ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴቶች ቤት ውስጥ ለሚሠሩት የላባችን ዋጋ ይከፈለን ብለው ቢጠይቁ ስንት ያወጣል?
ልጅን መንከባከብ፣ ምግብ ማብሰል፣ ንጽሕና መጠበቅ፣ ውሃ መቅዳት፣ የማገዶ እንጨት መልቀም፣ የታመመን መርዳት በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሴቶች የሚከውኗቸው ከባድ ኃላፊነቶች ናቸው።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ያሉ ድርጅቶች እነዚህን ተግባራት፣ የማይከፈልበት የእንክብካቤ ሥራዎች ሲሉ ይጠሯቸዋል።
ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) ሴቶች በእነዚህ የሥራ መስኮች ላይ ከወንዶች ከሁለት እጥፍ በላይ የላቀ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ ይላል።
በቀን በአማካይ አምስት ሰዓትም ለዚህ ሥራ ይሰጣሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ይህ ሥራ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ቢቆጠር ኖሮ፣ የንግድ፣ የትራንስፖርት እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች አንድ ላይ ተደምረው ሊያስገኙ የሚችሉትን ገቢ ይበልጣል ይላል።
የኢትዮጵያ ሴቶችስ በዚህ በማይከፈልበት የእንክብካቤ ሥራ ላይ በቀን ስንት ሰዓት ያሳልፋሉ?
ትነበብ ብርሃነ፣ በዚህ ዙሪያ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን የሚሰራው አክሽን ኤይድ ዳይሬክተር ናቸው።
"አንዲት የኢትዮጵያ ሴት በቀን 13 ሰዓት ለዚህ ሥራ ብቻ ጊዜዋን ትሰዋለች" ይላሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሴቶች የሚሰራው ይህ የእንክብካቤ ሥራ በገንዘብ ቢሰላ "እስከ 11 ትሪሊዮን ያወጣል" ይላሉ።
በኢትዮጵያ ጥልቅ ጥናት ባይካሄድም፣ ተቋማቸው ማኀበረሰብ ውስጥ መለስተኛ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ገልፀው፣ አንዲት ሴት በቀን በቀን የምትሰራው የእንክብካቤ ሥራ በወር ቢተመን እስከ 90 ሺህ ብር ሊያወጣ ይችላል ይላሉ።
በተጨማሪም ይህንን በማድረጋቸው እናቶች እና ሴቶች መሠረታዊ መብቶቻቸውን ከመጠቀም ይገደባሉ።
አስረጅ ሲጠቅሱም ትምህርት ቤት ከመሄድ ይስተጓጎላሉ፤ ጤናቸው ላይ ጉዳት ሊከተል ይችላል፤ የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ሊያጡ እንዲሁም ደግሞ በራሳቸው እድገት ላይ ሊያጠፉ የሚችሉትን ጊዜ ይወስድባቸዋል ሲሉ ይዘረዝራሉ።
እንደዚህ የሚለፋበት ጊዜ ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ እውቅና ካለማግኘቱም በላይ እንደ ሥራ ራሱ አይታይም ይላሉ ትነበብ ብርሃነ።
ዳይሬክተሯ አክለውም ይህ እንደ ሥራ አለመቆጠሩ አንዱ የችግሩ ምንጭ መሆኑን በመጥቀስ ምክንያቱን ሲያብራሩ፣ አንዲት የቤት እመቤት ሥራሽ ምንድን ነው ተብላ ብትጠየቅ እርሷ ራሱ "ሥራ የለኝም" ብላ ነው የምትመልሰው ይላሉ።
ከእነርሱ ባሻገርም ባሎችን ጨምሮ ሌላው የማኅበረሰብ አካልም፣ አንዲትን የቤት እመቤት ሥራ እንደሌላት ነው የሚቆጥሩት።
አይኤልኦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ የማይከፈልበት የእንክብካቤ ሥራ በአማካኝ 75 በመቶ በሴቶች ይሰራል ይላል።
