ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጄነራል አል ቡርሐን 15 ሚኒስትሮች ያሉት ካቢኔ አቋቋሙ
የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን 15 ሚኒስትሮች ያሉት ካቢኔ አቋቋሙ።
ይህ ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ሥልጣን ጨብጠው የቀድሞውን ካቢኔ ከበተኑ በኋላ ለመጀመሪያ ያቋቋሙት ካቢኔ ነው።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳን በሽግግር መንግሥት እየተመራች ሳለ ነው ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት።
ጦሩ በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራውን የሲቪሊ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ካስወገደ በኋላ በሱዳን ቁጣ ተቀስቅሶ ቆይቷል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ቢያንስ 70 ሰዎች በደኅንነት ኃይሎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ነገር ግን የአዲሱ ካቢኔ መቋቋም ወታደራዊው መንግሥት ከሥልጣን ይነሳ እያሉ ለሚጠይቁ ሱዳናዊያን ምላሽ የሚሆን አይመስልም።
በርካታ ሱዳናዊያን ዳኞች የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚደረጉ ጭቆናዎች ምርመራ እንዲደረግባቸው ሲጠይቁ ነበር።
ዳኞቹ ወታደራዊው አገዛዝ ያልታጠቁ ሰልፈኞች ላይ ግፋና የመብት ጥሰት ፈፅሟል ሲሉ ይከሳሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ በሲቪሎች የሚመራ መንግሥት እስኪቋቋምና ግጭቶች እስካልቆሙ ድረስ ለሱዳን የምታደርገውን ምጣኔ ሃብታዊ እገዛ እንደምትገታ አስታውቃለች።
ባለፈው ጥቅምት ወር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የተወገዱት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ሥልጣናቸው ከተመለሱ በኋላ በፈቃዳቸው ከመንበራቸው መነሳታቸው ይታወሳል።
በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ከተወገዱ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ወደ ኃላፊነታቸው ተመልሰው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ የሥልጣን መልቀቅ ውሳኔ የሱዳን መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በጦር ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር እንዲገባ አድርጎታል።
በጥቅምት ወር አጋማሽ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሩን አመራሮች ከበተነና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢደነግግም ጦሩ የተቃውሞ ሰልፎችን መቆጣጠር አልተቻለውም።
ለወራት የቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንደሚሉት ዋነኛ ጥያቄያቸው ጦሩ ሥልጣን በሲቨሎች ለሚመራ መንግሥት አስረክቦ ከመሪነት መንበሩ ገለል እንዲል ነው።
ከአልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ሥልጣን በአገሪቱ ጦር ሠራዊትና በሲቪል ፖለቲከኞች መካከል ተከፋፍሎ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምም ሁለቱ ወገኖች ሳይስማሙ ተቃውሞው ቀጥሎ ቆይቷል።
ሕዝባዊውን ለውጥ የመሩት ኃይሎች ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን ውጪ ሆኖ ሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋምና ሱዳን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖራት ግፊትና የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።