ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ነዳጇ ላይ ማዕቀብ ከተጣለባት ለአውሮጳ የምታቀርበውን የተፈጥሮ ጋዝ እንደምታቋርጥ ዛተች
አሜሪያ እያውጠነጠነች እንዳለችው በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ውሳኔ ላይ ከደረሰች ሩሲያ በምትኩ ለአውሮጳ የምታቀብለውን የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቷን እንደምታቋርጥ ዛተች፡፡
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒትር አሌክሳንደር ኖቫክ እንዳሉት፣ የሞስኮን ነዳጅ ማቀብ ውጤቱ እጅግ የከፋ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዳፋውም ለዓለም ይተርፋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ ማስጠንቀቂያቸው ሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ከተጣለ ምናልባትም የአንድ ድፍድፍ በርሜል የነዳጅ ዋጋ አስከ 300 ዶላር ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ አሜሪካ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጮችን እያየች እንደሆነ ሲዘገብ ነበር፡፡
ጀርመንና ኔዘርላንድስ ግን በሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ማዕቀብ መጣል እኛኑ መልሶ ይጎዳናልና ይቅርብን እያሉ ነው፡፡
የአውሮጳ ኅብረት የኃይል አቅርቦቱን በአመዛኙ የሚያሟላው ከሩሲያ ነው፡፡
በአማካይ ካየነው የአውሮጳ ኅብረት 40 ከመቶ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቱን እና 30 ከመቶ የነዳጅ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከሩሲያ ነው፡፡
ሩሲያ እንደዛተችው ድንገት አቅርቦቷን ብታቆም ክፍተትን ለመሙላት የአውሮጳ አገራትን ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ሊከታቸው ይችላል፡፡
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኖቫክ በሩሲያ ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳሉት የአውሮጳ ገበያ ሩሲያ አቅርቦት ካቆመች ለከፍተኛ ችግር ይጋለጣል፡፡
‹‹ተተኪ የኃይል አቅርቦት ለማግኘት ዓመታት ሊወስድባቸውም ይችላል፤ ከኛ ይልቅ እነሱ ይጎዳሉ›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ጀርመን ባለፈው ወር የኖርድስትሪም-2 አዲሱን የጋዝ መስመር ለማቆም መወሰኗ በራሱ ዋጋ የሚያስከፍላት ይሆናል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ሩሲያ በዓለም የተፈጥሮ ጋዝ ምርት የሚስተካከላት አንድም አገር የለም፡፡
ድፍድፍ ነዳጅ በማምረትም በዓለም 2ኛዋ አገር ናት፡፡ በነዚህ ምርቶቿ ላይ ዕቀባ ሲደረግ መልሶ የራሷን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳም እሙን ነው፡፡
ዩክሬን ምዕራቡ ዓለም በሩሲያ የኃይል ምርቶች ላይ ሙሉ እቀባ እንዲጥል ትፈልጋለች፡፡ ነገር ግን ምዕራቡ ዓለም እና የተቀረው የዓለም ክፍል በዚህ እቀባ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሊቀጣጠልበት እንደሚችል ስጋት ተደቅኗል፡፡
ይህ በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ዕቀባ ዙርያ ንግግር መጀመሩ በራሱ የዓለም ነዳጅ ዋጋን ረብሾታል፡፡
ትናንት የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋን በ14 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ 139 ዶላር እንዲገባ ምክንያት ሆኗል፡፡
አሜሪካ የአውሮጳ ኅብረት ከጎኗ ባይሰለፍም እንኳ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ዕቀባ ልትጥል እንደምትችል ሮይተርስ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከሩሲያ የምታስገባው የነዳጅ መጠን ከጠቅላላው 3 ከመቶ ብቻ በመሆኑ ብዙም ችግር ላይገጥማት ይችላል፡፡
ለአውሮጳ አገራት ግን ትልቅ ፈተናን ይደቅንባቸዋል፡፡
ሰኞ ዕለት የጀርመኑ መራሒ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ ማዕቀብ ሊጣል ይችላል የሚለውን ሐሳብ ውድቅ አድርገዋል፡፡
‹‹እኛ ሆን ብለን ነው በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ ዕቀባ ያላደረግነው፤ ያን ብናደርግ ክፍተቱን የሚሸፍንልን ሌላ አካል ለማግኘት እንቸገራለን›› ብለዋል፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯት ተከትሎ 1.7 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ማዕከላዊ ዩሮፕ ተሰደዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ጎረቤት ፖላንድ ነው የገቡት፡፡
ሩሲያና ዩክሬን ለ3ኛ ዙር ድርድር የተቀመጡ ሲሆን ንግግራቸው እምብዛምም ፍሬ አላፈራም፡፡
ጦርነቱ በዓለም የነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንዲከሰት አድርጓል፡፡