ለመብረር የተዘጋጁት የደቡብ አፍሪካ ልጃገረዶች

የ14 ዓመቷ ፓባሎ (ፓቢ) ሌቅሆትሳ አራት መቀመጫ ካለው ትንሽ አውሮፕላን በደስታ ፈንድቃ ዘላ ወጣች።

"በጣም አስደናቂ ነበር። ተቆጣጥሬዋለሁ ብዬ አስቤ ነበር ገባህ?" ትላለች በደስታ እየተሽከረከረች። አውሮፕላንን መቆጣጠር ከጆሃንስበርግ ወጣ ብላ ከምትገኘው ሶዌቶ ከተማ ለመጣችው ታዳጊ ከህጻንነቷ ጀምሮ ስታልመው የነበረው ጉዳይ ነበር።

በግራንድ ሴንትራል አውሮፕላን ጣቢያ የአየር ማረፊያው ላይ ቆማ በደስታ ትጮሃለች፤ የደስታ ቃላትም ከአንደበቷ እየጎረፉ ነው።

"አውሮፕላኗ በጣም የምትግርም ናት። በጣም ደስ ይል ነበር።"

ከዚህ ደስታ ጀርባ ያለችው ለደቡብ አፍሪካ የፖሊስ አገልግሎት አብራሪ በመሆን የመጀመሪያዋ የደቡብ አፍሪካዊት ጥቁር ሴት ሬፊልዌ ሌዳብዌ ናት።

በተጨማሪም የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጥቁር ሴት ሄሊኮፕተር አብራሪ ናት። ይህም የስኬቷን ግማሽ እንኳን አይሆንም። ሬሊፍዌ ገርል ፍላይ ፕሮግራም ኢን አፍሪካ ፋውንዴሽን (ጅኤፍፒኤ) የተባለው እና ወጣት ሴቶችን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በሂሳብ እንዲሳተፉ አቅማቸውን ለማጎልበት ለተቋቋመው ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት መስራችም ናት።

በየዓመቱ ልጃገረዶች ስለ ሮቦቲክስ ኮዲንግ እና አቬዬሽን የሚማሩበት የበረራ ካምፕ ታዘጋጃለች። በዚህም እያንዳንዳቸው ልጃገረዶች በዓመቱ ውሰጥ የሆነ ጊዜ ነጻ የበረራ ትምህርት ያገኛሉ።

የአብራሪነት የደንብ ልብሷን ለብሳ የአብራሪነት ተራውን የሚረከቡትን ታዳጊ ልጃገረዶች እየተመለከተች "ልጃገረዶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ። የግድ አብራሪ ለመሆን እንዲመርጡ አይደለም፤ ነገር ግን በራሳቸው የሚተማመኑ ለማህበረሰቡ እና ለምጣኔ ሀብታችን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ብሎም ለህብረተሰባችን መልሰው የሚሰጡ በራሳቸው የሚተማመኑ ወጣት ሴቶች እንዲሆኑ ነው" ትላለች።

ለበረራ ያላት ፍቅር ወደ ሌሎች እንዲጋባ ማድረግ ትችላለች። ያም ነው የደቡብ አፍሪካ የሴት አቪዬሽን ባለሙያዎች እና የአፍሪካ የወደፊት የሳይንስ መሪዎችን የማፍራት ህልሟን ለማሳካት ጉልበት የሆናት።

በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ቆማ እያለ ሌሎች አብራሪዎች ይጠሯታል፣ እጃቸውን ያውለበልቡላታል፣ ይቀላለዷታል እንዲሁም በረራን የተመለከቱ የተለያዩ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክር ይጠይቋታል።

ጥያቄያቸውን በፈገግታ ተሞልታ እየመለሰች ለሳምንት የሚዘልቀውን እና 100 ለሚሆኑ ከ14 እስከ 18 ዓመት እድሜ ላላቸው ከደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና ለመጡ ልጃገረዶች በማጋሊየስበርግ ተራሮች ውስጥ ካምፕ ታዘጋጃለች።

ይሁንና አንድ ወላጅ ብቻ ባለበት ቤት ከስድስት እህት እና ወንድሞች ጋር በሊምፖፖ ያደገችው ሬፊልዌ 17 ዓመት እስኪሞላት ድረስ አውሮፕላን አጠገብ እንኳን ደርሳ አታውቅም ነበር።

ከጆሃንስበርግ ወደ ኬፕታውን እስክትበር እና አውሮፕላኑ በሴት እየበረረ መሆኑን እስካወቀችበት ጊዜ ድረስ በዩንቨርስቲ ቆይታዋ የነበራት እቅድ ሀኪም መሆን ነበር።

የደቡብ አፈሪካ አየር መንገድ የበረራ ቡድን አባል ሆና መስራት እስክትጀምር ድረስም ህልሟ ባለበት ተገትቶ ነበር። የግል የበረራ ትምህርት መከታተልም ጀምራ ነበር። ወዲያው ግን አማራጭ የገንዘብ ማግኛ መንገድ እንደሚያስፈልጋት ተገነዘበች።

