ዋልያዎቹ ከምድባቸው የማለፍ እድላቸው ምን ያህል ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በካሜሮን እዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እየተሳተፈ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ያደርጋል።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስተናገዱት ዋልያዎቹ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋቸውን ከቡርኪና ፋሶ ጋር ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ያደርጋሉ።

ዋልያዎቹ በመጀመሪያው ጨዋታቸው በኬፕ ቬርድ 1 ለ 0፤ በሁለተኛው ግጥሚያ ደግሞ በአዘጋጇ ካሜሩን 4 ለ 1 መሸነፋቸው ይታወሳል።

ለመሆኑ ዋልያዎቹ ከምድባቸው የማለፈ እድላቸውም ምን ያል ነው?

መልሱ - ጠባብ ነው።

ዋልያዎቹ ሁለት ጊዜ ተሸንፈው 4 የጎል እዳን በመያዝ በምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ቡርኪና ፋሶ በውድድሩ መክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇን 1ለ0 ስትመራ ቆይታ ተከታትሎ በተቆጠሩባት ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶች በካሜሮን 2 ለ 1 ተሸንፋለች።

ቡርኪና ፋሶ በቀጣይ የምትጋጠመው ከኬፕ ቬርድ ነው። ኬፕ ቬርድን 1 ለ 0 በማሸነፍ በምድብ ሀ ኬፕ ቬርድን በጎል ልዩነት በመብለጥ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የምድቡን ሁለቱንም ጨዋታዎች ያሸነፈችው ካሜሮን በአንደኝነት እየመራች ነው።

ዋልያዎቹ ያለባቸውን 4 የግብ እዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ከምድቡ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ቡርኪና ፋሶን 5 ለ 0 እና ከዚያ በላይ በሆነ ውጤት አሸንፈው፤ የኬፕ ቬርድ ቡድን በካሜሮን የማይበገሩ አናብስት መሸነፍን መጠበቅ አለባቸው።

ነገር ግን በእግር ኳስ ሜዳ የሚከሰተውን መተንበይ ባይቻልም ዋልያዎቹ የምድቡ ሁለተኛ በሆነችው ቡርኪና ፋሶ ላይ በርካታ ጎሎችን አስቆጥረው ማሸነፍ የዋዛ አይሆንላቸውም።

በፈረንጆቹ 2013 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ በአንድ ምድብ ተደልድለው እንደነበረ ይታወሳል።

በዚህ ውድድርም ቡርኪና ፋሶ ዋልያዎቹን 4 ለ 0 አሸንፈው እንደነበር ይታወሳል።

ምርጥ ስተኛ?

የአፍሪካ ዋንጫ 24 ብሔራዊ ቡድኖችን እያሳተፈ ይገኛል። ይህ ማለት እያንዳንዳቸው አራት ቡድኖችን ያቀፉ ስድስት ምድቦች አሉት ማለት ነው።

ከእነዚህ መካከል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የሚይዙ ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር በቀጥታ ሲያልፉ፤ አራት ምርጥ ሦስተኛ ቡድኖችም ቀጣዩን የ16ቱን ዙር ይቀላቀላሉ።

ዋልዮቹም ከምድባቸው ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ ለመጨረስ ቡርኪና ፋሶን አሸንፈው የኬፕ ቬርድ በካሜሮን መሸነፍን መጠበቅ አለባቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ዋልያዎቹ ከሌሎች ምድቦች ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ የመጨረስ እድል ያላቸውን አገራት ውጤት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።