የኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ አስወጣ

ሳፋሪኮም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ በአገሪቱ ለሚያካሂደው ኢንቨስትመንቶች አደጋ መደቀኑንና የሚፈጠሩት ክስተቶች የወደፊት የንግድ ውሳኔዎች ላይ ተዛማጅነት እንዳለው ለቢቢሲ ገለጸ።

ኩባንያው በቅርቡ የተቀጠሩ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሠራተኞቹንና ተቋራጮችን ከአገሪቱ ማስወጣቱን አስታውቆ፤ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞቹ ደግሞ ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ገልጿል።

በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ ትልቁ እና ትርፋማ የሆነው የቴሌኮም ኩባንያ፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ጎረቤት ክልሎች እየተዛመተ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ንደጓ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከወራት በኋላ አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ያሸነፈው ሳፋሪኮም በአውሮፓውያኑ 2022 አጋማሽ ላይ ሁሉም መሰረተ ልማቶች ከተዘረጉ በኋላ ሥራውን እንደሚጀምር ብሩህ ተስፋ አሳድረዋል።

ቢቢሲ በዛሬ ረቡዕ ጠዋት አዲስ አበባ በሚገኘው የኩባንያው ጽህፈት ቤት በመገኘት ባደረገው ቅኝት አነስተኛ እንቅስቃሴ የተመለከተ ሲሆን ይህም በቅርብ ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ ለኩባንያው እርግጠኛ አለመሆኑን ጠቋሚ ነው።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘውና በሳፋሪኮም የሚመራው የኩባንያዎች ጥምረት በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ እና ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለመቅጠር አቅዷል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ ናቸው።

ሳፋሪኮም የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ለመደገፍ ከአሜሪካ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ይገኛል የተባለው የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሁኔታ ላይ እርግጠኛ አይደለም።

የአሜሪካ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥሏል። ከዚህም መካከል አጎዋ የተሰኘው የአሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል መታገድ ይገኝበታል።

እንደ አውሮውያኑ በ2020 በአግዋ ሥርዓት አማካኝነት ኢትዮጵያ 237 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ወደ አሜሪካ አስገብታለች።