ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፉት ቀናት በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የተላከ እርዳታ የለም አለ
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፉት ቀናት በየብስ ወደ ትግራይ የተላከ የሰብዓዊ እርዳታ የለም አለ።
ድርጅቱ ይህን ያለው ከቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነዳጅ እና ምግብ ነክ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከአፋር መዲና ሰመራ ወደ መቀለ ከተማ እየተጓዙ ነው ካለ በኋላ ነው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ እንዳስታውቀው፤ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ማለትም መጋቢት 10 እና 11 2014 ዓ.ም. መዳረሻቸውን አፋር ክልል ያደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሰመራ መነሳታቸውን ገልጿል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ በኢሜይል በሰጡት ምላሽ፤ "መዳረሻቸውን ትግራይ ሳይሆን በአፋር ላሉ ማኅብረሰቦች ነበር" ብለዋል።
ይሁን እንጂ ተሸከርካሪዎቹ የታሰበላቸው ስፍራ ሳይደርሱ አፋር ውስጥ እክል እንደገጠማቸውና ወደተነሱበት ስፍራ መድረስ ባለመቻላቸው ከእነጭነታቸው "በሰላም ወደ ሰመራ ተመልሰዋል" ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርብ መጋቢት 09/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የእርዳታ ምግብ የጫኑ 20 እንዲሁም ነዳጅ የጫኑ 3 ተሸከርካሪዎች ሐሙስ መጋቢት 08/2014 ዓ.ም. ከአፋር ሰመራ ወደ መቀለ እየተጓዙ ነው ብሎ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ለማድረስ ገንቢ ሚና እየተጫወት እንደሆነ ገልጾ፤ የትግራይ ኃይሎች ግን በአፋር ክልል ላይ በከፈቱት ጥቃት የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ የሆነው የአብአላ መስመር በመዘጋቱ የእርዳታ አቅርቦት ሥራው ተስተጓጉሏል ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከመጋቢት 7 ጀምሮ 17 ሰብዓዊ ድርጅቶች መድኃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዲያጓጉዙ ፍቃድ አግኝተዋል ብሏል።
ይህ በእንዲ እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ረቡዕ መጋቢት 07/2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ የተላከ የምግብ እርዳታ የለም ያሉ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 83 በመቶ የሚሆነው የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ድርጅት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ ያለ የሰብዓዊ እርዳታ አለመኖሩን ገልጾ፣ በቅርቡ ግን የፌደራል መንግሥቱ እና የአፋር ክልል ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ መፍቀዳቸው የሚበረታታ ነው ብሏል።
ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የምግብ እርዳታው እንዲደርሳቸው ከፌደራል እና ከክልል ባለሥልጣናት ጋር እንሰራለን ብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሚመሩት ድርጅት መርኅ በተቃራኒ ወገንተኝነትን እያንጸባረቁ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲከሳቸው መቆየቱ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ወራት በፊት እንዳለው በትግራይ ክልል ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር።