በድጋሚ በወጣው የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዕጣ ፒኤስጂ እና ማድሪድ ተገናኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ዕጣ አወጣት በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጎ የአምናው አሸናፊ ቼልሲ ከፈረንሳዩ ክለብ ሊል ይጫወታል።
"የቴክኒክ ችግር" በመጀመርያው የዕጣ አወጣጥ ውጤት ላይ ስህተት በመፍጠሩ "ተሰርዟል" ብሏል የአውሮፓ እግር ኳስ የበላይ አካል ዩኤፋ።
የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ ከፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ሲጫወት የስድስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሊቨርፑል ከሦስት ጊዜ አሸናፊው ኢንተር ሚላን ጋር ይጋጠማል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከስፔኑን ሻምፒዮን አትሌቲኮ ማድሪድን የሚጫወት ይሆናል።
ከፍተኛ ግምት በተሰጠው ድልድል የ13 ጊዜ ሻምፒዮኑ ሪያል ማድሪድን ከፈረንሳዩ ሃያል ክለብ ፓሪስ ሴን ዠርመን ጋር ይፋለማል።
የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ደድልድል
- ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ከባየር ሙኒክ
- ስፖርቲንግ ሊዝበን ከማንቸስተር ሲቲ
- ቤንፊካ ከአያክስ
- ቼልሲ ከሊል
- አትሌቲኮ ማድሪድ ከማንቸስተር ዩናይትድ
- ቪያሪያል ከጁቬንቱስ
- ኢንተር ሚላን ከሊቨርፑል
- ፒኤስጂ ከሪያል ማድሪድ
ዕጣው እንደገና እንዲወጣ ለምን ተደረገ?
በመጀመሪያው ዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓት የማንቸስተር ዩናይትድ ስም ከቪያሪል ጋር ወጣ። ሁለቱ በምድብ ጨዋታ ወቅት በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ ስለነበሩ ለመፋለም ሕጉ አይፈቅድላቸውም።
የአውሮፓ የእግር ኳስ የበላይ አካል ዩኤፋ ቴክኖሎጂው ይህ እንዳይፈጠር መከላከል ነበረበት ብሏል።
ያለፈው የውድድር ዘመን የዩሮፓ ሊግ አሸናፊው ቪያሪያል በምትኩ ከፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ ጋር እንዲጫወት ዕጣ ደረሰው።
ሌላ ውዥንበር ደግሞ ተከሰተ። ዩናይትድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ከሚጫወቱ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ወጥቶ በቦታው ሊቨርፑል ተተካ።
ዩናይትድ ከስፔኑ ቡድን ጋር የመጫወት እድል የነበረው ሲሆን በተቃራኒው በተመሳሳይ ምድብ አብረው የነበሩት ሊቨርፑልና አትሌቲኮ መጋጠም አይችሉም።
አውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር "የትኞቹ ቡድኖች እርስበርስ መጫወት እንደሚችሉ መመሪያ የሚሰጠው የውጭ አገልግሎት አቅራቢ ሶፍትዌር ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የዕጣ ድልድል ላይ ስህተት ተፈጥሯል" ብሏል።
"በዚህም ምክንያት የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓቱ ተሰርዞ በድጋሚ ይከናወናል" ብሏል።
በተሰረዘው ዕጣ ድልድል መሰረት ቤነፊካ ከሪያል ማድሪድ፣ ቪያሪያል ከማንቸስተር ሲቲ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ከባር ሙኒክ፣ ኤፍ ሲ ሳልስቡርግ ከሊቨርፑል፣ ኢንተር ሚላን ከአያክስ፣ ስፖርቲንግ ከዩቬንቱስ፣ ቼልሲ ከሊል እና ፓሪሰንዠርመ ከማንቸስተር ዩናይትድ ተገናኝተው ነበር።
ቼልሲ የመጀመሪያውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በሜዳው የሚያደርግ ብቸኛው የእንግሊዝ ቡድን ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት ቡድኖች ምድባቸውን በአንደኛነት በማጠናቀቃቸው ከሜዳቸው ውጪ በመጫወት ይጀምራሉ።
በዚህ የውድድር ዘመን ትልቅ ለውጥ የተደረገው ከሜዳ ውጪ ብዙ ጎል ያገባ ያልፋል የሚለው ሕግ እንዲቀር ተደርጓል። ሁለት ቡድኖች በ180 ደቂቃ አቻ ከሆኑ ወደ ተጨማሪ ሰዓት ያመራሉ።
ቡድኖቹ በተጨማሪ 30 ደቂቃዎች በጎል መለያየት ካልቻሉ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ይሸጋገራሉ።
የዘንድሮው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ግንቦት 28 በሴንት ፒተርስበርግ ሩሲያ ይካሄዳል።












