በኢንተርኔት መቋረጥ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ ከፍተኛ ገንዘብ አጥታለች - ሪፖርት

የተቆለፈ ኢንተርኔት

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በኢንተርኔት መቋረጥ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ በመቀጠል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዳጣች አንድ ሪፖርት አመለከተ።

ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጦች በአገራት ላይ ያስከተሉትን ኪሳራ በተመለከተ ቶፕ ቴን ቪፒኤን ባወጣው ሪፖርት ላይ በአፍሪካ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።

በመላው ዓለም መንግሥታት በአገራቸው ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በማቋረጣቸው በአጠቃላዩ የምድራችን ምጣኔ ሀብት ላይ የ5.5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራን ማስከተላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በዚህም መሠረት ከሁለት ሳምንታት በፊት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኢንትርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ በመደረጉና የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በመዘጋታቸው ኢትዮጵያ 164.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳጣች ተገልጿል።

የኢንተርኔት መቋረጥ በአፍሪካ

ከአንድ ዓመት በላይ በቀጠለው የትግራይ ጦርነት ምክንያት በክልሉ የኢንተርኔት አገለግሎት መቋረጡን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ባለፈው ግንቦት ወር የተሰጠው ብሔራዊ ፈተና በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሾልኮ ወጥቷል በሚል በመላው አገሪቱ ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም ከአገልግሎት ውጪ እንደነበሩ ጠቅሷል።

እንደ ሪፖርቱ በአንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጪ ሆነው የቆዩት ለ8,760 ሰዓት ሲሆን የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኮች ደግሞ ለ104 ሰዓት ተዘግተው ቆይተው ነበር።

በዚህም ሳቢያ በኢትዮጵያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ሚዲያ መስተጓጎል መቸገራቸውንና 165 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት መድረሱን አመለክቷል።

የኢንተርኔት መቋረጥ የሚያስከትለው ኪሳራ

ዓመታዊው ሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ ያጋጠሙ ዋነኛ የሆኑና ሆን ተብለው የተቋረጡ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመመዝገብ የተነተነ ሲሆን፣ በዚህም የደረሱ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራዎችና አገልግሎት የተነፈጉ ሰዎችን ብዛት አቅርቧል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንተርኔት መቋረጥ ከፍተኛ ኪሳራ የገጠማት አገር ምሥራቅ እስያዊቷ አገር ምያንማር ስትሆን፣ ይህም በአገሪቱ የጦር ጄነራሎች የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ዓመት በምያንማር ኢንተርኔት ለ12,238 ሰዓታት የተቋረጠ ሲሆን ይህም የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራን አስከትሎባታል።

ሁለተኛዋ ደግሞ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ስትሆን ሆን ተብሎ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት 104.4 ሚሊዮን ሕዝብ ከአገለግሎት ውጪ ሆኖ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ አድርጓታል ተብሏል።

እንዲቋረጡ የተደረጉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች

ከኢንተርኔት መቋረጥ በተጨማሪ አገራት የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮችንም ለይተው አገልግሎት እንዳይሰጡ ያደርጋሉ። በዚህም ባለፈው ዓመት ከሁሉም በበለጠ ዕቀባ ተጥሎበት የነበረው ትዊተር ሲሆን፣ በተከታይነት ፌስቡክና ዋትስአፕ በአንዳንድ አገራት ውስጥ አገልግሎታቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በአጠቃላይ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 21 አገራት ውስጥ 50 የሚሆኑ ዋነኛ የሚባሉ የኢንተርኔት መቋረጦች በተለያዩ ምክንያቶች እንዳጋጠሙ ተመዝግቧል።

ይህም በአጠቃላዩ የዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ የ5.45 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራን በማስከተል ከቀደመው ዓመት በ36 በመቶ ከፍ ማለቱን የቶፕ ቴን ቪፒኤን ሪፖርት ዓመልክቷል።

ኢንተርኔት በተቋረጠባቸው አገራት ውስጥ 486.2 ሚሊዮን ሰዎች ከአገልግሎት ውጪ ለመሆን የተገደዱ ሲሆን፣ ኢንተርኔት በመንግሥታት ሲቋረጥ ከተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር እንደሚያያዙም አመልክቷል። በዚህም ሳቢያ በምርጫ፣ በመሰብሰብና በመናገር ነጻነቶች ላይ ጥሰቶች ያጋጥማሉ።

በዘመናዊው ዓለም የኢንተርኔት አገልግሎት ከመሠረታዊ የሰዎች ፍላጎቶች ውስጥ እየታየ ያለ ሲሆን፣ ኢንተርኔት ለበርካታ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች ዋነኛው መሳሪያ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጥ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚያስከትለው ኪሳራ ቀላል የሚባል አይደለም።