ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ መቀለ እየተጓዙ ነው አለ
የእርዳታ ምግብ እና ነዳጅ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሰመራ ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ እየተጓዙ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ሐሙስ መጋቢት 08/2014 ዓ.ም. የእርዳታ ምግብ የጫኑ 20 እንዲሁም ነዳጅ የጫኑ ሦስት ተሸከርካሪዎች ከአፋር ሰመራ ወደ መቀለ እየተጓዙ ነው ብሏል።
መግለጫው በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላት በየቀኑ 40 መኪኖች የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ እንዲጓዙ ይደረጋል ሲል ገልጧል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በላይ የሰዎች ጤና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ዶ/ር ቴድሮስ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ የሚመሩት ድርጅት 95 ሺህ ሜትሪክ ቶን መድኃኒት ወደ ትግራይ ለማድረስ ፍቃድ አለማግኘቱን ተናግረዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ላለፉት 500 ቀናት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ውስጥ ያሉ 6 ሚሊዮን ሰዎችን ይፋዊ ባልሆነ እቀባ ሥር አድርገዋል ብለዋል።
የዋና ዳይሬክተሩን መግለጫ ተከትሎ ለኢትዮጵያ ዜና አገለግሎት (ኢዜአ) ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ኃላፊ ዶክተር ለገሠ ቱሉ ክሱ "ከእውነታው የራቀ እና መንግሥትን በሐሰት የወነጀለ ነው" ብለዋል።
ኃላፊው ጨምረው "ህወሓት የእርዳታ መተላለፊያ ኮሪደሮችን መዝጋቱን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላኖች በሳምንት ከሦስት ጊዜ በላይ ወደ ትግራይ እርዳታ እየተጓጓዘ” መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ለማድረስ ገንቢ ሚና እየተጫወት እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፤ የትግራይ ኃይሎች ግን በአፋር ክልል ላይ በከፈቱት ጥቃት የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ የሆነው የአብአላ መስመር በመዘጋቱ የእርዳታ አቅርቦት ሥራው መስተጓጎሉን ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከመጋቢት 7 ጀምሮ 17 ሰብዓዊ ድርጅቶች መድኃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዲያጓጉዙ ፍቃድ አግኝተዋል ብሏል።
ተጨማሪ 11 አጋር ድርጅቶች ደግሞ በአውሮፕላን 257 ሺህ 192 ኪሎ ግራም መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁሶች እና የምግብ አቅርቦት ወደ መቀለ ማድረሳቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጨምሮ አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ የተላከ የምግብ እርዳታ የለም ያሉ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 83 በመቶ የሚሆነው የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ አይደለም ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሚመሩት ድርጅት መርኅ በተቃራኒ ወገንተኝነትን እያንጸባረቁ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲከሳቸው መቆየቱ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ወራት በፊት እንዳለው በትግራይ ክልል ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር።