ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥዑም ቡና ለምን ስታርባክስ ያጣጥመዋል?

ይህ ብሶት የወለደው ጥያቄ ነው። በአንድ ስኒ ቡና ውስጥ የሚማሰል የዘመን ጥያቄ።

ርዕዮተ ዓለም፣ የእጅ አዙር ቅኝ ገዥነት፣ የካፒታሊዝም መርገምት፣ የማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት፣ የምጣኔ ሃብት ፖለቲካና ምስቅልቅሎሽ በዚህ ጥያቄ ውስጥ ይማሰላሉ።

ጥያቄው አጭር ነው።

ስታርባክስ (Starbucks) አቦሉን እየጠጣ የኢትዮጵያ ገበሬ ለምን በረካው ይደርሰዋል?

ኔስሌ (Nestle) ትኩስ ቡና ፉት እያለ የካልዲ ልጆች ለምን ቅራሪውን ይጠጣሉ?

በዚህ ሐተታ ፍጻሜ አንድ አዲስና ድፍረት የተመላበት ሐሳብ ይቀርባል።

"ካልዲ" ሊያልፍለት የሚችለው ፍየሉንም፣ ቡናውንም፣ ስኒውንም የራሱ ሲያደርገው ነው የሚል የቡና ፍልስፍና።

እሱን ሐሳብ በድፍረት ከሚያነሱ እንግዳችን ጋር እንሟገታለን።

ከሁሉ በፊት ግን አንድ ነገር መጥራት አለበት።

የኢትዮጵያ ቡና ልኬት

የኢትዮጵያ ቡና ልኬቱ የቱ ጋ ነው? የምር የኢትዮጵያ ቡና በአገር ውስጥ እንደሚናገነው ነው? ወይስ "ከምሥራቅ አፍሪቃ 1ኛ" እንደሚባለው አባዜ ሌላ ቅጥያ ነው?

በሌላ አነጋገር ከኢትዮጵያ ማኅጸን የሚወለደው አረቢካ ቡና የዓለም ቦታው በትክክል የቱ ጋ ነው?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መቼስ ከአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የቀረበ ሰው የለም። የፌይርፋክሱ አቶ ዘመዴነህ።

ለምን ቢባል እሳቸው የሥራ ባህሪያቸው ሆኖ በርካታ የዓለም ከተሞችን ይዞራሉ።

ዘርፈ ብዙ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ገብተዋል።

የግዙፍ ኩባንያ አለቆች ጋር ሻይ - ቡና ተባብለዋል። ፊርማ እያኖሩ ተፈጣጥመዋል፤ ተጨባብጠዋል። ከብራዚል እስከ አሜሪካ፣ ከአርጀንቲና እስከ ሳዑዲ ኖረዋል፡፡

ስለዚህ ጥያቄዎን እንድገምላቸው?

"የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ደረጃውና ልኬቱ ወየት ነው? ቡናችን የምናስበውን ያህል ገናና ነው?"

አቶ ዘመዴነህ ለዚህ ምላሽ ወደ ሦስት ከተሞች በምናብ ይዘውን እንዲበሩ እንፍቀድ።

ፓሪስ፣ ለንደን እና ዋሺንግተን።

ይህን ቃለ ምልልስ ስናደርግ ከነበሩበት ከዋሺንግተን ዲሲ መጀመር እንችላለን።

ዋሺንግተን

"ከወራት በፊት ሁለት ነጭ ሴት ወጣቶች አዲስ የቡና ሱቅ ከፈቱና ጋብዘውኝ ሄድኩ" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

ሁለቱ ፈረንጆች ኢትዮጵያን ጎብኝተው ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ነው የቡና ሱቅን የከፈቱት። ይህ የቡና መጠጫ ቤት የት ነው የሚገኘው?

በካፒቶል ሒል አቅራቢያ፤ በሕዝብ እንደራሴዎች የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ዋና በር በኩል።

የአሜሪካ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት 435 አባላት አሉት፡፡ በዚያ ላይ በዚያው ሰፈር ገባ ወጣ የሚሉ ተጨማሪ 100 የሴኔት አባላት አሉ።

ምን ማለት ነው ይሄ?

በዚች ቡና መሸጫ ጎራ የማይል እንደራሴ የለ ይሆናል።

በዚህች ካፌ ያ ሁሉ እንደራሴ የሚጋፋው የኢትዮጵያ ቡናን ለመቃመስ ነው። ምክንያቱም እጅግ ዝነኛ ነዋ።

አቶ ዘመዴነህ አይበሉት እንጂ ይሄኔ እነ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የኢትዮጵያን ቡና ፉት ብለው ይሆናል ሸንጎ የሚቀመጡት። ማን ያውቃል?

ለንደን

ከአቶ ዘመዴነህ ጋር ከዋሺንግተን ወደ ለንደን እንብረር።

የምንበረው የቡናችንን ልኬት በአቶ ዘመዴነህ የጉዞ አጋጣሚዎች ውስጥ አጮልቆ ለመቃኘት ነው።

በለንደን እጅግ ቅንጡው አውቶሞቢል ሮልስ ሮይስ ይባላል።

ሮልስ ሮይስ በጣም ትንሹ መነሻ ዋጋው 300 ሺህ ዶላር ነው።

እንጂ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ፣ በትዕዛዝ ብቻ የሚመረቱ አውቶቢሎችም አሉት።

ታዲያ ሮልስ ሮይስ ለናጠጡ ሃብታሞች አዳዲስ ሞዴል መኪናዎችን ሲሸጥላቸው አንድ ውድ ስጦታ አብሮ ያኖራል።

ይህን ስጦታ ከመኪናው ኪስ ውስጥ ሸጎጥ አድርጎ ያስቀምጣል። ምን ይሆን?

ይህ ስጦታ የከበረ ድንጋይም፣ አልማዝና ወርቅም አይደለም። እጅግ ተወዳጁን አረንጓዴውን ወርቅ እንጂ። የታሸገ ኢትዮጵያ ቡና።

ይህ ስለኢትዮጵያ ቡና ልኬት ብዙ ይናገራል።

ፓሪስ

ከለንደን እንውጣ፣ ወደ ጎረቤት ፓሪስ እናቅና፤ አቶ ዘመዴነህ ያዩትን ዕንይ፡-

የፓሪስ እምብርት የት ነው ካልን ሾንዞሊዜ (Champs-Élysées) አደባባይ ናት።

በየዓመቱ ሚሊዮን ጎብኚዎች ይርመሰመሱበታል።

በሾንዞሊዜ እምብርት የዝነኛው ቡና የኔስሌ አውራው የቡና ጣቢያ (Flagship store) ይገኛል።

ልክ ወደ ውስጥ ሲዘለቅ፣ ዕውቁ ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ ኔስፕሬሶ የቡና ማሽንን ሲያስተዋውቅ ይታያል።

ክሉኒ ከነ መልከ መልካምንቱ በግዙፍ ሰሌዳ ላይ ሲታይ የኮረዳ ልብ ያቀልጣል።

ከጆርጅ ክሉኒ ጎን አንድ እጅግ ውድ ዕቃ አለ። የሚሊዮኖችን ልብ የሚያቀልጥ፤ የኢትዮጵያ ቡና!

"አስበው! ይህ በፓሪስ ዋነኛው የኔስሌ ቡና መሸጫ ነው! ታዲያ ይህ ምን ይነግርሃል?" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

የዚህ ሁሉ ሽርሽር ማጠንጠኛ አንድ ነው። የኢትዮጵያ ቡና ልኬት በዓለም የዝና ማማ ላይ መሆኑን መመስከር።

"ታያለህ! ብራንዲንጉን ኔስሌ ሠርቶልናል። እኛ መድከም አይጠበቅብንም እኮ። ከእኛ የሚጠበቀው የቡና ስኒው ላይ የገበያ ድርሻ መያዝ ነው" ይላሉ፣ አቶ ዘመዴነህ።

እሳቸው ይህን ጽንሰ ሐሳብ በእንግሊዝ አፍ "Controlling the cup" ይሉታል።

ሐሳቡ ሲገለጽ እንደ ስኒ ቡና ቅልብጭ ያለ ይምሰል እንጂ መልዕክቱ ጥልቅ፣ የሚፈልገው ሥራ ውስብስብ ነው።

ለመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በቡና እንዲያልፍላት ከተፈለገ "ስኒውን መቆጣጠር አለባት" ሲባል ምን ማለት ነው?

