ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአና ፍራንክን ቤተሰብ ለናዚ አሳልፎ የሰጠ ተጠርጣሪ ከ77 ዓመታት በኋላ በአዲስ ጥናት ታወቀ
የአና ማስታወሻ ታሪክ ባለቤት የሆነችው አን ፍራንክን እና ቤተሰቧን ለናዚዎች አሳልፎ የሰጠው ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም የተባለ ግለሰብን የጠቆመ አዲስ የምርመራ ውጤት ይፋ ተደረገ።
አይሁዳዊዋ ታዳጊ አና እ.ኤ.አ. በ1945 በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በ15 ዓመቷ ነበር ህይወቷ ያለፈው። ከአና ህልፈት በኋላ የታተመው የግል ማስታወሻዋ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈ በናዚ ግፍ ሰለባ የተጻፈ ግለ ታሪክ ነው።
አንድ የቀድሞ የኤፍቢአይ ባልደረባን ጨምሮ የአንድ የምርመራ ቡድን አባላት በአምስተርዳም የሚኖረው አርኖልድ ቫን ደን በርግ የተባለ አይሁዳዊ የራሱን ቤተሰብ ለማዳን የአናን ቤተሰቦች አሳልፎ ሳይሰጥ እንዳልቀረ ተናግረዋል።
የታሪክ ተመራማሪዎችን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ያቀፈው ይህ ቡድን ይህንን በርካታ አመታት ያለፈውን ጉዳይ ለመፍታት ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ስድስት አመታት በስራ ላይ አሳልፏል። ከተጠቀሙባቸው ዋና ዋና ስልቶች ውስጥም በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማመሳከር የሚረዳ አንድ የኮምፒዩተር ቀመርን መጠቀምን የሚጨምር ሲሆን ይህም በሰዎች ቢሰራ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰዓታትን ይወስድ እንደነበር ተገልጿል።
ተጠርጣሪው ቫን ደን በርግ የአምስተርዳም የአይሁድ ምክር ቤት አባል ሲሆን ይህ ምክር ቤትም በአይሁድ አካባቢዎች የናዚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረ ነው። ምክር ቤቱ እ.ኤ.አ. በ1943 የተበተነ ሲሆን አባላቱም እንደማንኛውም አይሁድ ወደ ማጎሪያ ካምፖች እንዲገቡ ተደርጎ ነበር።
ነገር ግን የምርመራ ቡድኑ ቫን ደን በርግ ወደ ማጎሪያ ካምፑ እንዳልተላከ እና በአምስተርዳም ከተማ በሰላም ሲኖር እንደነበረ አረጋግጧል።
"ቫን ደን በርግ በወቅቱ ወደ ካምፕ ከመወርወር የሚያተርፉትን ነገሮች ሲያጣ ራሱን እና ሚስቱን ለማትረፍ ሲል ለናዚዎች ዋጋ ያለው መረጃ መስጠት ነበረበት" ሲል የቀድሞ የኤፍቢአይ አባል ቪንስ ፓንኮክ ሲቢኤስ ለተሰኘው ቴሌቪዥን ተናግሯል።
አክሎም የምርመራ ቡድኑ አንድ አይሁዳዊ ሌላ አይሁዳዊን አሳልፎ ሰጠ የሚነውን አምኖ ለመቀበል ተቸግሮ እንደነበርም አልሸሸገም። እንዲሁም የአን አባት ኦቶ ፍራንክ ራሱ ጉዳዩን ያውቅ እንደነበር እና ሚስጥር አድርጎ ይዞት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን ማግኘታቸውንም የምርመራ ቡድኑ አባል ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም ተደራጅቶ ተቀምጦ የነበረ ፋይል ውስጥ አርኖልድ ቫን ደን በርግ የአናን ቤተሰብ አሳልፎ እንደሰጠ የሚገልጽ እና የጸሃፊው ማንነት የማይታወቅ ደብዳቤ ለአና አባት ተጽፎ መገኘቱም ተግለፏል።
የምርመራ ቡድኑ አባል የሆኑት ፓንኮኬ ለቴሌቪዥን ጣቢያው እንደተናገሩት ይህ እውነታ ይፋ ሳይደረግ የቀረው በፀረ ሴማዊነት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
"ምናልባት ይህንን እውነታ ይፋ ቢያደርገው እሳቱን የበለጠ እንደሚያቀጣጥለው ተሰምቶት ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል። "ነገር ግን ቫን ዴን በርግ አይሁዳዊ መሆኑን ተከትሎ ህይወቱን ለማዳን ሲል ናዚዎች ሊያጠቁት የሚችሉት ቦታ ላይ መቀመጡን መዘንጋት የለብንም" ሲልም ተናግሯል።
የኔዘርላንዱ ዴ ቮልስክራንት ጋዜጣ እንደዘገበው ቫን ደን በርግ በ1950 ህይወቱ አልፏል። የአና ፍራንክ ሀውስ ሙዚየም በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ የምርመራ ቡድኑ ተግባር እንዳስደነቀው ገልጿል።
የሙዚየሙ ዋና ዳይሬክተር ሮናልድ ሊዮፖልድ አክለውም አዲሱ ጥናት "ጠቃሚ አዳዲስ መረጃዎችን እና ለተጨማሪ ምርምር የሚያበቁ አስደናቂ መላምቶችን ፈጥሯል" ብለዋል። ሙዚየሙ በምርመራው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሌለው በመግለጽ ነገር ግን ማህደሮችን እና ሙዚየሙን የምርመራ ቡድኑ እንዲጠቀም ፈቅዶ ነበር።