ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለየት ያሉ መረጃዎች
የሴቶች ቀን በየዓመቱ ማርች 8 ይከበራል፡፡ ለመሆኑ ማን ጀመረው?
አጀማመር
ታሪኩ በአጭሩ ይህ ነበር፡፡
ድሮ በ1908 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 15 ሺህ ሴቶች ወደ አደባባይ ወጡ፡፡ በየት አገር? በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ፡፡
ምን ፈልገው? ጥሩ ደመወዝ፣ ጥሩ የሥራ ቦታ፣ ጥሩ የሥራ ሁኔታ እና የሥራ ሰዓት ማስተካከያ እንዲደረግ፡፡
በዋናነት ደግሞ ሴቶች መምረጥ እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅ አደባባይ ወጡ፡፡ ሴቶች በአሜሪካን አገር መምረጥም ሆነ መመረጥ አይችሉም ነበር፡፡
ከዓመት በኋላ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ዕለቱን ብሔራዊ የሴቶች ቀን ብሎ ጠራው፡፡
ይህ በሆነ በሁለተኛው ዓመት ክላራ ዚክተን የተባለች ሴት በዓሉ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ እንዲከበር ሐሳብ አቀረበች፡፡
ይህ የሆነው ደግሞ በዴንማርክ፣ ኮፐንሐገን በተደረገ ጉባኤ ላይ ነበር፡፡
ከ17 አገራት የተውጣጡ ወደ መቶ ሴቶች ታድመውታል፤ ጉባኤውን፡፡ የክላርን ሐሳብ ተቀበሉት፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ታዲያ ጀርመን፣ ስዊትዘርላንድ ኦስትሪያና ዴንማርክ የምር በዓሉን ማክበር ጀመሩ፡፡
ዘንድሮ ታዲያ ይህ በዓል ለ111ኛ ጊዜ ነው የሚቀከበረው፡፡
ይሁንና በደንበኛው ዓለም አቀፍ ይዘት ኖሮት መከበር የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ1975 ዓ/ም ነበር፡፡ ይህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕለቱን የሴቶች ቀን ብሎ ማወጁን ተከትሎ ነው፡፡
ለምን ማርች 8 ተመረጠ?
ክላራን አስታወሳችኋት? ኮፐንሐገን ላይ ሐሳቡን ያቀረበችው የሴቶች መብት ተቆርቋሪ?
ሐሳቡን ስታቀርብ ግን ቀን አልመረጠችም ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ማርች 8 ተመረጠ?
ነገሩ ዛሬ በዩክሬን ላይ ጦር ከሰበቀችው ሩሲያ ጋር ይያያዛል፡፡
ድሮ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ አካባቢ፣ ልክ በ1917፣ የሩሲያ ሴቶች አመጹ፡፡ "ሰላምና ዳቦ" የሚል መፈክር ይዘው የሞስኮና የፒተስበርግ ከተሞችን አጥለቀለቁ፡፡
ሩሲያን አንቀጠቀጧት፡፡ አመጹ ቶሎ አልበረደም፡፡ ለአራት ቀናት የዘለቀ ነበር፡፡
የሩሲያው ቄሳር አማራጭ አልነበረውም፡፡ ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ፈቀደ፡፡
ይህ ጊዜ ታዲያ በጁሊያን ዘመን አቆጣጠር የካቲት 23 ነበር፡፡
ይህ ዕለት በጎርጎሮሲያዊያኑ ሲመነዘር መቼ ቀን ጋር ይገጥማል?
ማርች 8፡፡
የወንዶች ቀን ለምን አይከበርም?
ብዙ ሰዎች ልብ አይሉትም እንጂ ዓለም አቀፍ የወንዶች ቀን ይከበራል፡፡ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ኅዳር 19 ታስቦ ይውላል፡፡ የሚያሳዝነው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን ዕውቅና አልሰጠውም፡፡
ተመድ ዕውቅና ይንፈገው እንጂ የወንዶች ቀንን ኮስተር ብለው የሚያከብሩ አገራት ጥቂት አይደሉም፡፡
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ከ80 በላይ አገራት ያከብሩታል፡፡
በአመዛኙ ለጾታ እኩልነት አርአያ ለሚሆኑ ወንዶች ዕውቅና በመስጠት ነው የሚከበረው፡፡
ሐምራዊ ቀለም ለምን ተመረጠ?