በርካሽ ገዝተውን፣ እነሱ ይደምቁበታል

የቡና ገበያ ውድድር እንዴት ያለ ነው? ሸማች ባወጣው የወደቀ ዋጋ የሚተመን ነው።

ለዚያም ነው ብራዚልን ድርቅ ሲደቁሳት፣ የኢትዮጵያ ቡና ቶሎ የሚፈላው።

ለዚህም ነው ብራዚል ከዓለም የቡና ገበያ ስትፋታ፣ ለኢትዮጵያ ቡና ሠርግና ምላሽ የሚሆነው።

በዓለም የቡና ላኪዎች ዝርዝር ብራዚልን የሚያኽል የለም።

ቬትናምና ኮሎምቢያ ይከተላሉ።

ኢንዶኒዥያና ኢትዮጵያ ደግሞ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ።

በተወዳጁ አረቢካ ቡና ግን ከብራዚል ተከታትለው የሚመጡት ኮሎምቢያና ኢትዮጵያ ናቸው።

ያለመታደል ሆኖ የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ የሚወስኑት ፈርጣማ ኩባንያዎች እንጂ ምስኪን ገበሬዎች አይደሉም።

ቢሆንም ግን ቡና አብቃይ አገራት፣ በተለይም ብራዚል ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና ፍሬ ሲመናመን የዓለም ቡና ፍላጎትና አቅርቦቱ ይዛነፋል።

ስታርባክስና ኔስሌ ያፋሽካሉ።

ይሄኔ በቡና ሱስ የሚያዛጉ ጀርመኖች፣ ደቾች፣ ጃፓኖችና ሳዑዲዎች ወደ ኢትዮጵያ ያማትራሉ።

ይሄን ጊዜ ነው የቬትናምና የኢትዮጵያ ገበሬ ፈገግ የሚሉት።

ፈገግታቸው ግን ቶሎ ይጠፋል።

የቬትናምን ባናውቅም፣ የኢትዮጵያ ገበሬ ፈገግታው ሙሉ አይሆንም። ፈገግታውን የሚጋርዱ በርካታ ሰርጎ ገቦች በገበያው ሰንሰለት ተሰግስገው ቆይተዋል።

የቡና ግብይቱ ከዘመነ ወዲህ መሻሻል ቢኖርም ሩቅ ምሥራቅ፣ አትላንቲክ ማዶ እና መካከለኛው ምሥራቅ የምንልከው ቡና ሌላ እንቅፋት ይገጥመዋል።

ፈርጣማዎቹ ሸማቾቻችን፣ 'ዋጋ አንጨምር' እያሉ ያስቸግሩናል። በራሳችን ቡና በስንት መሸጥ እንዳለብን ይነግሩናል።

አቶ ዘመዴነህን ጨምሮ በርካቶች እንደሚያምኑት እንዲህ አቅመቢስ ያደረገን ዕሴት አልባ ጥሬ ቡና መላካችን ነው።

እንጂማ ኒውዮርክ ማዲሰን ጎዳና አንድ ስኒ ቡናችን በ5 ዶላር ፉት የሚላት ብዙ ነው። ያውም ተስገብግቦ፤ ለዚያውም ሳያቅማማ።

የብዙ ምዕራባዊያን ሞጃዎች ቀን የሚበራው ከይርጋጨፌና ከሲዳማ በሚፈነጠቅ ፍሬ ነው።

ምን ዋጋ አለው ታዲያ፣ ከዚች ወርቅ ስኒ ቡና የኢትዮጵያ ገበሬ ሽራፊ 50 ሳንቲም ዶላር እንኳ ተንጠባጥባ አትደርሰውም። ለምን?

ፍየሏ ካልዲን ረግማው ይኾን?

የኢኮኖሚ ዋልታ-ቡና! ቡና!

ቡና ለኢትዮጵያ የገቢ ሱሷ ነው። ቡና ሳታጠጣ የውጭ ምንዛሬ አኼርና ሪዝቅ አይከፈትላትም።

ኢትዮጵያና ቡና ለዓመታት እንደተዋደዱ ያሉት ለዚሁ ነው።

መቼም የማይጠገነው የንግድ ሚዛንን በስሱም ቢሆን ለመጠገን የሚፍጨረጨረው እሱ ነው። 'ቡናችን! የኢኮኖሚው ዋልታችን!'

