የብሪታኒያ ጦር ከሩሲያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ላለችው ዩክሬን መሳሪያ እያቀረብኩ ነው አለ

ሩሲያ 100 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ማስፈሯን ተከትሎ ዩክሬንን ለመከላከል በሚል ብሪታንያ ለዩክሬን አጭር ርቀት ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን እያቀረበች እንደሆኑ የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስትር አስታውቀዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤን ዋላስ ለፓርላማ አባላት መብራሪያ በሰጡበት ወቅት የብሪታንያ አነስተኛ ቡድን ወደ ዩክሬን ተልኮ ወታደራዊ ስልጣና እንደሚሰጥም ተናግሯል።

ሚኒስትሩ አክለውም የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬንን ይወራሉ ለማለት "አሳማኝ እና ትክክለኛ ምክንያት" አለ ብለዋል።

ሩሲያ ግን ጎረቤቷን ዩክሬንን የመውረር ዕቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን ይህንን የምዕራባውያንን ክስ ውድቅ ታደርጋለች።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2015 ጀምሮ በርካታ የብሪታኒያ ወታደሮች የዩክሬን ጦርን ለማሰልጠን በሃገሪቱ ይገኛሉ። እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን መውረሯን ተከትሎ ዩኬ የዩክሬን የባህር ኃይልን መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ እንደምትረዳት ቃል ገበታለች።

ሚኒስትሩ ዋላስ የዩኬ እርዳታ በዚህ ብቻ ላይገታ እንደሚችል ጠቅሰዋል። ከሩሲያ "እየጨመረ ካለው አስጊ እንቅስቃሴ" አንጻር ዩኬ ደህንነትን የተመለከቱ ተጨማሪ እርዳታ እንደምትሰጥ አስረድተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ የመሰሪያውን አይነት ባይገልጹም በመጀመሪያው ዙር ቀላል መሰሪያ ሰኞ ዕለት ለዩክሬን መላኩን ጨምረው ገልጸዋል።

"ዩክሬን ድንበሯን የመጠበቅ ሙሉ መብት አላት። እናም ይህ አዲስ የእርዳታ ማዕቀፍ ይህን መብቷን ለማጠናከር አቅም ይሰጣታል" ሲሉ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም መሳሪያዎቹ ስልታዊ የሚባሉ እና ለሩሲያ ስጋት የሚሆኑ አይደሉም ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ ማንኛውንም "አደጋ የሚፈጥር እርምጃ" ከወሰደች " ለመከላከል ዝግጁ የሆነ የአለም አቀፍ ማዕቀብ አለ" ሲሉ ገልጸዋል።

በዲፕሎማሲው አሁንም ቢሆን ተስፋ አለኝ ያሉት ሚኒስትሩ ለዘመናት የሩሲያ ወዳጅ እንደነበርን ሁሉ እንደዛው መቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል።

በዩኬ የሚገኙት የዩክሬን አምባሳደር ብሪታኒያ የጦር መሳሪያ እና ተጨማሪ ወታደር ለመላክ መወሰኗን የሚደነቅ ነው ብለዋል። ሆኖም መሰረታዊው ችግር ዩክሬን የኔቶ አባል አለመሆኗ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተኩስ ማቆም ስምምነት ተደርጓል ቢባልም እንደ አውሮፓውያኑ ከ2014 ጀምሮ በምስራቅ ዩክሬን በሩሲያ በሚደገፉ ተገንጣዮች እና በዩክሬን ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

የምዕራባውያን እና የዩክሬን የስለላ ተቋማት በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ ላይ ድንበር አቅራቢያ የሰፈረው የሩሲያ ጦር ወረራር ሊፈጽም እንደሚችል አመላክተዋል።

ሩሲያ በበኩሏ የኔቶ ጦርን እንቅስቃሴ ለመከላከል በአከባቢው ወታደሯቸውን ማስፈሯን ትናገራለች።