ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ መሆን የምታስበው የኤሮስፔስ መሃንዲሷ ቤቴልሔም
ቤተልሔም ግርማ ትባላለች።
ትምህርቷን አዲስ አበባ ውስጥ ልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ተከታትላለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለች- አምስት ኪሎ።
አምስት ኪሎ ሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ገባች። ግና አልገፋችበትም።
ጉዞ ወደ ቻይና።
"አምስት ኪሎ ሲቪል ምህንድስና ጀምሬ አቋርጬ ነው ወደ ቻይና የሄድኩት" ትላለች ቤተልሔም ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ።
ልጅ እያለች ጀምራ 'ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?' ስትባል 'አስትሮኖት' ነበር ምላሿ።
"በጣም ትንሽ እያለሁ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ? ስባል አስትሮኖት ነበር የምለው። ያኔ ስለ ህዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በማይወራበት ጊዜ ማለት ነው" ብላለች።
ብዙ ነገሮች ግን አምስት ኪሎ ስትገባ ወደ ሲቪል ምህንድስና እንድታዘነብል ገፋፍተዋታል።
"ከዚያ እያደግኩ ስመጣ ምርጫዬን አስተካከልኩ" ብላ ትጀምራለች። ". . . በአካባቢዬ ያሉትንም ሰዎች እየሰማሁ መጣሁ። አባቴም የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ ስለነበር እኔም ያንን ለመማር መረጥኩ" ትላለች።
ለትምህርቱ ያላት ፍላጎት ግን አልዘለቀም።
ውጤታማም አልነበረችም።
ለዚህም ነው "ወደ ፍላጎቴ፣ ወደምወደው ነገር መመለስ እንዳለብኝ አሰብኩ" የምትለው።
"ያቋረጥኩት አንደኛ ምክንያት የፍላጎት ማጣት ነው። በእኔ ፍላጎት ሳይሆን ያለውን ነገር ብቻ በማየት ነበር ሲቪል ምህንድስና ልማር የፈለግኩት። ብዙም ውጤታማ አልነበርኩም። ስለዚህ ወደምወደው ዘርፍ አቀናሁ" ትላለች።
ፍላጎቷን ለማሳካት ደግሞ ቻይናን መረጠች።
ሕልሟን ሸክፋ ጉዞ ወደ ቻይና።
"ቻይና ሄጄ በናንጂንግ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኤሮኖቲክስ ኤንድ አስትሮኖቲክስ ውስጥ ኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ አጥንቻለሁ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ ነው የሠራሁት" ስትል ትገልጻለች።
ኤሮኖቲክስ የበረራ ሳይንስ ነው። ኤሮኖቲክስ አውሮፕላን ወይም ሌላ በራሪ ቁስን የመንደፍም መስክ ነው።
ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? ሲባሉ ሐኪም፣ ፓይለት ወይም ጋዜጠኛ ሊሉ ይችላሉ። ቤተልሔምስ ለምን ኤሮኖቲክስን አስቀደመች?
"በልጅነቴ ደስ የሚሉኝ ነገሮች ነበሩ። በረራ እና ህዋ ላይ በጣም ፍላጎት ነበረኝ። በዚያ ላይ ደግሞ በጊዜው የነበረኝ ችሎታና ጥንካሬ ሒሳብ ትምህርት ላይ ነበር። በዚህ ምክንያት ወደዚህ ዘርፍ መጣሁ" ስትል ትመልሳለች።