በየዓመቱ የ16 ቢሊዮን ዶላር የገቢ ሸቀጥ የዞረ ድምር ዕዳን በ3 ቢሊዮን ተኩል ነው የሚጣጣው። ልዩነቱን ተመልከቱት።

ከዚህ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ የቡና ድርሻን የሚጠጋ አንድም ሸቀጥ የለም።

ወርቅ እንኳ ቡና ላይ አልደረሰበትም። ጨርቃ ጨርቅም፣ ኤሌክትሪክም፣ ቦሎቄም ሰሊጥም መላክ ጀምረን ነበር፡፡ የቡናን ያህል ዶላር አላመጡም እንጂ።

በአሐዝ እናውራ ከተባለም ይቻላል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ትልካለች።

በዚያ ላይ ቡና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚሆነው ሕዝብ ቁጥር የዋዛ አይደለም።

እንደው ለስሌት እንዲመች የኢትዮጵያ ሕዝብ መቶ አሥር ሚሊዮን ነው ቢባል፣ 20 ሚሊዮኑ በቡና ሰንሰለቱ በአንድም ሆነ በሌላው ይነካል። ወይም ተጠቃሚ ነው።

የቡና ጫካ ወርድን ወደ አምራቾች ጓሮ ብናማትር ግን ሚሊዮነር መሆን የሚገባቸው ገበሬዎች ኑሯቸው ፈቀቅ አላለም።

ወጥተው ወርደው፣ ኮትኩተው፣ አብቅለው ከዚህ ረዥም የቡና ሰንሰለት የሚያገኙት እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።

እንዲህ እንደ ዘንድሮው በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ እጥፍ ጭማሪ ኖሮት እንኳ አብቃዮች አልቦረቁም።

ለምን ከተባለ የቡና አብቃይ ገበሬ ከጠቅላላ ድርሻው 10 እጁን እንኳ አይወስድም።

ዘንድሮ ቡና በዓለም ገበያ ዋጋው ተመነደገ እየተባለ ራሱ የኢትዮጵያ ገበሬ እንዴት ፈገግ ሊል አልቻለም?

ኢትዮጵያንስ አረንጓዴ ወርቄ እያለች የምታቆላምጠው ተክል መቼ ይኾን የሚያበለጽጋት?

ደግሞ'ኮ በአፍሪቃ በቡና አረቢካ ኢትዮጵያን የሚያህል የለም። ሩዋንዳም፣ ኡጋንዳም፣ ኬንያም ቢደማመሩ አይደርሱባትም።

"በዓለም ላይ ከነዳጅ ቀጥሎ በስፋት የሚሸቀጥ የቡናን ያህል ምንም ሸቀጥ የለም" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

ቡና ለኢትዮጵያ ወርቅ ብቻ ሳይሆን ነዳጃም ሆኖ ዘልቋል ማለት ነው።

ሳዑዲ ለነዳጇ እንደምትሳሳው ኢትዮጵያም ለቡናዋ ብትቆረቀር አይገርምም።

ሳዑዲዎች ስለ ነዳጃቸው ከ30 ዓመት በፊት ስለነደፉት አንድ ስትራቴጂ ከአፍታ ቆይታ በኋላ አቶ ዘመዴነህ ይነግሩናል። እኛ ለቡናችን ልንኮርጀው የሚገባ ነገር ስለሆነ።

አሁን የጀመርነውን ሐተታ እንጨርስ። ቡናና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው?

አዎ! ቡና ለኢትዮጵያ ሱሷ ነው የምንለው በምክንያት ነው።

ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ቡና ልካ ያገኘችው አዱኛ 1 ቢሊዮን ዶላር ሊሞላ ጥቂት መቶ ሺህ ዶላሮች ብቻ ነበር የጎደሉት።

ዛሬ ላይ ቆመን ባለፉት አራት ወራት የተላከውን የቡና መጠን ብናሰላ ራሱ 100 ሺህ ቶን አልፏል።

ዘንድሮ ከዚህም ከፍ ያለ መጠንና ዶላር እየተጠበቀ ነው።

ወደ 280 ሺህ ቶን ተልኮ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ለማምጣት ነው እየተሠራ ያለው።

ዘንድሮ ዋናዎቹ የአረንጓዴው ወርቅ መዳረሻ አገራት ደግሞ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና ቤልጂየም ሆነዋል።

ሌላም መልካም ዜና አለ፣ ዘንድሮ።

የዓለም 2ኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ በሆነችው ቻይና ቡና መጠጣት እየተዘወተረ ነው። ይህ ወደፊት እጅግ ሰፊ ገበያን ይዞ ሊመጣ ይችላል።

ሌላም መልካም ዜና አለ ዘንድሮ!

