በኢትዮጵያ የቪፒኤን አገልግሎት ፍላጎት ከ5 ሺህ በመቶ በላይ ጨመረ

ቪፒኤን

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images

ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ የቪፒኤን (VPN) አገልግሎት ፍላጎት በ5109 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ቶፕቪፒኤን.ኮም (Top10VPN.com) አስታወቀ።

የዲጂታል መረጃ ደኅንነት (ዲጂታል ፕራይቬሲ) ላይ የሚሠራው ቶፕቪፒኤን.ኮም እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ የቨርቿል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን) ፍላጎት የጨመረው መንግሥት እንደ ፌስቡክ፣ ሜሴንጀር፣ ኢንስታግራም እና ቴሌግራም ያሉ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ከዘጋ በኋላ ነው።

መንግሥት ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መጀመር ጋር በተያያዘ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መዝጋቱ ይታወሳል።

ቶፕቪፒኤን.ኮም መንግሥታት የኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ ክልከላዎችን ሲጥሉ ዜጎች ክልከላዎቹን ለማለፍ የቪፒኤን አገልግሎቶችን እንደሚጠቀሙ ይገልጻል።

መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ባለፈው ሰኞ እንዲቋረጡ ካደረገ በኋላ፤ የቪፒኤን አግልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የዲጂታል ፕራይቬሲ ቡድኑ አስታውቋል።

መንግሥት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ክልከላዎችን ከመጣሉ በፊት በነበሩት 28 ቀናት የነበረው የቪፒኤን አማካይ ፍላጎት፤ ሰኞ ዕለት ከ1ሺህ በመቶ በላይ ጨምሮ እንደነበረ ይገልጻል።

ማክሰኞ ጥቅምት 30 ደግሞ የቪፒኤን ፍላጎት ከአማካዩ ከ5ሺህ በመቶ በላይ ተሻግሮ እንደነበረ ቡድኑ ገልጿል።

ቪፒኤን ምንድነው?

ሰዎች ቪፒኤንን በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች ይጠቀሙበታል። ይህም ለተጠናከረ ደኅንነት፣ ግለኝነት እና ነጻነት።

ቨርቿል ፕራይቬት ኔትዎርክ የኢንርኔት ደኅንነት የሚሰጥ፣ ግለኝነትን የሚጠብቅ እና ነጻነት የሚሰጥ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) ነው።

ቪፒኤን መተግበሪያ በስልክዎ ወይም በኮምፒውተርዎ መካከል እና በሌላ ቦታ በሚገኝ ከመረጡት የቪፒኤን ሰርቨር ጋር ግንኙነት ይፈጥራል።

ቪፒኤን መጠቀም፤ መጎብኘት የማይቻሉ ድረ ገጾችን ለማየት፣ መተግበሪያዎች እንዲሠሩ ለማደረግ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (እንደ ኢትዮቴሌኮም ያሉ) ተጠቃሚዎች የሚጎበኙት ድረ ገጽ መረጃ እንዳይኖራቸው ያደርጋል።

ቪፒኤን የሚሰራው እንዴት ነው?

በቪፒኤን ስልክዎን/ኮምፒውተሮን ከኢንተርኔት ጋር ሲያገናኙ ቪፒኤኑ ስልክዎን/ኮምፒውተሮን በሌላ ስፍራ ከሚገኝ ሰርቨር ጋር ያገናኛል።

በዚህም ቪፒኤኑ የተጠቃሚውን የኢንርኔት አድራሻ (አይፒ አድሬስ) እና መገኛ ቦታ በመቀየር ክልከላዎችን አልፎ እንዲጠቀም ያስችላል።

ለምሳሌ አንድ ሰው በአካል አዲስ አበባ ከተማ ሆኖ በቪፒኤን አማካኝነት ኢንተርኔት ቢጠቀም፤ ቪፒኤኑ የተጠቃሚውን አይፒ አድሬስ ቀይሮ መገኛውን አውሮፓ ወይም አሜሪካ ሊያደርገው ይችላል።

ቪፒኤን በስልክ፣ በኮምፒውተር፣ እና ታብሌት ላይ ብቻ ሳይሆን በስማርት ቴሌቪዥኖች እና ራውተሮች ላይ ጭምር መጫን ይቻላል።

የቪፒኤን ደኅንነት የተጠበቀ ነው?

የኢንተርኔት ደኅንነትን ለማረጋገጥ ቪፒኤን ቁልፍ ሚና እንዳለው እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ቪፒኤኖች ደኅንነታቸው የተረጋገጠ ነው ማለት አይደለም።

ደኅንነታቸው ያልተረጋገጡ ቪፒኤኖችን አውርደን ስልኮቻችን/ኮምፒውተሮቻችን ላይ መጫን ለመረጃ መንታፊዎች እራሳን ማጋለጥ ነው። ስለዚህም የዘርፉ ባለሙያዎች ደኅንነታቸው የተጠበቁና የተመሰከረላቸው ቪፒኤኖችን እንድነንቀም ይመክራሉ።

Top10VPN.com በብዙ ቪፒኤኖች ላይ ፍተሻዎችን አድርጌ ለይቻለሁ ያላቸውን ቪፒኤኖችን አጋርቷል።

ቡድኑ ክፍያ ከሚጠየቁባቸው ቪፒኤኖች መካከል የተመረጡ ናቸው ካላቸው መካከል ኤክስፕረስቪፒኤን (ExpressVPN)፣ ኖርድቪፒኤን (NordVPN) እና ሳይበርጎስት (CyberGhost) ይጠቀሳሉ።

ክፍያ የማይጠይቁ፣ ደኅንነታቸው የተረጋገጠ እና የተሻለ አገልገሎት ይሰጣሉ ካላቸውን የቪፒኤን አገልግሎቶች መካከል ደግሞ ዊንክራብ (Windcribe) እና ፕሮቶንቪፒኤን (ProtonVPN) ተጠቃሽ ናቸው።