ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍሪካዊው ተማሪ የምግብ ብክነትን ለመፍታት ጥረት ላይ ነው
የ23 ዓመት የምህንድስና ተማሪ የምግብ ብክነት ችግርን ሊፈታ የሚችል የፈጠራ ውጤት እውን ሊያደርግ ይችላል?
ላውረንስ ኦኬታዮት ዩጋንዳን በመኪና እየዞረ ነው።
ለአፍሪካ የምግብ ብክነት ቀውስ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብሎ የፈጠረውን መሳሪያ በተመለከተ ወሬውን እያደረሰ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በአህጉሪቱ በየዓመቱ የሚጣለው ምግብ እስከ 300 ሚሊዮን ሰዎችን ሊመግብ ይችላል። በኡጋንዳ ብቻ እስከ 40 በመቶው አትክልትና ፍራፍሬ መጨረሻው መደፋት ነው።
ነገር ግን የ23 ዓመቱ የምህንድስና ተማሪ ላውረንስ የእርሱ የፈጠራ ውጤት የሆነው 'ስፓርኪ ድራየር' የተባለው ማሽን ሁሉንም ነገር እንደሚቀይር ተስፋ ሰንቋል።
መሳሪያው ከአትክልት ቦታ በሚወጣ ቆሻሻ የሚሰራ ማድረቂያ ሲሆን አትክልትና ፍራፍሬዎችን በፍጥነት ያደርቃል። ምንም የካርቦን ልቀት እንዳይኖር በማድረግ ከቀናት አልፎ ለወራት እንዲቆዩ ያስችላል።
ትንሽ ማቀዝቀዣ የሚመስልና ኡጋንዳን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት ውሱን ሰዎች ብቻ በሚያገኙት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይሆን ከቆሻሻ በሚገኝ የኃይል አቅርቦትን የሚጠቀም ነው።
የበሰበሰ ምግብ
"በገበያዎች ውስጥ የሚሸጡት አብዛኛዎቹ ምግቦች ከጥቅም ውጪ የሚሆኑት አርሶ አደሮቹ በተገቢው ሁኔታ ማከማችት ስለማይችሉ ነው። እናም በሚቀጥለው ቀን ለመሸጥ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ትኩስ ፍራፍሬ እና አትክልት መውሰድ አለባቸው።"
"በበጋ ወቅት እዚህ የሚበቅለው ጥቂት ስለሆነ ሰዎች ይራባሉ" ይላል ላውረንስ በኪትጉም የሰሜናዊ ክፍል ዋና ከተማ በሚገኝ እና በሞቀ ገበያ መሃል እየተጓዘ ትናንሽ ሱቆችንና የበሰበሰ ምግብ ቁልልን እያለፈ።
የእያንዳንዱ ስፓርኪ ድራየር የመነሻ ዋጋው 80 ዶላር ወይም 2200 ብር ገደማ ነው። እያንዳንዱ ማሽን 10 ኪሎ ግራም ማንጎን በሁለት ሰዓታት ውስጥ ያደርቃል።
ማሽኑ በጋዝ የሚነድ እሳት የሚገጠምበት ትንሽ ክፍል ያለው ሲሆን ቁርጥራጮች የተከማቹበትንና ከላይ ያለውን የማድረቂያ ክፍል ያሞቃል፡፡ በተጨማሪም በማድረቁ ሂደት ወቅት ጎጂ አየር እንዳይወጣ የሚከላከል አቀጣጣይ መቀየርያ አለው፡፡
የስፓርኪ ድራየር አማራጮች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ማድረቂያዎች ናቸው። ነገር ግን በጣም ውድ ናቸው። በፀሐይ ኃይል ወይም በፀሐይ ሙቀት በመጠቀም የሚያደርቁ ባህላዊ የማድረቂያ ዘዴዎች ደግሞ በዝናብ ወቅት ካለመስራታቸውም ባሻገር በጣም ዘገምተኛ ናቸው።
ይሄን ያህል አቅም ቢኖረውም ላውረንስ እስካሁን የሸጠው ማስን ብዛት በጣም ጥቂት ነው፤ ሰባት ብቻ። ታዲያ የእርሱ የፈጠራ ውጤት በእርግጥ ይሰራል?
ከኪቱጉም የሦስት ሰዓት መንገድ ርቆ የሚኖረው የላውረንስ አጎት ጆይ ኦኬታዮት ማድረቂያውን ከሚጠቀሙት የመጀመሪያዎቹ አርሶ አደሮች አንዱ ነው።
ላውረንስ ሀሳቡን ለማመንጨት የተነሳሳው አጎቱ የግብርና ሥራን ለመተው እንዳሰበ ከነገረው በኋላ ነው።
"ከምናመርተው አብዛኘውን እንጥለው ነበር፤ አሁን ዝናብ ሲጥል እንኳን ማንጎ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ማድረቅ እንችላለን። ስለዚህ ከአሁን በኋላ ምንም የምናባክነው ነገር አይኖርም"
"በበጋ ወቅት የደረቁ ምግቦችን በተመረቱበት ወቅት ከሚሸጡበት ዋጋ በአራት እጥፍ እንሸጣለን" ይላል ጆይ ለተጨማሪ ገቢው ምስጋና ይግባው እና በእርሻው መሃል የገነባውን ህንጻ እየጠቆመ።
ባለስልጣናት ምግብ ብክነት ችግር እንዳለ ቢያምኑም መፍትሄ ማፈላለግ ግን ተስኗቸዋል።
"በኡጋንዳ ያሉን ሁለት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ብቻ ናቸው" ይላል የግብርና ሚኒስቴር ሠራተኛው ጀምስ ቱምዋይን። "መንግሥት በዚህ የንግድ ዘርፍ ላይ አይሰማራም፤ የግል ድርጅቶች ደግሞ እዚህ ያለውን እምቅ የገበያ አቅም አልተረዱትም።"
በተለያዩ አካባቢዎች ለተለዩ ምርቶች የምግብ ማቀነባበሪያ ማዕከላት ለመገንባት እቅድ አላቸው። ነገር ግን ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነው።
ወደ ኪትጉም ስንመለስ ላውረንስ ነገን ተስፋ አድርጓል። የፈጠራ ሥራውን በማስፋፋት ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ማዳረስ ይፈልጋል።