ሮማን አብራሞቪች በዩኬ መንግሥት እቀባ ተጣለባቸው

የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት የሆኑት ሩሲያዊው ባለሀብት ሮማን አብራሞቪች ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ ጋር በተያያዘ በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እቀባ ተጣለባቸው።

በዚህም ሮማን አብራሞቪች የሀብት እገዳ እና የጉዞ ገደብን ጨምሮ ሌሎች እቀባዎች ከሚጣሉባቸው ሰባት ሩሲያውያን ከበርቴዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።

በዚህ የዩናይትድ ኪንግደም የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ የሩሲያው ፕሬዝዳንት የቅርብ ወዳጅ ናቸው የተባሉት ቢሊየነሮቹ ኢጎር ሴቺን እና ኦሌግ ዴሪፓስካ ተካተውበታል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንዳሉት ሩሲያ የፈጸመችውን ወረራ ለደገፉ ሰዎች "የትም ቦታ እንደፈለጉት መሆን አይችሉም" ሲሉ አገራቸው እርማጃ እንደምትወስድ አመልክተዋል።

"ዛሬ የተወሰደው እርምጃ ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን ሕዝብ ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ የሚያሳይ ነው። የሰላማዊ ሰዎችን መገደል፣ ለሆስፒታሎች ውድመት እና በሉአላዊ ወዳጃችን ላይ የተፈጸመን ወረራ በደገፉት ላይ የምንወስደው እርምጃ ምህርት የለውም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን።

ከሳምንታት በፊት "እጅግ ከባድ ውሳኔ በመወሰን" የእግር ኳስ ቡድናቸውን ቼልሲን ለመሸጥ በተገደዱት በሮማን አብራሞቪች ላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እቀባ እንዲጥል ግፊት ሲደረግበት ቆይቷል።

የ55 ዓመቱ ሮማን አብራሞቪች ባይቀበሉትም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት 9.4 ቢሊዮን ፓወንድ የሚደርስ ሀብት ያላቸው አብራሞቪች "በፑቲን የሥልጣን ዘመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱ ጥቂት ከበርቴዎች መካከል አንዱ" እንደሆኑ አመልክቷል።