የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ይጠበቃሉ

የፎቶው ባለመብት, State department
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት ለአራት ቀናት ወደ አዲስ አበባ፣ ካርቱም እና ሪያድ በመጓዝ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
ባለሥልጣናቱ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ የሆኑት ሞሊ ፊ እና በአምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ምትክ በቅርቡ የተሾሙት አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ናቸው።
ከሰኞ ጥር 09 እስከ ጥር 12/2014 ዓ.ም በሚደረገው በዚህ የዲፕሎማቶቹ ጉዞ በኢትዮጵያና በሱዳን ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ባለሥልጣናቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ ፕሬዝዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ሰኞ ጥር 02/2014 ዓ.ም ያደረጉት "ገንቢ የስልክ ውይይት ተከታይ ጉዳዮችን" ያነሳሉ ብሏል።
በዚህም ዲፕሎማቶቹ የአየር ጥቃቶች እና ሌሎች ግጭቶች እንዲቆሙ፣ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲመቻችና ለሁሉ አቀፍ ብሔራዊ ውይይት የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲመቻቹ በአሁኑ ወቅት የተከፈተውን የሰላም ዕድል እንዲጠቀሙበት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ያበረታታሉ ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣኗ ሞሊ ፊ እና ልዩ መልዕክተኛው ሳተርፊልድ ወደ አዲስ አበባ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሪያድና ወደ ጎረቤት ሱዳን እንደሚያመሩ ተገልጿል።
በዚህም ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በቀውስ ውስጥ ለምትገኘው ሱዳን በሲቪሎች የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ከሳዑዲ በማስከተልም ሁለቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊዎች ወደ ሱዳን ካርቱም በማቅናት ከዴሞክራሲ ደጋፊ አክቲቪስቶች፣ ከሴቶችና ከወጣቶች ቡድኖች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከጦር ኃይሉ መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
ከዚያ በማስከተል የመጨረሻ የጉዟቸው መዳረሻ የምትሆነው አዲስ አበባ ስትሆን፣ እዚያም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ወይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ መሪዎች በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ጦርነትና በአገሪቱ ስላሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መወያየታቸውን የወጡ መግለጫዎች አመልክተዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ አሜሪካ በያዘችው አቋምና በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።
የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ከጣለው የቪዛ እገዳ እንዲሁም ከሁለት ሳምንት በፊት ተግባራዊ የሆነው ኢትዮጵያ ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ታስገባበት የነበረው የአጎዋ ተጠቃሚነት የእገዳ እርምጃ ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥትም አሜሪካ ለአማጺያኑ የሚያደላ መግለጫና እርምጃ እየወሰደች ነው በማለት አሜሪካን በወገንተኝነት ሲከስ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ተሰናባቹ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን አዲስ አበባ ደርሰው ከተመለሱ በኋላ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስልክ መነጋገራቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጅማሬ ሊሆን እንደሚችል በስፋት ተነግሯል።
አሜሪካ ጦርነቱ በድርድር መቋጫ እንዲያገኝ ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ብትቆይም እስካሁን ውጤት ሳይገኝ ቆይቷል።
ከሰኞ ጀምሮ ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚያቀኑት ሁለቱ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ሙያ ያዳበሩ ዲፕሎማቶች መሆናቸው ይነገራል።
ሜሪ ካትሪን ሞሊ ፊ ሜሪ አሁን ያሉበትን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊነት የተረከቡት ባለፈው መስከረም ወር ሲሆን ከዚያ በፊት ለሦስት ዓመታት ያህል በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ውስጥም በከፍተኛ ኃላፊነት አገልግለዋል።
አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ ደግሞ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀ ልምድ እንዳካበቱ ይነገርላቸዋል።
አምባሳደር ሳተርፊልድ በቱርክ፣ በሶሪያ፣ በቱኒዚያ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና ሊባኖስ ውስጥ አገራቸውን ወክለው በዲፕሎማትነት ሰርተዋል።
አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ማይክ ፖምፔዮ ከፍተኛ አማካሪ ነበሩ።