የአረቢካ ቡና ዋጋ በ10 ዓመት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

ይህ ካለፈው የፈረንጆች ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር እጥፍ ዋጋ መሆኑ ነው።

"የቡና ዋጋ እንዲህ ሊመነደግ የቻለው የብራዚል ድርቅ መከሰትና የዓለም ምጣኔ ሀብት በድንገት ከፍተኛ መነቃቃት በመገጣጠማቸው ነው" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

ለመሆኑ በንግድ ሚዛን መዛነፍ ፍዳዋን ለምታየው ኢትዮጵያ ይህ ግሩም ዜና ምን ያህል የሚያስቦርቅ ነው?

የአረቢካ ቡና ዋጋ እጥፍ መሆን የገበሬዎቻችንን ኑሮና ገቢ ፈቀቅ ያደርገዋልን?

እንዴት ነው ኢትዮጵያ ስኒውን የምትቆጣጠረው?

መነሻችን ላይ ያነሳነውን ሐሳብ ተጨማሪ ቡና ፉት እያልን እናውጠንጥን።

ዕሴት መጨመር አንድ ነገር ነው። በዚህ ረገድ ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ለውጦች አሉ።

ሆኖም ቡና አብቃዮቻችንን ቢሊየነር አላደረጉም። ለምን?

የቡና ገበያ ዋጋም ተመንድጎ ሳለ የቡና ማኅጸን ኢትዮጵያ ግን አሁንም አላለፈላትም። ለምን?

አቶ ዘመዴነህ ደጋግመው፣ "ምክንያቱም ስኒውን ስላልተቆጣጠርን ነዋ" ይላሉ።

እሳቸው ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው ካልን፤ የቡና ሰንሰለቱን የመጨረሻ ጫፍ ኢትዮጵያ ትዘውረው ማለታቸው ነው።

ስኒውን እንዴት ነው ኢትዮጵያ የምትቆጣጠረው?

"ለምሳሌ ለምን ከኔስሌ ጋራ ተሻርከን ሱቅ አንከፍትም? በትንሹ መጀመር እንችላለን። ኢኩይቲ (ድርሻ) መግዛትም ይቻላል" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

እውነት ነው። ኢትዮጵያ ድንገት ተነስታ እንደ ሰታርባክስ 33 ሺህ ካፌ በመላው ዓለም መክፈት ቀላል እንደማይሆንላት እሳቸውም ተረድተውታል።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ዘመዴነህ፣ "ነገር ግን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ላይ የእኛ የቡና መሸጫ ጣቢያዎችን ማኖር ይቻላል።"

ለምሳሌ የት?

"ለምሳሌ ኒውዮርክ ማዲሰን ጎዳና፣ ወይም ደግሞ ፓርክ አቬኒዩ ላይ፣ አሊያም ዝነኛው ፊቭዝ አቬኒዮ (5th Avenue) አካባቢ። በእነዚህ ቦታዎች እኛ የምንቆጣጠረው የኢትዮጵያ ቡና መሸጫ ቢኖርስ?"

ለምሳሌ የት?

"ለምሳሌ…በፓሪስ ሾንዞሊዜ ጎዳና፣ በለንደን ኦክስፎርድ ጎዳና ኢትዮጵያ የቡና ሱቆች ቢኖሯትስ?"

"…ወይም ደግሞ ከግዙፍ የቡና ኩባንያዎች ድርሻ ብንገዛስ? ለምን አይሆንም?"

አረንጓዴው አምባሳደር

አረቢካ የኢትዮጵያ አረንጓዴው አምባሳደር ነው። ማንም የእሱን ያህል አገሪቱን አላስተዋወቀም።

እግረ መንገዱን ኢትዮጵያን ያስተዋውቅ እንጂ የምዕራብ አገር ኩባንያዎችን ኪስን ነው እያደለበ ያለው። ምን ተሻለ?

