ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑቲን ለሩሲያ መዝመት የሚፈልጉ የውጭ አገር ዜጎች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቀረቡ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ለሩሲያ ለመዝመት ጥያቄ ያቀረቡ የሌላ አገር ዜጎች ተመዝግበው ፍላጎታቸውን እንዲፈጽሙ ጥሪ አቀረቡ።
በሩሲያ የደኅንነት ጉባኤ ስብሰባ ላይ ፑቲን እንዳሉት ምንም እንኳ የውጭ ዜጎች ቢሆኑም በሩሲያ ከሚደገፉ ኃይሎች ጎን ለመሰለፍ የፈቀዱ ሁሉ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ያሻል ብለዋል።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እንደተናገሩት በተለይ ከመካለኛው ምሥራቅ አካባቢ ብቻ 16ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ለሩሲያ ወዶ ዘማችነት ለመግባት ፍላጎት አሳይተዋል።
መዋጋት የሚፈልጉትም ሩሲያ ለምትደግፋቸው የዩክሬን ተገንጣይ ኃይሎች እንደሆነ ተመላክቷል።
አሜሪካ እንደምትለው ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሩሲያ የከተማ ሽምቅ ውጊያ የካበተ ልምድ ያላቸው ሶሪያዊያን ይገኙበታል።
ሞስኮ የባሻር አል አሳድ ቀኝ እጅና ደጋፊ ስትሆን በሶሪያው የእርስ በእርስ ጦርነት ጊዜ አሳድን ከሥልጣን ከመወገድና ከሞት የታደገች አገር ናት።
ፑቲን እነዚህ ሶሪያዊያን እንደሆኑ የሚገመቱ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎች ለሩሲያ ወደው ለመዝመት ጥያቄ ያቀረቡ በሙሉ በዶንባስ ከሩሲያ አጋሮች ጋር ተሰልፈው መዋጋት እንዲችሉ ሁኔታዎች በፍጥነት እንዲመቻቹ አዘዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በዚህ የደኅንነት ስብሰባ ላይ ከዩክሬን የተማረኩ የሚሳኤል መቃወሚያዎች በዶንባስ አውራጃ ራስ ገዝ ነን ለሚሉት ሉሃንስ እና ዶኔስክ ተዋጊዎች እንዲሰጡ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ፑቲን በበኩላቸው በዚህ ጉዳይ ላይም ቀጭን ትዕዛዝ ለመከላከያ ሚኒስትራቸው አስተላልፈዋል።
"እንግዲያውስ እንዳልከው አድርግ" ነበር ያሉት ፑቲን ለመከላከያ ሚኒስትሩ፤ በዚሁ የደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ።
ይህን ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ከሶሪያ የሚነሱ ወንበዴዎች ሕዝባችንን ሊጨርሱ እየመጡ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በእርግጥ የውጭ ዜጎች የሆኑ ወዶ ዘማቾች ወደ ሩሲያ ብቻ ሳይሆን ወደ ዩክሬንም እያመሩ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ዜሌንስኪም ቢሆኑ ይህን አምነዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 16ሺህ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሌላ አገር ዜጎችን ጨምሮ ለዩክሬን ለመዝመት ፍላጎት አሳይተዋል።
ቻርለስ ሊስተር የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለቢቢሲ አስተያየት ሲሰጡ፣ "የሶሪያ ዘማቾች ለፑቲን ምን ሊፈይዱ እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም" ይላሉ።
"አሳድ ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን የሚልኩ ከሆነ ወደዚያ የሚዘምቱት ሶሪዊያን ጥይት ማብረጃ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፤ ምክንያቱም መልከአ ምድሩ በፍጹም የተለየ ስለሆነ" ይላሉ እኒሁ ተንታኝ።
ዎልስትሪት ጆርናል ከአሜሪካ ደኅንነት ምንጮቼ አገኘሁ ብሎ በጻፈው ዘገባ ሩሲያ ከሶሪያ ወታደሮችን እየመለመለች የምትገኘው ዋና ከተማ ኪዬቭን ለመቆጣጠርና የከተማ ሽምቅ ውጊያ ላይ ሶሪያዊያን ጎበዞች ናቸው ከሚል እሳቤ ነው።
በተመሳሳይ የአሜሪካ የደኅንነትና ጥበቃ የግል ኩባንያዎች ጠቀም ያለ ዶላር በማውጣት የውጭ ዜጋ ወታደሮችን ለዩክሬን ዘብ እንዲቆሙ፣ ብሎም እንዲዋደቁ እየመለመሉ እንደሆነ ዘገባዎች ወጥተዋል።
የደኅንነትና ጥበቃ ኩባንያዎቹ ግን እኛ እየመለመልን ያለነው የጦር ተዋጊዎችን ሳይሆን ሰላማዊ ዜጎችን ከዩክሬን የሚያስወጡ ልዩ ኃይሎችን ነው ሲሉ ያስተባብላሉ።