ቤተልሔም መመረቅ ብቻ ሳይሆን በማዕረግ ጭምር ነው የተመረቀችው።
ትምህርቱ ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ ብዙ ጥያቄ ይቀርብላት ነበር።
"ሁሌም ካምፓስ እያልሁ ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት ስመጣ እና 'ምን እያጠናሽ ነው?' ብለውኝ ስነግራቸው ሰዎች 'እእእ እዚህ አገር ነው ለመሥራት የምታስቢው? እዚህ አገር ግን ያዋጣል?' ይላሉ። በጣም ለብዙ ሰው ጥያቄ ነበር የሚሆንበት።"
"ብዙ ሰው ኪሳራ እንደሆነ ነበር የሚያሰበው። መለስ ብለን ስናይ ግን በዓለማችን ብዙ ለውጥ አምጪ የሚባሉ ሰዎች አያዋጣም በሚባል መንገድ ሄደው ነው ለውጥ ያመጡት። እና የሆነ ሰዓት ላይ ወደዚያ አስተሳሰብ [አያዋጣም ተብሎ ለውጥ ማምጣት ላይ] ነበር የገባሁት" ስትል ትመልሳለች።
ግን አዋጣሽ? የቢቢሲም ጥያቄ ነበር።
"በትክክል አዎ። ያዋጣል የሚለውን ግን እንደ አተረጓጎማችን ይለያያል።'
ምን ማለትሽ ነው ታዲያ ያዋጣል ስትይ? ብለን ሌላ ጥያቄ ሰነዘርን።
"ማዋጣት ማለት በብር ብቻ ወይንም በገቢ ብቻ አይደለም። ለእኔ ያዋጣል ማለት የምወደውን ሥራ መሥራት መቻሌ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ነው የገቢ ጉዳይ መምጣት አለበት ብዬ የማምነው። የምወደውን ነገር ስሠራ በሚጠበቀው ደረጃ መሥራት እችላለሁ። ከዚያ ደግሞ ምርታማ መሆን እችላለሁ። እኔ እሱን መንገድ ነው መከተል የፈለግኩት" ስትል ትመልሳለች።
ፈተና የበዛበት የትምህርት ሕይወት
እዚህ ጋር ተማሪ ወደነበረችበት ጊዜ እንመልሳችሁ።
አንዳንዶች 'ምን እየተማርሽ ነው?' ሲሏት 'ኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ' እያለች ትመልሳለች።
ሰዎች ፊት ላይ የምታየውን ግራ መጋባት ለመቅረፍ ወይ ደግማ ትነግራቸዋለች ወይም ደግሞ "'የአውሮፕላን ኢንጂነሪንግ' ብዬ ለማስረዳት እሞክራለሁ" ትላለች።
ሰዎችን ስለምትማረው ትምህርት ማስረዳትማ ትንሹ ጉዳይ ነው።
ቤተልሔም መጀመሪያ ትምህርቷን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቋረጠች። ቀጥሎ ወደ ቻይና ባቀናችበት ወቅት ለአንድ ዓመት ቋንቋ መማር ነበረባት። በዚህ ሁሉ ምክንያት ለዓመታት ከጓደኞቿ ወደኋላ ቀርታለች።
አንዳንዶቹ ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል። ሌሎቹ ደግሞ ሥራም ጀምረዋል።
ይህም ከሌሎቹ ወደኋላ እንድትቀር አድርጓታል።
አሁንም ትንሽ ወደኋላ እንመልሳችሁ።
ትንሽ እያለች ወላጅ አባቷ በካንሰር ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የምትገልጸው ቤተልሔም "እናቴ ናት ለብዙ ጊዜ ብቻዋን ያስተማረችን" ሰትል ትገልጻለች።
እናቷ ውጭ ልከው ለማስተማር አቅም አልነበራቸውም። ቤተልሔም ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጀመረችው ትምህርት ይልቅ የነፍሴ ጥሪ ወደ ምትለው 'ኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ' ፍላጎቷ አዘንብሏል።
