አሜሪካና ጃፓን ህዝቦቻቸው በሱናሚ ማዕበል እንዳይጎዱ ከባህር ዳርቻዎች እንዲርቁ እያስጠነቀቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, NOAA
አሜሪካ እና ጃፓን በደቡብ ፓስፊክ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሳቢያ የተከሰተው የምድር ነውጥና የውቅያኖስ ማዕበል (ሱናሚ)ን እንዳይጎዱ በባህር ዳርቻዎች ያሉ ነዋሪዎች እንዲወጡ እያስጠነቀቁ ነው።
ጃፓን እስከ ሶስት ሜትር የሚደርስ ማዕበል እንደሚኖር አስጠንቅቃለች፤ እስካሁን ባለውም 1.2 ሜትር ርዝመት ያለው ማዕበል የአገሪቱ ደቡባዊ ክፍልን መትቶታል።
አሜሪካ ኃይለኛ ሞገድ፣ ማዕበል እንደሚከሰቱ እና የውሃ ዳርቻዎችም በጎርፍ ሊጥለቀለቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቃለች።
ግዙፉ የውሃ ውስጥ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ከአንድ ሜትር በላይ የሚደርስ ማዕበል ያስከተለ ሲሆን በፓስፊክ ደሴት ከምትገኘው ቶንጋ ግዛትም ጋር እንዲጋጭ አድርጎታል።
የሁንጋ ቶንጋ-ሁንጋ ሃፓይ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በደቡብ ፓስፊክ ውቅያኖስ እንዲሁም በበርካታ አሜሪካ ግዛቶች ተሰምቷል።
ፍንዳታውንም ተከትሎ በርካታ የቶንጋ ግዛቶች በአመድ ተሸፍኗል እንዲሁም የኤሌክትሪክ፣ የስልክ መስመሮች እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።
ፍንዳታው ያደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም።
በማህበራዊ ትስስር ገፅ የወጡ ቪዲዮዎች ቤተ ክርስቲያንና የተለያዩ ቤቶች በውሃ ተጥለቅልቀው ያሳዩ ሲሆን በዋና መዲናዋ ኑኩአሎፋ በአመድ መሸፈኗን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
በርካቶችም በመኪና ለመሸሽ ሲሞክሩና በከፍተኛ ሁኔታም የትራፊክ መጨናነቅ መፈጠሩን በማህበራዊ ትስስር ገጽ የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያሉ።
የከተማዋ ነዋሪ ሜሬ ታውፋ እንደተናገረችው ፍንዳታው የደረሰው ቤተሰቦቻቸው ለእራት ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ሲሆን ታናሽ ወንድሟ በአቅራቢያው ቦምቦች የሚፈነዳ መስሎት ነበር ብላለች።
"በመጀመሪያ ያደረግኩት ታናሽ እህቴን ጎትቼ ጠረጴዛ ስር መደበቅ ነበር። ወላጆቼን እና ሌሎች ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ጠረጴዛው ስር እንዲገቡም እየጮህኩ ነበር" በማለት ግለሰቧ ስተፍ ኮ ንዝ ለተባለ የኒውዚላንድ የዜና ጣቢያ ተናግራለች።
ግለሰቧ እንደተናገረችው ቀጥሎም በቤታቸው ውሃ በፍጥነት መግባት እንደጀመረ ነው።
አክላም "በየቦታው ጩኸቶች መሰማት ጀመሩ፣ በርካቶችም ሁሉም ሰው ከፍ ወዳለ ቦታ እንዲሄድ በጩኸት መናገር ጀመሩ " ሲትል አክላለች።
ከእሳተ ገሞራው የፈሰሰው የጋዝ፣ ጭስ እና አመድ ወደ ሰማይ 20 ኪሎሜትር መድረሱን የቶንጋ ጂኦሎጂካል ሰርቪስ አሳውቋል።












