ዋይት ሃውስ ሩሲያ የኬሚካል ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች አለ

ጄን ሳኪ

የፎቶው ባለመብት, Win McNamee

ሩሲያ በዩክሬን የኬሚካል ወይም የባዮሎጂካል መሳሪያ ጥቃት ልትፈጽም ስለምትችል "ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል" ሲል ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

ሩሲያ ስለ አሜሪካ የባዮሎጂካል መሳሪያ ቤተሙከራዎች እና በዩክሬን የኬሚካል ጦር መሳሪያ እያበለጸገች ነው ስትል የምትገልጸው የተሳሳተ ነው ሲሉ የነጩ ቤት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ገልጸዋል ።

የሐሰት መረጃዎቹ ተጨማሪ ምከንያት አልባ ጥቃቶችን ለማስረዳት መሞከሪያ "ግልጽ ዘዴ" ነው ሲሉ ጠርተውታል።

ይህ የተገለጸው ምዕራባውያን ባለስልጣናት ስለ አዲስ ጥቃቶች ተመሳሳይ ስጋቶችን ካጋሩ በኋላ ነው።

ጦርነቱ ሊባባስ ስለሚችልበት አደጋ በተለይም ሩሲያ ያልተለመዱት የጦር መሳሪያዎች የመጠቀም አዝማሚያዋ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

እነዚህ መሳሪያዎች ደግሞ በአብዛኛው የሚያመለክቱት የኬሚካል መሳሪያዎችን ቢሆንም ቃሉ ታክቲካል ሲሆን (አነስተኛ) የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን፣ ባዮሎጂካል መሳሪያዎችን እና አደገኛ ቦምቦችን ያካትታል።

"የምንጨነቅበት በቂ ምክንያት አለን" ብለዋል አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣን።

ምክንያቱ ደግሞ በከፊልም ቢሆን ሩሲያ በተሰማራችባቸው ሌሎች ጦርነቶች መታየታቸው ነው። በተለይም በሶሪያ በአጋሮቿ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ይጠቀሙ ነበር።

ሳኪ "ሩሲያ ምናልባት በዩክሬን የኬሚካል ወይም ባዮሎጂካል መሳሪያዎችን እንድትጠቀም ወይም ስለመሳሪያዎቹ የውሸት ስጋት በመፍጠር ጥቃት ልትፈጽም ስለምትችል ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል። ይህ ግልጽ ዕቅድ ነው" ብለዋል።

ረቡዕ ዕለት የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ቴርሞባሪክ ሮኬቶችን ተጠቅማለች።

እነዚህ ሮኬቶች ከፍተኛ ሙቀት ያለው ፍንዳታ ለመፍጠር ከአካባቢው አየር ኦክስጅን ስለሚሰበስቡ ቫኩም ቦምብ በመባል ጭምር ይታወቃሉ።

ይህም ተመሳሳይ መጠን ካላቸው ፈንጂዎች የበለጠ አውዳሚ ያደርጋቸዋል። ፍንዳታ በደረሰበት አካባቢ ያሉ ሰዎች አስከፊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

ሚኒስቴሩ አክሎም ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት ያላቸው የሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያዎች "ልምድ ያላቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችን" በዩክሬን ለመዋጋት እያሰማሩ ሊሆን እንደሚችል ጽፏል።

የሩስያ ቅጥረኛ ወታደሮች ሶሪያ፣ ሊቢያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ጨምሮ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ፈጽመዋል በሚል ይክሰሳሉ ብሏል።

በኬሚካላዊ መሳሪያ ጥቃት ላይ ያለው ፍራቻ የተፈጠረው ሩሲያውያን እየፈጠሩት ካለው ሃሰተኛ ስጋት ነው ሲሉ ምዕራባውያን ባለስልጣናት ተናግረዋል ።

የሩሲያ ኤምባሲ በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው በአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር የገንዘብ ድጋፍ የባዮሎጂካል የጦር መሳሪያዎች አካላት በዩክሬን ቤተሙከራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ "በቅርብ ጊዜ የተገኙ ሰነዶች" አሉ።

አሜሪካ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ "ሩሲያ ለዓመታት በዩክሬን እና በሌሎች ሃገሮች የሃሰት መረጃ ስርጭት አካል ነው" በማለት ገልጻለች።

ዩክሬናውያን

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images/Getty Images

ባለፉት ጥቂት ቀናት የሩሲያ ባለስልጣናት እና መገናኛ ብዙሃንም በበኩላቸው ዩክሬን የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮችን የሚበትን አደገኛ ቦምብ ለመሥራት ማቀዷን ተናግረዋል።

ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ ትፈልግ ነበር ያሉት ደግሞ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው።

አንዳንዶች ሞስኮ ለምን ዩክሬንን እንደወረረች ለህዝቧ አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ እየሞከረች ነው ብለው ያምናሉ። የምዕራባውያን ባለስልጣናት ግን "የውሸት መረጃዎቹ" ለመሰረት ቢስ ጥቃቶች ሊውሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

ለምሳሌ ሩሲያ ማንኛውንም ያልተለመደ የጦር መሳሪያ ከዩክሬን መጋዘኖች ወይም ወታደሮች እንዳገኘች ወይም መጀመሪያ ዩክሬናዊያን ጥቅም ላይ እንደዋሉት ልትናገር ትችላለች። በዚህም ሞስኮ በቀጣይ ያልተለመዱ የጦር መሳሪያዎች መጠቀሟን ትክክለኛ እንደሆነ ለማረጋገጥ ሊውል ይችላል።

ሶሪያ ውስጥ መሳሪያዎቹን ከመጠቀማቸው በፊት ተመሳሳይ ታሪኮች ከሩሲያ እንደመጡ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

የስለላ መረጃዎች በሚመስል መልኩም "ሌሎች ጠቋሚ ነገሮችም አሉ። ይህ ለእኛ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የሩሲያ አጋር የሆነው የአሳድ መንግስት በሶሪያ የኬሚካል ጦር መሳሪያን በተለያዩ ጊዜያት በሠላማዊ ሰዎች ላይ ተጠቅሟል።

ሩሲያ እአአ በ2018 በሳልስበሪ ሰርጌ ስክሪፓል ላይ እንደተደረገው የግድያ ሙከራ እና በ2020 ደግሞ ሩሲያ ውስጥ በተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ላይ እንደተጠቀመችው ዓይነት የነርቭ ስርዓትን የሚያጠቃ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ትጠቅማለች ተብላ ትከሰሳለች።

የኬሚካል የጦር መሳሪያ ስምምነትን የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፍ ቡድን (ኦፒሲደብሊው) እንደሚለው የኬሚካል መሳሪያን ማለት በመርዛማ ባህሪያቱ ምክንያት ሆን ተብሎ ለሞት ወይም ጉዳት የሚያደርስ መሳሪያ ማለት ነው ሲል ይገልጻል።

እነዚህ መሳሪያዎች በተፈጥሯቸው የማይለዩ እና ከመጠን በላይ የሆነ ጉዳት እና አላስፈላጊ ስቃይ ለመፍጠር የታቀዱ በመሆናቸው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ የተከለከሉ ናቸው።