የተደራጁ ወንጀለኞችን ትኩረት የሳበው የኬንያ አቮካዶ ምርት

የአቮካዶ ዛፎች

ኬንያ ውስጥ የአቮካዶ አምራቾች የንግድ ስራ የተደራጁ ወንጀለኞችን ትኩረት ስቧል። አንድ የአቮካዶ ዛፍ በዓመት እስከ 600 ዶላር ድረስ ያስገኛል።

የአቮካዶ ፍላጎት በአሜሪካና አውሮፓ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ኬንያ የአቮካዶ ምርቷን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች።

ይህንን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የበላይነት ይታይበት የነበረውን የአቮካዶ ዘርፍ ኬንያ ባለፈው ዓመት በመረከብ በአፍሪካ ትልቅ መጠን ያለው የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ አገራት መላክ ችላለች።

አረንጓዴው ወርቅ የሚል ስያሜ የተሰጠውን ይህንን ዛፍ ከወንጀለኞች ለመከላከል ደግሞ የኬንያ ገበሬዎች ኢመደበኛ የጥበቃ ቡድኖችን እያቋቋሙ ነው።

በኬንያዋ ሙራንጋ ካውንቲ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኘው ትልቅ እርሻ አካባቢ ትንሽ መሸት ሲል ስድስት ወጣቶች የዝናብ መከላከያና ለብሰው፣ ባትሪ ይዘውና የቻሉትን ያክል ታጥቀው ይታያሉ።

ጠባቂዎቹ ወጣቶች ገጀራ፣ ዱላና ማንኛውንም ነገር ይዘው ነው እርሻውን የሚጠብቁት።

እነዚህ ጠባቂዎች የአቮካዶ እርሻውን እንዲጠብቁ በባለቤቶቹ ነው የተቀጠሩት። በዚህ አደገኛ ስራ ሰዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ አንዳንዴም ሕይወታቸው ያልፋል።

ገበሬዎቹ ወደን ሳይሆን ተገደን የገባንበት ሁኔታ ነው ይላሉ። አቮካዶ ለመስረቅ በምሽት የሚመጡ የተደራጁ ወንጀለኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል።

'' ከራሳችንና ከነሱ ሕይወት መምረጥ አለብን፤ የሚያሳዝነው እኛ እራሳችንን ለመከላከል የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ መገደዳችን ነው'' ይላል አንደኛው ገበሬ። በቅርቡም አንድ የአቮካዶ ሌባ መገደሉን ነገረን።

2 ሺ ስኩዌር ሜትር በምትሆን አነስተኛ ማሳ ላይ አቮካዶ የሚያመርተው ይህ ገበሬ ትልልቅ ግምቦችን መገንባት እራሱ ከሌቦች እንደማያድን ይናገራል።

'' ዓመቱን ሙሉ ዛፎቹን ስትንከባከብና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ስታደርግ ቆይተህ ልክ ፍሬ ማፍራት ሲጀምሩ ሌቦቹ በአንድ ምሽት የዓመት ልፋትህን ሰርቀው ያድራሉ'' ሲል ችግሩ ምን ያክል የከፋ እንደሆነ ያስረዳል።

ሌላኛው ገበሬም ቢሆን ተመሳሳይ ሀሳብ ነው ያለው። '' ምንም ያክል ግምብ ብትገነባ ያልፉታል አልያም ይሰብሩታል'' ይላል።

ይህ አርሶ አደር መላው አካባቢ በዚህ ምክንያት እንዳይጎዳ ይሰጋል። በርካታ ነዋሪዎች በትልልቅ የአቮካዶ እርሻዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ አነስተኛም ብትሆን የራሳቸው ማሳ አላቸው።

''እኛ ትንሽ ተዘናግተን እንቅልፍ ከወሰደን ቤተሰቦቻችን የሚላስ የሚቀመስ አይኖራቸውም''

