ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ በምትልካቸው ምርቶች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ሞስኮ በምዕራባውያን አገራት ለተጣለባት ማዕቀብ አጸፋ ከ200 በላይ የተለያዩ አይነት ምርቶች ከሩሲያ ወደ ውጭ እንዳይላኩ እገዳ ጣለች።
በዚህ የሩሲያ የማዕቀብ እርምጃ የቴሌኮም፣ የህክምና፣ የግብርና፣ የኤሌክትሪክ እና የቴክኖሎጆ መሳሪያዎች ማዕቀብ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በተጨማሪም "ሩሲያን የሚጎዳ እርምጃ የወሰዱ" ባለቻቸው አገራት ላይ የእንጨት ምርቶች ሽያጭን አግዳለች።
ይህ የሩሲያ እርምጃ የአውሮፓ ሕብረትን እና አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች 48 አገራትን የሚመለከት ነው።
የሩሲያ የማዕቀብ ውሳኔ ከአገሪቱ የሚላኩ ምርቶች ላይ አስካለንበት የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ ድረስ እገዳ እንዲጣልባቸው አድርጓል።
በሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኻይል ሚሹስቲን በተፈረመው በዚህ ትዕዛዝ ላይ እንደተጠቀሰው ከሩሲያ ወደ ውጭ አገራት የሚላኩ ምርቶችን ማቀብ "በሩሲያ ገበያ ውስጥ መረጋጋት ለመፍጠር አስፈላጊ ነው" ተብሏል።
ይህ የሩሲያ የአጸፋ እርምጃ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ምዕራባውያን በሩሲያ የገንዘብ እና የኃይል አቅርቦት ላይ ከባድ የሚባሉ ተከታታይ ማዕቀቦችን በመጣላቸው የመጣ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ሀብት ካላቸው ሩሲያውያን ከበርቴዎች መካከል ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ቅርበት አላቸው በተባሉት ላይም ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱና ጉዞ እንዳያደርጉ ዕቀባ ተጥሎባቸዋል።
ሩሲያ ወደ ውጭ እንዳይላኩ ካገደቻቸው ምርቶቿ መካከል መኪኖች፣ የባቡር ፉርጎዎች፣ የእቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነሮች እና የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እንደሚገኙበት ታውቋል።
በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመልክቱት ዩናይትድ ኪንግደም ከሩሲያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ከሚያደርጉ አገራት መካከል ስትሆን በዚህም በሁለቱ አገራት መካከል በአጠቃላይ 15.9 ቢሊዮን ፓወንድ የሚያወጣ የንግድ ልውውጥ ይካሄዳል።
ሩሲያ ለአውሮፓ አገራት ነዳጅ እና ጋር በማቅረብ ከፍተኛ ድርሻ ያላት ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላ አገራት እነዚህን ምርቶች መግዛታቸውን ለማቆም ውይይት እያደረጉ ነው።
አሜሪካ ከሩሲያ ትገዛ የነበረው የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት እንዲቋረጥ በዚህ ሳምንት ወስናለች።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ሳቢያ ምዕራባውያን በአገሪቱ ላይ ከባድ ምጣኔ ሀብታዊ እቀባን እየጣሉ ሲሆን፣ ግዙፎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎቻቸውም ሥራቸውን እያቋረጡ ከሩሲያ እየወጡ ነው።
በዚህም ምክንያት ሩሲያ በአጸፋው ለእነዚህ አገራት የምታቀርባቸውን ተለያዩ አይነት ምርቶችን ላለመሸጥ የወሰነችው።