የሕንድ መንግሥት ለማዘር ትሬዛ ፋውንዴሽን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፎችን ከለከለ

የማዘር ትሬዛ በጎ አድራጎት ድርጅት ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰብአዊ ሥራዎቻቸው በሚታወቁት እማሆይ ትሬዛ ከ72 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የበጎ አድራጎት ድርጅትን ለመርዳት ከውጭ አገራት የሚገኙ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪዎችን ፈቃድ ማደስ ማቆሙን የሕንድ መንግሥት አስታወቀ።

የበጎ አድራጎት ተቋሙ በሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳት የያዘ ሲሆን መነኮሳቱ አሳዳጊ የሌላቸውን ልጆች፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን እና ሆስፒታሎችን ይቆጣጠራሉ።

በገና በዓል ቀንም የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር "በአሉታዊ ግብአቶች" አማካኝነት ፈቃዱን ማደስ ማቆሙን አስታውቋል።

የሂንዱ አክራሪዎች ተቋሙ የበጎ አድራጎት ፕሮግራሞቹን በመጠቀም ሰዎችን ወደ ክርስትና ሐይማኖት ለመቀየር ይሰራል የሚሉ ክሶችን ለረዥም ጊዜ ሲያቀርቡ ሲያቀርቡና ተቋሙ ይህንን ሲያስተባብል ቆይቷል።

ትላንት ሰኞ "ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ" የትኛውንም አይነት ከውጭ አገር የሚገኝ የፋይናንስ ድጋፍ እንደማያስተዳድር ተቋሙ ይፋ አድርጓል።

ቀደም ብሎም የምዕራባዊ ቤንጋል ሚኒስትር የሆኑት ማማታ ባንሬጄ በትዊተር ገጻቸው መንግሥት የእማሆይ ትሬዛን ፋውንዴሽን የባንክ አካውንት ማገዱን መግለጻቸው ከፍተኛ ትችትን አስከትሎ ነበር። ነገር ግን መንግሥት የባንክ አካውንቱ አልታገደም ሲል አስተባብሏል።

የሮማን ካቶሊክ መነኩሴዋ እማሆይ ትሬዛ ከአገራቸው መቄዶኒያ ኑሯቸውን ወደ ሕንድ በማድረግ ነበር ይህንን በመላው ዓለም ከፍተኛ ድጋፍን ያተረፈውን የበገ አድራጎት ተቋም የመሰረቱት።

እማሆይ ትሬዛ እ.ኤ.አ. በ 1979 ላበረከቱት የሰብአዊነት ሥራ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተቀብለዋል።

እንዲሁም ሕይወታቸው ካለፈ ከ19 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2016 በፖፕ ፍራንሲስ አማካኝነት ቅድስትነታቸው ታውጇል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ናሬንድራ ሞዲ የሚመራው የሕንድ መንግሥት የሌሎች የሲቪል ማኅበራት እና የበጎ አድራጎት ተቋማትን ከውጭ አገራት የሚገኙ የገንዘብ ድጋፎችን ለማስቆም ፍላጎት ነበረው።

ባለፈው ዓመትም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የግሪን ፒስን የባንክ አካውንቶችን መንግሥት አግዶ ነበር።

እንዲሁም በማው ሕንድ በሚገኙ አናሳ ቁጥር ያላቸው ሐይማኖቶች ተከታዮች ላይ በርካታ ጥቃቶች ተቃጥተው ነበር።

እንደ የሕንድ የኢቫንጀሊካል ሕብረት ከሆነ በደቡባዊ ካራንአታካ ውስጥ ብቻ 40 የጥቃት ዛቻ እና ማስፈራሪያዎች ደርሰዋል።

እንዲሁም ባለፈው ቅዳሜ ተከብሮ የዋለውን የገና በዓል ሕገወጥ የሂንዱ ቡድኖች በሰሜናዊ ሕንድ ቤተክርሰቲያኖችን በማፍረስ እንዲሁም ለበዓሉ ወደ ተደረጉ ስብሰባዎች በመሄድ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ነውጥ መፍጠራቸው ተዘግቧል።

በሕንድ አብዛኛው ዜጋ የሂንዱ እምነት ተከታይ ቢሆንም ከ 24 ሚሊዮን በላይ የክትስትና እምነት ተከታይ ይገኛል። ይህም ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሩ የሁለት በመቶ ድርሻ አለው።

ባለሥጣናት ሰዎችን ከሂንዱ ወደ ክርስትና እና ወደ እስልምና ለመቀየር የሚደረጉ ዘመቻዎችን ለማስቆም አቅደው መንቀሳቀሳቸውም ይነገራል። በርካታ ክልሎችም ለጋብቻ ተብለው የሚደረጉ የሐይማኖት ለውጥን የሚከለክል ሕግ ለማውጣት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።