ኬንያ ውስጥ የአቮካዶ ምርት የሚሰበሰበው ከፈረንጆቹ የካቲት መጀመሪያ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ውስጥ ነው። ነገር ግን የአቮካዶ ሌቦቹ ገና ለመቆረጥ ያልደረሱ ፍሬዎችን ነው የሚወስዱት። በጥቁር ገበያ እንዚህ አቮዶዎች ይቸበቸባሉ።

የኬንያ መንግሥት ይህንን ለመከላከል በማሰብ ከሕዳር ወር እስከ ታህሳስ ድረስ ምንም አይነት አቮካዶ ወደ ውጪ አገራት እንዳይላክ የሚከለክል ሕግ አውጥቷል።

ነገር ግን ይህ እርምጃ እምብዛም ውጤታማ የሆነ አይመስልም። የተደራጁ የአቮካዶ ሌባዎችን ለመከላከል ሲሉም ገበሬዎቹ ምርቱ ከመድረሱ ቀደም ብለው ለመሰብሰብ ተገድደዋል።

የአቮካዶ ምርቱ ዛፎቹ ላይ መታየት ከጀመረ የሌቦች አይን ውስጥ ይገባል። ከአንድ ሳምንት በላይ የቆዩ አቮካዶዎች ደግሞ ወዲያው ይሰረቃሉ። ስለዚህ ገበሬዎቹ ወደው ሳይሆን ተገድደው ምርቱን ያለጊዜው ለመሰብሰብ ተገደዋል።

ሌላኛው የኬንያ ሜሩ ካውንቲ ደግሞ ሁኔታው በእጅጉ የከፋ ነው። የገበሬዎቹም የጥበቃ ስርአት በእጅጉ የተጠናከረና በቴክኖሎጂም ጭምር የታገዘ ነው።

በዚህ አካባቢ በየቀኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአቮካዶ ፍሬዎች ይለቀማሉ። አንድ አቮካዶ ደግሞ 19 የኬንያ ሺሊንግ ወይም ወደ 7 ብር አካባቢ ይሸጣል።

''በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሰዎች የሻይ ማሳ ሳይሆን የአቮካዶ ማሳ ነው የሚኖራቸው። አቨካዶ በጣም አስገራሚ ተክል ነው'' ይላል በሜሩ ያነጋገርነው ገበሬ።

የቴክኖሎጂ እውቀት ካለው ልጁ ጋር በመሆንም ትልቁን የአቮካዶ ማሳቸውን ይጠብቃሉ።

''ወንድ ልጄ የፊልም ጥናት ምሩቅ ነው። በቅርቡም ድሮኖችን በመጠቀም 200 የሚደርሱ የአቮካዶ ዛፎቻችንን የ24 ሰአት ጥበቃ ለማድረግ እየሰራ ነው። ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም ከአቮካዶ ምርት ከምናገኘው ትርፍ አንጻር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም''

ይህ አርሶ አደር እንደነገረን ከሆነ ከቀናት በፊት የአቮካዶ ሌቦቹ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ መጋዘን ተከራይተው የሰረቁትን አቮካዶ ሲያከማቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። አንዳንድ ገበሬዎችም የራሳቸውን የፍትህ እርምጃቸለመውሰድ እንደሚሞክሩ ነግሮናል።

''አንዳንድ ምሽቶች ላይ ሌቦቹ ሲያዙ በፊሽካ የአካባቢውን ማህበረሰብ እናሳውቃለን። ሰዎች ወዲያው ተሰባስበው የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ። እንዳንዴም ሌቦቹ ይገደላሉ። ሰዎች ዓመቱን ሙሉ የለፉበት ምርት ሲሰረቅ በጣም ይናደዳሉ''

የኬንያ ንግድ ሚኒስቴር እንደሚለው ባለፈው ዓመት ብቻ የኬንያ ገበሬዎች ከአቮካዶ ሽያጭ 132 ሚሊየን ዶላር ገቢ አግኝተዋል። ሊያውም ደግሞ ከአጠቃላይ ምርቱ 10 በመቶውን ብቻ ነው ወደ ውጭ አገራት መላክ የቻሉት።