ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ ውስጥ በማንችስተር 'ደርቢ' ምክንያት አንድ ታዳጊ ተገደለ
ኡጋንዳ ውስጥ የማንችስተር ከተማ ክለቦች እግር ኳስ ጨዋታ ይተላለፍ አይተላለፍ በሚል የተነሳውን ግርግር ለማብረድ የመጣ ፖሊስ አንድ ታዳጊ ገደለ።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በማንችስተር ሲቲና በማንችስተር ዩናይትድ መካከል የነበረውን ፍልሚያ ትምህርት ቤታቸው አላሳይም በማለቱ ወደ ቅጥር ግቢው ድንጋይ ወርውረዋል።
የ19 ዓመቱ ታዳጊ ከግርግሩ ለመሸሽ በሚል አንድ ዛፍ ላይ ሳለ ነበር በጥይት ተመቶ የወደቀው ሲሉ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
1 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ያሉት ትምህርት ቤቱ በግድያው ምክንያት ለሁለት ሳምንት በመዘጋቱ ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል።
የጉሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አዋኒ ጂሚ በሁኔታው እጅግ እንደተበሳጩ ለቢቢሲ ገልጠዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በፖሊስ ጥይት የተገደለው ታዳጊ ከሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋውሮ ከመጣ ስድስት ሳምንት ቢሆነው ነው።
ዳይሬክተሩ ታዳጊውን "ጨዋ፣ ትሁትና ጠንካራ ተማሪ" ሲሉ ገልፀውታል።
አዋኒ ክስተቱን ሲያስረዱ እሑድ ዕለት የነበረው የማንችስተር 'ደርቢ' ከተማሪዎች የጥናት ክፍለ ጊዜ ጋር በመጋጨቱ ነው ጨዋታው እንዳይታይ የተከለከለው።
ዳይሬክተሩ አክለው ትምህርት ቤቱ ለወትሮው ቀደም ብለው የሚጀምሩ ጨዋታዎች በተለይ ደግሞ በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት ከ8-10 ሰዓት ያሉ ጨዋታዎችን ለተማሪዎች ያሳያል።
ይህ የሚሆነው ተማሪዎች ምሽት 1፡30 የጥናት ፕሮግራም ስላላቸው ነው።
ነገር ግን እሑድ ዕለት የማንችስተር ደርቢ ከሚያመልጠን ጥናት ይቅርብን ያሉ ተማሪዎች ግርግር በማስነሳታቸው የትምህርት ቤቱ ጥበቃዎች ሁኔታውን ለማረጋጋት ጣልቃ ይገባሉ።
ሁኔታዎች እየጋለ የመጣው አንድ የአካባቢው ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ከተኮሰ በኋላ ስልክ ደውል ከወታደራዊው ኃይል እርዳታ ከጠየቀ በኋላ ነው።
"የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት እርምጃ ከተገቢው በላይ ነው ብዬ ነው የማስበው" ይላሉ ዳይሬክተሩ።
አዋኒ ጂሚ እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ባሉት 30 ዓመታት እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞት አያውቅም።
የጉሉ ከተማ አስተዳደር ከትምህርት ቤቱ ጋር ከመከረ በኋላ ለሁለት ሳምንት እንዲዘጋና ተማሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ወስኗል።