ስለዚህ ወደ ቻይና ስትሄድ ግማሹን በስኮላርሺፕ ግማሹን ደግሞ ሠርታ በመክፈል ለመማር ነበር ያቀደችው።
ቻይና ስትደረስ ግን ሁኔታው እንዳሰበችው አልነበረም።
"ሄጄ ሳየው የተለየ ነው። ትንሽ ከባድ ነበር። እንዳሰብኩት ቀላል አይደለም። ነገር ግን በዚያ ከባድ መንገድ ማለፌ የአሁኑ ማንነቴን ቀርጾታል ብዬ አስባለሁ" ትላለች።
ይህን አለፍኩ ስትል ሌላ ችግር ደግሞ ገጠማት- የሁለተኛ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለች ያጋጠማት የመኪና አደጋ።
ቻይና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢንተርንሺፕ (የሥራ ላይ ልምምድ) ትሠራ ነበር።
ወደ ቻይና ከመመለሷ በፊት ከአራት ሴት ጓደኞቿ ጋር ለመዝናናት ወደ ቢሾፍቱ አቀኑ። በዚህ ወቅት ነው አደጋው የደረሰባቸው።
አደጋው እንዴት እንዳጋጠማቸው ምንም አታውቅም። የነገሯትን ግን እንዲህ አጫውታናለች።
"እንደነገሩኝ ከሆነ" እያለች ነው ያወራችን "እንደነገሩኝ ከሆነ ወደ ቢሾፍቱ እየሄደን እያለ አውራ ጎዳና ላይ ሆነን አንድ መኪና ገጭቶን ጥሎን ሄደ። ከዚያ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ወሰዱን።"
"እስካሁንም ትዝታው የለኝም። ትዝ የሚለኝ [ሆስፒታል ውስጥ] ስነቃ መንቀሳቀስ አልችልም ነበር። ጭንቅላቴ ተመትቶ ስለነበር አንደኛ የአጭር ጊዜ የመርሳት ችግር ገጥሞኝ ነበር። ግራ ዓይኔ ከቦታው በመንቀሳቀሱ ደብል ቪዥን [ተደራራቢ ምስል ማየት] ሆኖ ነበር። የዳሌ አጥንቴም ተሰብሮ ነበር። መራመድ አልችልም ነበር። በክራንች ነበር የምራመደው። እንደዚህ ዓይነት ከባድ ጉዳት ነበር የደረሰብኝ።"
ከአራቱ ሴቶች ቤተልሔም እና ሌላ ጓደኛዋ ከኋላ ወንበር ነበር ተቀምጠው የነበረው። እነሱም ናቸው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው።
"እኔና ጓደኛዬ ከኋላ ነበር የተቀመጥነው። ጓደኛዬ በጣም ተጎድታ ታይላንድ ድረስ ሄዳ መታከም ነበረባት።"
"የመርሳት ችግሩ በየአምስት ደቂቃው ነበር የምረሳው። የድሮ ትውስታዎች ነበሩኝ። አሁን ያገኘሁትን ሰው ግን ከአምስት ደቂቃ በኋላ [በድጋሚ] ሰላም እላለሁ። በኋላ እየቆየ [መርሳቱ] በዛው ጠፋ።"
ቤተልሔም ሐኪም ቤት አንድ ሳምንት ቆየች።
ሕክምናዋን ስትከታተል ትምህርት ቤት 15 ቀን አረፈደች። 'ልናግድሽ ነው' የሚል መልዕክት ከዩኒቨርሲቲው ደረሳት።
ሐኪም ደግሞ ተጨማሪ የሦስት ወር ሕክምና እንደሚያስፈልጋት አሳውቋታል።
"ለትምህርቴ ብዙ ዋጋ በመክፈሌ ሐኪሞቹ ባይቀበሉም ክራንች ይዤ ሻንጣ እየጎተትኩ ወደ ቻይና ሄድኩ" ስትል ታስታውሳለች።
"ሰውነቴ ውስጥ ብዙ መድኃኒት ነበር። ክፍል ውስጥ [ትምህርቴን] መከታተል አልችልም፣ ያመኛል። ሥራ መሥራት አልቻልኩም። ውጤቴም መውረድ ጀመረ። በትኩረት ማጥናትም አልቻልኩም። ክፍል ውስጥ እንቅልፌ ይመጣ ነበር" ትላለች።
ሆኖም አደጋው ከስጋት ይልቅ ተስፋን ከሐዘን ይልቅ ደስታን ይዞላት መጣ። እንዴት?