አቶ ዘመዴነህ የሚሉት የዕውቅ ቡና ቸርቻሪዎችን (Retail Brand) ቦታ ቀስ በቀስ ካልተቀራመትን ቡናችን መቼም ሊታደገን አይችልም፣ ነው።

አረቢካ የኢትዮጵያ ነው። ቡና ጠጪዎች በኢትዮጵያ የሚተመነውን ውድ ዋጋ ለመክፈል በፍጹም አያቅማሙም። በመሀል ግን ቡና ገዥ ኩባንያዎች ተሰንቅረዋል።

ቡና ጠጪዎች ለኢትዮጵያ ዝነኛ ቡና ለአንዲት ስኒ 5 ዶላር ለመክፈል ፈቅደዋል። በመሀል ግን ይህን ዶላር የሚሰበስቡ ሌሎች ናቸው።

የዶላሩን አቦል የሚያጣጥሙት እነ ኔስሌ ናቸው።

"አንድ ቡና ጠጪ 5 ዶላር የሚፍለው እኮ ለብራንዱ ነው። ለጥዑም ቡናችን ነው። ለምን ሌላው ሲወስደው ቆመን እናያለን ታዲያ?"

ይህ ነው አቶ ዘመዴነህ እየተንገበገቡ የሚጠይቁት ተደጋጋሚ ጥያቄ።

እርግጥ ነው አንድ አገር ከሃብቷ በይበልጥ የምትጠቀመው የንግድ ሰንሰለቱን (value chain) በተቆጣጠረችው መጠን ነው።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የቡናን የግብይት ሰንሰለት ልትቆጣጠር ቀርቶ የለችበትም። ከቡና ንግድ ሰንሰለቱ 20 ከመቶው ከቁጥጥሯ ውጪ ነው።

በጥሩ ሁኔታ ቡና ማሸግ እንኳ የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ነው።

አቶ ዘመዴነህ እንደሚሉት በአማካይ ለስኒ 5 ዶላር የሚከፍለው ደንበኛ ጋር በዚህም በዚያም ብላ ኢትዮጵያ ቀጥታ ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋታል።

የኢትዮጵያን ቡና አፍቃሪዎች ለእነ ኔስሌ እና ስታርባክስ ብቻ አደራ ሰጥተን ልንተዋቸው አይገባም ነው የሚሉት።

ለመሆኑ የአቶ ዘመዴነህ ሐሳብ መሬት ላይ መውረድ የሚችል ነው? ወይስ ተምኔታዊ?

"እውነት ነው፣ አሁን ስናገረው ላይመስል ይችላል። ዛሬ ከተጀመረ ግን የዛሬ 10 እና 20 ዓመት ያልፍልናል" ይላሉ።

ለዚህ እንደ ሁነኛ ማስረጃ የሚያቀርቡት ደግሞ 'አሳምሬ አውቃቸዋለሁ፣ አብሬያቸውም ሠርቻለሁ' የሚሏቸውን ሳዑዲዎችን ነው።

የዛሬ 30 ዓመት ግድም ሳዑዲዎች ቢያማትሩ ዓለም በፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ተጥለቅልቋል።

ቆም ብለው አሰቡ።

'እንዴ! እኛ ከምንልከው ድፍድፍ ነዳጅ ወስደው ነው ይህን ሁሉ ኢንዱስትሪ የከፈቱት። እኛ ጥሬውን ካልሰጠናቸው ከየት ያመጡታል?' ብለው ቁልፍ ጥያቄ ጠየቁ።

መልሱ፣ 'ከየትም!' የሚል ነበር።

ታዲያ ለምን እኛ ራሳችን አንሠራውም አሉ። ስትራቴጂ ነደፉ።

አሁን ሳዑዲ በዓለም ከፍተኛ ፔትሮ ኬሚካል አምራች ከሆኑ አገሮች ተርታ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያም ቡናን እራሷ ማድረግ ትችላለች። "ምክንያቱም አረቢካን እኛ ካልሰጠናቸው ከየት ያመጡታል?" ይላሉ።

"እርግጥ ነው ቡና እንደ ነዳጅ ተጽእኖ የመፍጠር የእምቢታ ጉልበት (leverage) አይሰጠን ይሆናል። ቢሆንም የሳዑዲዎችን ስትራቴጂ መከተል እንችላለን። ስኒውን መቆጣጠር እንችላለን። መጀመር ያለብን ግን አሁን ነው። ዛሬ።"