ከተመለሱት የተለየ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ እንዳስታውቀው፤ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ማለትም መጋቢት 10 እና 11/2014 ዓ.ም. መዳረሻቸውን አፋር ክልል ያደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሰመራ መነሳታቸውን ገልጿል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ በኢሜይል በሰጡት ምላሽ እነዚህ ተሽከርካሪዎች "መዳረሻቸው ትግራይ ሳይሆን ሰብአዊ እርዳታ ለሚጠብቁ በአፋር ክልል ውስጥ ላሉ ማኅበብረሰቦች ነበር" ብለዋል።

ይኹን እንጂ ተሸከርካሪዎቹ የታሰበላቸው ስፍራ ሳይደርሱ አፋር ውስጥ እክል እንደገጠማቸውና ወደተነሱበት ስፍራ መድረስ ባለመቻላቸው ከነጭነታቸው "ወደ ሰመራ ተመልሰዋል" በማለት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ጠቅሰዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአፋር ክልል ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች እርዳታ ለማቅረብ ጉዞ የጀመሩት መኪኖች እንዲቆሙ በማድረግ የእርዳታ እህሎችን የማውረድ እና ጉዟቸውን የማስተጓጎል ክስተቶች ስለመኖራቸው አንዳንድ ሪፖርቶች አመልከተዋል።

ዶክተር ለገሠም አልፎ አልፎ እንዲህ አይነት ክስተት እንደሚያጋጥም፣ ይህም ችግር "በዋነኛነት ወደ አማራ ክልል በሚሄዱት ላይ እና አንዳንዴ ደግሞ ለክልሉ ሕዝብ በሚቀርበው እርዳታ ላይ እንደሚከሰት" በመጥቀስ ይህንን ችግር ለመፍታት የአፋር ክልላዊ መንግሥት ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል በተጨማሪ መንግሥትና የረድኤት ድርጅቶች እርዳታ ከአፋር አራት ወረዳዎች ለተፈናቀሉ እየቀረበ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ለገሠ፣ ከዚህ አንጻር እስካሁን ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ለሚገኙ እና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፉን ለማድረስ ጥረቱን አላቋረጠም ያሉት ዶ/ር ለገሠ፤ መንግሥት በአየር በረራ ለሚደርሱ የእርዳታ አቅርቦቶች ፈቃድ ሰጥቶ ያለምንም ችግር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

"በየብስ ያልተቻለውን መንግሥት ከራሱም፣ ከረጂ ተቋማትም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላን በሳምንት ቢያንስ ሦስት ቀን እንዲመላለስ እያደረገ ነው" በማለት አለመቋረጡን አብራርተዋል።

አክለውም በአካባቢው ላይ መንግሥት ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለውም ያሉት ኃላፊው "መንገዱ ተከፍቶ በሠላማዊ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ከአካባቢው ሳይፈናቀል እርዳታውን በቀዬው እንዲያገኝ መንግሥት ይፈልጋል" ብለዋል።

ይኹን እንጂ በአሁኑ ወቅት በርካታ "የትግራይ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ሰቆጣ፣ ራያ ቆቦ እንዲሁም ወደ ኤርትራ እየፈለሱ" መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ለገሠ፣ ስለዚህ መንግሥት የምግብ እህል እርዳታው ሕዝቡ ባለበት እንዲቀርብለት ይፈልጋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በተደጋጋሚ እንደሚሉት ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ አስካሁን መቋጫ ባላገኘው ጦርነት ሳቢያ በትግራይ ክልል ከሚኖረው ሕዝብ ከአምስት ሚሊዮን የማያንሰው ሰብአዊ እርዳታ የሚጠብቅ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

ከትግራይ ክልል ባሻገር ጦርነቱ በተስፋፋባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ውስጥም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከመንግሥታቱ ድርጅት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።