"በጣም ከባድ ቢሆንም በውጭ ከሚታየው ይልቅ በውስጤ ጥንካሬና ከምንጊዜውም በላይ የመኖር ጉጉት ነበረኝ። ሕይወቴ የተቀየረበት ያን ጊዜ ይመሰለኛል። እንደ አዲስ እንደተሠራሁ ይሰማኛል። 'በጣም ደስ የሚልሽ አጋጣሚ' ስባል የመኪና አደጋው እላለሁ። ምክንያቱም በዚያ ችግር ባልፍም አዲስ አቅጣጫ የሰጠኝ አጋጣሚ ነበር። ወደዚያ ተመልሼ ሳስብ ደስ የሚል ትውስታ ነበረኝ" ስትል ሐሳቧን ታስረዳለች።
የግራ ዓይኗ አሁንም ምስል እየደራረበ ያሳያታል። "ኑሮ እንዳለ አልጋ በአልጋ መሆን የለበትም። ፈተና ቢኖርም መቀጠል አለበት። ሕይወት የተሟላ መሆን የለበትም" ስትል ትገልጻለች።
ጓደኛዋም ሕክምናዋን ተከታትላ ደህና ሆናለች። ሁሉም መሄድ ባለባቸው መንገድ እየተጓዙ ነው።
አራቱም ስለመኪና አደጋው እና ስለአጋጣሚያቸው የሚገልጽ መጽሐፍ በጋራ እየጻፉ ነው።
ትምህርቱ ተጠናቆ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ
ቤተልሔም ኢትዮጵያ ውስጥ ሕልሟን እየኖረች በሙያዋ እያገለገለች ትገኛለች።
በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ስፔንስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ረዳት ተመራማሪ ሆና እየሠራች ነው።
በኢንስቲትዩቱ በሚከናወኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈች ነው።
"በኤሮስፔስ ምህንድስና ጥናት እና ምርምር ዳይሬክቶሬት ውስጥ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እየሠራሁ ነው።"
"አንዱ የድሮን (የሰው አልባ አውሮፕላን) ፕሮጀክት ነው። ሌሎችም ደስ የሚሉ ፕሮጀቶች አሉን። ለምሳሌ የኤሮስፔስ ቤተ ሙከራ ለመገንባት አስበናል። ሥራውም ተጀምሯል። የኤሮስፔስ ቤተ ሙከራ እና ዎርክሾፕ ያካተተ ነው። ከእኛ ጥናት እና ምርምር ባለፈ የተለያዩ ተማሪዎችም ጥናት ማድረግ የሚችሉበት ቦታ ነው የሚሆነው" ስትል በኢንስቲትዩቱ ስለምትሠራቸው ሥራዎች ታስረዳለች።
በኤሮስፔስ ምህንድስና የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግር መርሃ ግብር የለም።
መርሃ ግብሩን ለማስጀመር በካሪክለም ቀርጻ የመሳተፍ ዕድልም አግኝታለች። ካሪኩለሙ ተገምግሞ አልፏል እና በቅርቡ ትምህርቱ መሰጠት ይጀምራል።
የቤተልሔም አሻራ በዚህ ብቻ አልተወሰነም።
ሌላው እና ብዙ ለውጥ ያመጣል የተባለለት የምትሳተፍበት ፕሮጀክት የግብርና ድሮን ነው።
ቤተልሔም እንደምትለው በኢትዮጵያ ያለው ኋላ ቀር የግብርና ዘዴ ዘርፉ ላይ እንድታተኩር አድርጓታል።
"አሁን እየሠራን ያለነው ኬሚካል ተሸክሞ የሚረጭ ተከስኮፕተር የሚባል ዓይነት ድሮን ነው።"
ድሮኑ ለእርሻ ሥራ ፀረ ተባይ እና ማዳበሪያ መርጨት የሚችል ነው።
ዓላማው ደግሞ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና ላይ ለውጥ በማምጣት ዕድገት ማስመዝገብ ነው።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከባህላዊ እርሻ ወደ ዘመናዊ በመቀየር ምርታማነትንም ለማሳደግ ነው።
"አርሶ አደሩ ብዙ ጊዜ የሚፈጅበትን ሥራ በድሮኖች በቀላሉ በትንሽ ደቂቃዎች ውስጥ መጨረስ ይችላል። ፀረ ተባይ እና ማዳበሪያ ከጤናም አኳያ በጣም አደገኛ ናቸው። ገበሬው በርቀት ሆኖ ድሮኑን እየተቆጣጠረ መሥራቱ ብዙ ጥቅም አለው" ስትል ስለምትሳተፍበት ፕሮጀክት ትገልጻለች።
የኢትዮጵያ ስፔንስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ዓላማ የሰው ኃይል መገንባት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉትን ነገሮች መሥራትንም ያካትታል።
