ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመንግሥታቱ ድርጅት በጦርነት ምክንያት የእርዳታ አቅርቦት መስተጓጎሉን ገለጸ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ መስመር ላይ ጦርነት በመኖሩ ወደ ትግራይ በሚያደርሰው የረድኤት አቅርቦት ሥራ መስተጓጎል እንደገጠመው ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች በጦርነት ምክንያት እንደ ምግብ እና መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ለመቀነስ፣ ለማራዘም እና ለመሰረዝ መገደዱን በመግለጫው አስታውቋል።
የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽ/ቤት (ኦቻ) ወደ መቀለ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ለመቀነስ፣ ለማራዘም እንዲሁም ለመሰረዝ የተገደድኩት የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊ መስመር ላይ ጦርነት በመኖሩ ነው ብሏል።
"ከሰመራ-በአብአላ-መቀለ በሚወስደው መስመር በኩል ወደ ትግራይ የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አብአላ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ማክሰኞ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ ይገኛል" ብሏል ኦቻ ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም ማምሻውን ባወጣው መግለጫ።
ኦቻ ከሐምሌ 26/2013 ዓ.ም. ወዲህ በአብአላ በኩል ለሰብዓዊ እርዳታ ኦፕሬሽን ጥቅም ላይ የሚውል ነዳጅ ወደ ትግራይ አልተላከም ያለ ሲሆን ትግራይ ውስጥ ባለው የነዳጅ እጥረት ምክንያት ድርጅቶች ነዳጅ በክልሉ ማግኘት አልቻሉም ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ከታኅሣሥ 23 አስከ ጥር 04/2014 ዓ.ም. ድረስ 10 ሺህ 500 ሰዎች የምግብ እርዳታ መቀበላቸውን ገልጾ፤ ይህ አሃዝ ከመጋቢት 2013 ወዲህ የሰብዓዊ እርዳታ የተቀበሉ አነስተኛው የተረጂዎች ቁጥር ነው ብሏል።
እንደ ተመድ ከሆነ በየሳምንቱ እርዳታ መቀበል ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከ800 ሺህ በላይ መሆን አለበት።
የመንግሥታቱ ድርጅት በተጨማሪም አጋር ያላቸው የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ያላቸው የምግብ ክምችት 28 ሺህ ሰዎችን ብቻ መርዳት የሚችል ስለመሆኑ ሪፖርት አድርገዋል ብሏል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት የተጀመረው የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ለ145 ሺህ ልጆች መሰጠቱን ገልጾ ይህን ክትባት 800 ሺህ ታዳጊዎች መወሰድ አለባቸው ብሏል።
የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመድኃኒቶችን የሙቀት መጠን በመቆጣጠር ሟጓጓዝ አዳጋች መሆን፣ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ከሌሎች እጅግ ከባድ ፈተናዎች ጋር ተደማምረው የኩፍኝ ክትባት ዘመቻውን አሰቸጋሪ አድርጎታል ይላል ተመድ።
አማራ እና አፋር
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተደራሽ በሆኑት የአማራ እና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች መስፋፋቱን ኦቻ በመግለጫው አውስቷል።
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ እርዳታ መቀሉን ገልጾ፤ ከ40 ሺህ ሰዎች በላይ ደግሞ ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን መቀበላቸውን አስታውቋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደቀደመ መኖሪያቸው መመለሳቸውን ተመድ ገልጿል።
በአፋር ክልል ደግሞ ባለፈው ሳምንት ከ47 ሺህ በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ መቀበላቸውን ኦቻ በመግለጫው አስታውቋል።
በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎችን ለመርዳታ 30 ተንቀሳቃሽ ቡድን አባላት መሰማራታቸውንም ኦቻ ጨምሮ ገልጿል።
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፋቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና የንብረት ውድመት አስከትሏል።
14 ወራትን ያስቆጠረው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ስለመቅጠፉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለማፈናቀሉ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ በተከሰተው ቀውስ ከ9.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሳምንታት በፊት አስታውቋል።
ጦርነቱ ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ተዋጊ ኃይሎች ጦርነቱን በአስቿካይ አቁመው ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ተመድን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።