ይህም በሴቶች እና በወንዶች መካከል እኩል የሥራ ድርሻ ክፍፍል እንደሌለ እና ሴቶች ከወንዶች አራት እጥፍ በበለጠ እንደሚሰሩ ያሳያል።
70 በመቶ የሚሆኑት በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ የዓለማችን ሴቶች በዝቅተኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሚገኙ ናቸው ይላሉ የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተሯ ትነበብ።
የሴቶች መብት ተከራካሪዎች፣ በመርኅ ደረጃ ይህ ሥራ በገንዘብ ተሰልቶ ለሴቶቹ ገቢ ሊያስገኝ ይገባ ነበር ይላሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በሚያስቀምጡት ስሌትም እንደ አርጀንቲና ባሉት አገራት ውስጥ ይህ ሥራ ለአገሪቷ ምጣኔ ሀብት ማለትም በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ላይ (ጂዲፒ) 7 በመቶ ያህል ያበረክታል።
እንደ ታንዛኒያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ ደግሞ የዚህ የሥራ ዘርፍ የኢኮኖሚ ድርሻ እስከ 63 በመቶ ሊደርስ ይችላል ይላሉ።
በተለይም የገጠር ሴቶች በዚህ ስራ ላይ ረዥም ሰዓት የሚያሳልፉ ሲሆን፣ ተቀጥረው የወር ደመወዝ የሚያገኙ የከተማ ሴቶች ሳይቀሩ በዚህ ስራ ላይ ይሰማራሉ።
እናቶቻችንን እና እህቶቻችንን ደመወዝ እንክፈላቸው ይሆን?
የአክሽን ኤይድ ዳይሬክተር የሆኑት ትነበብ ለዚህ ሥራ በመጀመሪያ እውቅና መስጠት እንደሚገባ ይናገራሉ።
ይህም የሚሆነው ከሴቶች ጀምሮ ቤተሰብ እና ማኅበረሰቡ ይህንን የእንክብካቤ ሥራ እንደ ሥራ ማየት ሲጀምር ነው ይላሉ።
"አንዲት ሴት ቤት ዋለችም፣ ከመሥሪያ ቤት ሠራችም፣ እርሻ ላይም ብትውል ሥራ አላት ነው የምንለው" ይላሉ ዳይሬክተሯ።
እንደውም ይላሉ ዳይሬክተሯ "አንድ አባወራ ደመወዝ የሚያገኝበትን ሥራ ጨርሶ ቤቱ ሲገባ፣ ሊያርፍ ይችላል። አንዲት ሴት ግን ከመሥሪያ ቤቷ ተመልሳ እስከ ለሊት የሚዘልቅ ተጨማሪ ሥራ ይጠብቃታል። እናም ይህ ሊታወቅለት ይገባል" ይላሉ።
እውቅና ከሰጠን በኋላ የሚቀጥለው ተግባር ሥራውን በሴቶች እና በወንዶች መካከል እኩል እንዲከፋፈል ማድረግ ነው።
"አባቶች፣ ወንድሞች እና አባወራዎች በዚህ ሥራ ላይ ከተሰማሩ፣ ሥራውን ከማቅለል በላይም ሴቶች በራሳቸው እድገት ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳል፤ ቤተሰቡንም በመልካም ሁኔታ እየገባ ይሄዳል" ይላሉ።
ትነበብ እንደሚሉት ለምሳሌ "ምግብ ማብሰል፣ ወንድ ሴት ሳይል ሁሉም ሰው በየሕይወቱ ሊማረው የሚገባ ክህሎት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን ለኢኮኖሚው ዘርፍ ምን ያህል እንደሚያበረክት በገንዘብ ተሰልቶ ሊታወቅ ይገባል። እንዲሁም ለምጣኔ ሀብት ያለውን አስተዋጽኦ ማስላት ይኖርብናል" ይላሉ።
በዚህም ለሴቶች ድጋፍ ለማድረግ እና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ ይቻላል ሲሉ ያብራራሉ።
ይህንን የማይከፈልበት የእንክብካቤ ሥራ እውቅና ከሰጠነው በኋላ በመንግሥት መዋቅር እንዲሁም ፖሊሲ ውስጥ እንደ አንድ የአገልግሎት ዘርፍ እንዲካተት በማድረግ ገቢ ማስገኘት መጀመር አለበት ይላሉ የሴቶች መብት ተከራካሪዎች።