ለግርብና ሥራ የሚውለው ድሮን ከዜሮ ነው የተጀመረው። አሁን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሥራ ተጠናቋል። ቀጣዩ ድሮኑን ገጣጥሞ መሞከር ብቻ ነው።
ቤተልሔም በቅርቡ በአፍሪካ የጠፈር ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ30 ዓመት በታች ያሉ ምርጥ 10 የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።
ጥቂት ሴቶች ብቻ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሁለት ወጣቶች ናቸው የተመረጡት።
"ከ30 ዓመት በታች ያሉ ምርጥ 10 የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች የሚለው ሽልማት በአፍሪካ ላሉ ምርጥ 10 የፈጠራ ሥራ ለሚሠሩ መሀንዲሶች፣ ተማራማሪዎች ወይም ደግሞ በህዋ ዘርፍ የተለየ ሚና የተጫወቱትን ለማስተዋወቅ የሚሰጥ ነው።"
"በየትኛው መስፈርት እንደተቀበሉኝ ባላውቅም በኤሮኖቲካል ምህንድስና አሁን የምሠራቸውን ሥራዎች አስገብቼ ነው የተመረጥኩት" ትላለች።
ለቤተልሔም በዝርዝሩ ውስጥ መካተቷን "ትልቁ ጥቅም በሰዎች አስተሳሰብ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ነው" ስትል ትገልጻለች።
አክላም "መመረጤ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። የተለያዩ ዕድሎችን ይከፍትልኛል። ወደፊት ብዙ በር እንዲከፈትልኝ ይረዳል። ከእኔ በላይ ግን ሌሎች ሰዎች 'ይህ ነገር አለ እንዴ?' እንዲሉ ያደርጋል" ትላለች።
ሌላው ቤተልሔም የምትሳተፈው 'ኢትዮ ስፔስ ኪድስ ክለብ' ውስጥ ነው።
ክለቡ በኢትዮጵያ በጠፈር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፍላጎትና ልዩ አስተዋጽኦ ያላቸውን ልጆች በመልመል ለማበራታት፣ ለማገዝ እና አቅማቸውን ለማሳደግ የተቋቋመ ነው።
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የተመረጡ ስድስት ልጆችን ይዘው ነው የጀመሩት።
ሌሎችን ለመቀበል ዝግጅታቸውን እያገባደዱ ነው።
ቢቢሲ፡ ምናለ እኔም ልጅ እያለሁ በዚህ ዓይነት ክለብ በተሳተፍኩ አላልሽም?
ቤተልሔም፡ [ሳቅ] በጣም ጥሩ ይሆን ነበር። ብዙ ነገር ይቀልልኝ ነበር። አሁንም የእኛ ልጆች ሲመጡ መሳተፍ ከቻሉ እንዳልከሰርኩ ነው የማስበው [ሳቅ]።
ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ተስፋ እና እንቅፋቶች የትኞቹ ናቸው?
ቤተልሔም፡ በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ዕድገት ብዙ ተስፋ እና ብዙ እንቅፋቶች አሉት። ተስፋ የምለው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ መጀመሩ ራሱ በአገራችን እና በሌላ አገር ያሉ ባለሙያዎችን መሳብ ጀምሯል። እኛንም እያገኙን ነው።
ስፔስ ሳይንስ ከዚህ በኋላ ከእኛ ብዙ የራቀ አይሆንም። ሕልም ሳይሆን እውን የሆነ ነገር ነውና የሚቀጥለው ትውልድ ይህንን ማስቀጠል ብዙ የራቀ አይሆንበትም። አሁን ብዙ ዕድል ከተፈጠረ ወደፊትም ይቀጥላል።
ከእንቅፋቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ብዬ የማስበው ዕቃዎች በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ከውጭ ነው የሚመመጡት። [ለግዢ] ከሚወጣው ገንዘብ ባለፈ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። አንዳንድ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳያልቁም ያደርጋል።