"በደቡብ አፍሪካ ይመለከተዋል ብዬ ለማስበው ኩባንያ ሁሉ ወደ 200 ያህል ደብዳቤዎች ጻፍኩ" ትላለች። በመጨረሻም ሦስቱ መልስ የሰጧት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ለሄሊኮፕተር አብራሪነት ስልጠና ገንዘብ እንደሚከፍልላት እና የንግድ አየር መንገድ አብራሪነት ፈቃድ ለማግኘት ያላትን አቅድ እንደሚደግፉላት የገለጸው የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አገልግሎት ይገኝበታል።

ሬፊልዌ አሁን ፖሊስን ለቃ ጊዜዋን በአሰልጣኝነት እያሳለፈች ሲሆን፤ ትኩረቷንም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ሴቶች ፍላጎት እንዲያድርባቸው መስራት ላይ አድርጋለች።

ከጆሃንስበርግ የሁለት ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ በሚገኘው አቧራማ እና ደረቅ ተራሮች ውስጥ በሬልፊዌ አራተኛው እና ከእስከዛሬው ሁሉ ትልቁ በሆነው የበረራ ካምፕ ለመሳተፍ ሴቶች በቦታው መድረስ ጀምረዋል።

በሙያቸው ስልጡን ናቸው። ሁሉም በሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ውጤት ያገኙ ናቸው። ይሁን እንጂ ተመሳሳይነታቸው የሚያበቃው እዚህ ላይ ነው።

በቀላሉ ከተለያየ ቤተሰብ እና የኋላ ታሪክ የመጡ ስለሆኑ ከከተሞች የመጡ ልጃገረዶች ሲኖሩ፤ ከግል ትምህርት ቤት የመጡ ልጃገረዶች ከዚህ በፊት ምንም አይነት ጥቁር ወይም ነጭ ጓደኛ ያለነበራቸው አሉ።

የካምፕ ቆይታቸው በበረራ ልምምዶች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ከባዶ ተነስቶ በመስራት እንዲሁም ለአነቃቂ ተናጋሪ እንግዶች ምርጥ ምርጥ ጥያቄዎችን በማቅረብ የተሞሉ ናቸው።

በጁሃንስበርግ ዩንቨርስቲ የሳይንስ ዲን ፕሮፌሰር ሜየር እንደሚሉት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ላይ በመላው አፍሪካ በተለይም ልጃገረዶች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፈሰስ ወሳኝ ነው።

"ወጣት ሴቶችን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲያጠኑ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ እንዲቆዩ ማበረታታት ጠቃሚ ነው። በቂ ወጣት ሴቶች እና ልጃገረዶች በሳይንስ ስኬታማ ሲሆኑ እያየን አይደለም ይህ መቀየር አለበት" ትላለች።

"በተለይ ጥቁር ሴቶች ወደ ዳር ተገፍተዋል። እናም እኛ በዘርፉ ያለን ትንሽ ቁጥር ያለን በመሆኑ ሌሎች እንዲያመለክቱ ማበረታታት እና ስኬታማነታቸውን ለማረጋገጥም ማገዝ አለብን" ትላለች።

የቦትስዋና የመጀመሪያዋ ሴት አብራሪ እና በቦትስዋና አየር መንገድ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ሲቪል አቭዬሽን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው ካፒቴን ሳክሂሌ ንዮኒ ሬይሊንግም ሀሳቡን ይጋራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት በተለምዶ አቭዬሽን ሴቶች የማይሰሙበት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነበር። ልጃገረዶችም ከፊታቸው ስላላው አስቸጋሪ የሥራ ዘርፍ በካምፕ ቆይታቸው የሚያስፈልገውን በመገንዘብ መዘጋጀታቸው አስፈላጊ ነው ሲሉ ያክላሉ።

ዝግጅት

በኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ዊሜን ኤርላይን ፓይለትስ የተጠናከረ መረጃ እንደሚጠቁመው በዓለም ላይ ካሉ አብራሪዎች መካከል ሴቶች 5 በመቶው ብቻ ናቸው።

እናም ምንም እንኳ ሬፊልዌ ለእነዚህ ልጃገረዶች መነቃቂያ ብትሆንም ከስኬቷ ጀርባ የገዛ እናቷን ታስቀምጣለች።

የሆነው ሆኖ ምን ጽናቱን ከየት አገኘችው?

"ሴቶች የዓለማችንን የሕዝብ ብዛት 50 በመቶው ይሸፍናሉ። ሴቶችን ለእነዚያ ሥራዎች ካላዘጋጃችሁ እንጠፋለን።"

በአቪዬሽን እና ህዋ ብቻ ሳይሆን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና ሒሳብ ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ይህ ልጃገረዶችን "ለወደፊቱ ሥራቸው ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋልና። ምንአልባትም ወደማህበረሰባቸው ሊመለሱ ወይም የድህነት እሽክርክሪቱን ሰብረው እንዲወጡ ሊያግዟቸው ይችላሉ።"

"በጊዜ ሂደትም ያለመመጣጠኑ ክፍተት ምንአልባትም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መጥበብ ሊጀመር ይችላል።"

"ለዚህ ነው የምንሰራውን የምንሰራው።"

ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ታሪክ የተዘጋጀው ከቢል እና ሊንዳ ጌትስ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው

#bbcinnovators