ሐምራዊ፣ አረንጓዴና ነጭ የሴቶች ቀንን ይወክላሉ፡፡
ሐምራዊ ቀለም ፍትሕንና ክብርን ይወክላል፡፡ አረንጓዴ ደግሞ ልምላሜና ተስፋን ይወክላል፡፡ ነጭ ንጽህናን ይወክላል፡፡ ይህ የቀለም ምርጫ የተደረገው በዩናይድ ኪንግደም በ1908 ላይ ነበር፡፡
በሩሲያ እንዴት ይከበራል?
የሴቶች ቀን በብዙ አገራት በተለያየ መንገድ ይከበራል፡፡ እንደ ሩሲያ ግን በድምቀት የሚከበርበት አገር የለም፡፡
ምናልባት ዘንድሮ ጦርነቱ ካደበበዘው እንጃ እንጂ፣ ሩሲያ ከዕለቱ ሦስት እና አራት ቀናት ቀደም ብላ ነው ለዚህ በዓል ሽር ጉድ የምትለው፡፡ በተለይ የአበባ ገበያው እንደ ጉድ ነው የሚደራው፡፡
በጣሊያንም እንዲሁ ነው፡፡ በብዙ የአውሮፓ አገራት አበባ በዚህ ዕለት ተወዳጅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአበባ ምርቶቿን በስፋት ከምትልክባቸውና ዳጎስ ያለ ገቢ ከምታገኝባቸው ዕለቶች አንዱ ይህ የሴቶች ቀን ነው፤ እንደ ፍቅረኛሞች ቀን ባይሆንም፡፡
በቻይና አከባበሩ ለይት ይላል፡፡ ሴቶች የግማሽ ቀን እረፍት ይሰጣቸዋል፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምን ይዟል?
የተባበሩት መንግሥታት የዘንድሮ የሴቶች ቀን መሪ ቃሉ (Gender equality today for a sustainable tomorrow") "የጾታ እኩልነት ለነገ ዘላቂነት" ይሁን ብሏል፡፡
ዋና ሐሳቡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሴቶች እንዴት ነገን እያበጃጁ ነው በሚለው ሐሳብ ዙርያ ይንሸራሸራል፡፡
ዘንድሮ ምን አዲስ ነገር አለ?
ይህ በዓል ዘንድሮ ሲከበር ታሊባን ሴቶች ትምህርት እምብዛምም አያስፈልጋቸውም ባለበት ዓመት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ታሊባን ይህ ሳያንሰው ሴቶች ወደ ሥራ ገበታ አትምጡ ሲል አውጇል፡፡ የሴቶች ሚኒስቴርን አፍርሷል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የሳራህ አቨራርድ በፖሊስ መገደል አዲስ ክርክርና የሴቶች መብት ጥያቄን እንደ አዲስ ቀስቅሷል፡፡
ሌላው ደግሞ ኮቪድ ነው፡፡ ኮቪድና ሴቶች ቀንን ምን አገናኘው ትሉ ይሆናል፡፡
ዘንድሮ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቤት እንድንቆይ ባደረገን የኮቪድ ተህዋሲ ወረርሽኝ የተነሳ ጭራሽ የማይታመኑ፣ በጣም አስቀያሚ የሴቶች ጥቃት ዜናዎችን የሰማንበት ዓመት ነበር፡፡
አደጉ፣ በለጸጉ፣ አወቁ፣ የሴት መብት ላይ ድርድር አያውቁም በምንላቸው አገራት ጭምር ሴቶች በእጅጉ ጥቃት ተበራክቶባቸው ታይቷል፡፡ በሴቶች ጉዳይ ገና እንደሆንን የታየበት ዓመት ነበር፡፡
ተመድ በ13 አገራት ውስጥ በሠራው አንድ ጥናት ከሁለት ሴቶች አንዷ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶባታል፡፡
የኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደብን ተከትሎ ሺህ እና መቶ ሺህ እናቶች፣ እህቶች፣ ሚስቶች፣ ጓደኞች፣ ልጃገረዶች በአንድም ሆነ በሌላ ሁኔታ የቤት ውስጥ ጥቃት ሲፈጸምባቸው የታየበት አስደንጋጭ ወቅት ነበር፡፡
አሁን 2022 ላይ ነን፡፡ ለሴቶች ምቹ የሆነች ዓለም ገና አልተወለደችም፡፡ ትግሉም ይቀጥላል፡፡