እንቅፋቶችን እንደ ዕድል ለሚቆጥር ሰውና በግሉ ዘርፍ እነዚህን ዕቃዎች የሚያመጡ ካሉ ትልቅ ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ። ተስፋም እንቅፋትም እያለን እንቅፋቶቹን ወደ ተስፋ እየቀየርን መሄድ ያለብን ይመስለኛል።
እስካሁን የህዋ ጣቢያ የመጎብኘት ዕድል እንዳላገኘች የምትገልጸው ቤተልሔም ዕድል ብታገኝ "ያለ ጥርጥር ስፔስ ኤክስን ብጎበኝ ደስ ይለኛል" ትላለች።
ወደ ህዋ ጣቢያ መጓዝ ብትችል 'ትልቅ ዕድል' መሆኑን ገልጻ ከዚያ በላይ ግን "ዕቀድ ይዤ አንድ ነገር ባበረክት ትልቅ ነገር ይመስለኛል" ትላለች።
በሙያዋ ውስጥ ካሉ ሰዎች ኤለን መስክ አርአያዋ እንደሆነ ትገልጻለች።
"ኤለን መስክ አይቻልም የተባሉ ነገሮችን እየሠራ ያሳየ ሰው ነው" በማለት ትጀምራለች።
"ኤለን መስክ አይቻልም የተባሉ ነገሮችን እየሠራ ያሳየ ሰው ነው። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብዙ የሚታሰቡ አልነበሩም። አሁን ገበያ ላይ በማዋል የነዳጅ መኪናዎች ከገበያ እንዲወጡ እየሠራ ነው። በተጨማሪም ስፔስ ሳይንስ ላይ ብዙ ነገር የሚያዘው በመንግሥታት ነው። በግለሰብ ደረጃ ገብቶ ናሳን እየተፎካከረ ነው። በአንዳንድ ሥራዎቹ ከናሳም የበለጠ መሆን ችሏል። ለእኔ ኤለን መስክ ጥሩ ነው" ስትል ታብራራለች።
በሕይወቴ ደግሞ አርአያዬ ክርስቶስ ነው የምትለው ቤተልሔም "ክርስቶስ ለሰው የሞተ እና የኖረ ነው። ለራሴ ምቹ ሕይወት መገንባት ሳይሆን በእኔ ሕይወት የሌሎችን ሕይወት መለወጥ ነው ዓላማዬ" ሰትል ትገልጻለች።
የቤተልሔም ጉዞዋ የውጣ ውረድም ቢሆን እዚህ ደርሷል። ወደፊትስ?
"እኔ ወደፊት የቴክኖሎጂ አንተርፕረነር [ሥራ ፈጣሪ] መሆን እፈልጋለሁ። እሱ ነው ሐሳቤ። በቅርቡ የራሴን ስታርት አፕ እጀምራለሁ። በዘርፉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ማሳደግ እና ዕቃዎችን በማስመጣት ለገበያ ማቅረብ አስባለሁ። በራሴ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት አቅጃለሁ" ስትል ትመልሳለች።
ቤተልሔም በእስካሁኑ ጉዞዋ ደስተኛ ናት። ቤተሰቦቿም ደስተኞች ናቸው። ያግዟታል። ምርጫዋን ደግፈው ከጎኗ ይቆማሉ። "በዚህም ዕድለኛ ነኝ" ትላለች።
"እኔ ግን ብዘገይም [ጓደኞቿ ከተመረቁ በኋላ በመመረቋ] የልፋቴን ዋጋ አግኝቻለሁ። የምፈልገው ዓይነት ሕይወት የምኖር ይመስለኛል። አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ።"
ስትመረቅ በጥሩ ውጤት በመሆኑ የቻይናው ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን እንድትከታተል ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቷት ነበር።
እሷ ግን "ወደ አገሬ ተመልሼ መሥራት እፈልግ ስለነበር ተመለስኩ" ስትል የመመለሷን ምክንያት ትናገራለች።
ሁለተኛ ዲግሪዋን ወደፊት ለመከታተል ዕቅድ አላት። ቻይና ላይሆን ይችላል የሚል ግምትም አላት።
ቢቢሲ፡ ለምን በሌሎች አገሮች ለመሥራት አልፈለግሽም?
ቤተልሔም፡ ወደ አገሬ ተመልሼ ለመሥራት ከመፈለጌም በላይ ሥራው በብዙ አገራት ምስጢራዊ ስለሆነ የሌላ አገር ሰው አይቀጥሩም።
ቢቢሲ፡ ቤተልሔምን ከአስር ዓመት በኋላ የት እናግኛት?
ቤተልሔም፡ በ10 ዓመት ውስጥ በአፍሪካ ትልቅ የቴክኖሎጂ ሶሉሽን አቅራቢ እና ለአፍሪካ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጣሪ ትሆናለች ብዬ አምናለሁ። ፈጣሪም ይረዳኛል [ሳቅ]።