የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለሚያቀርበው ድጋፍ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው ገለጸ

የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ለሚያቀርበው ድጋፍ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት እንዳጋጠመው ገለጸ።

ይህ የገንዘብ ችግር ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎችና ስደተኞች የምግብ ድጋፍ እንዲሁም አልሚ ምግቦች ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በሚያቀርበው ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነት እና በዝናብ እጥረት ምክንያት ሰብአዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ሲሆን፤ በተጨማሪ ደግሞ ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞችም እርዳታን ይሻሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የተለያዩ ድጋፎች ለሚያስፈልጋቸው 12 ሚሊዮን ሰዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ የ579 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ጉድለት አጋጥሞታል።

ይህም በሰሜን ኢትዮጵያ ለ3.7 ሚሊዮን ሰዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአስቸኳይ ለሚያቀርባቸው የምግብና የአልሚ ምግቦች የሚውለውን 316 ሚሊዮን ዶላር ይጨምራል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ስቴቨን ዌሬ ኦማሞ "በአገሪቱ ውስጥ የምግብ አቅርቦት አለ። ነገር ግን በሚቀጥሉት ሳምንታት የገንዘብ ድጋፍ ካልተነኘ፣ ያለውን ምግብ በመግዛት ወደሚፈለግበት ቦታ ማቀረብ ካልተቻለ ከጥቂት ወራት በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከባድ ረሃብና ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ" ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ጨምረውም በበርካታ ክልሎች ውስጥ በግጭት ምክንያት ለችግር ከተጋለጡት በተጨማሪ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡት የቆላማ አካባቢዎች ነዋሪዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ ላይ በሰሜን፣ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጥረት ሊከሰት እንደሚችል በቅርቡ የወጣ ግምገማ ማመልከቱን ድርጅቱ ጠቅሷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙት የአፋር፣ የአማራና የትግራይ ክልሎች ውስጥ ያለው የምግብ ዋስትና ሁኔታ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በግጭቱ ሳቢያ የእርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎል ከቀጠለ ወደ አስከፊ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል ብሏል።

በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢ በተከታታይ የሚጠበቀውን ያህል ዝናብ ባለመጣሉ ሳቢያ የተጠናከረ ድርቅ ተከስቶ በከብቶች ላይ ከባድ ጉዳት በማድረሱ በአካባቢዎቹ የተከሰተው የምግብ ዋስትና ችግር ለተከታታይ ወራት እንደሚቀጥል አመልክቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያከናውነው ተግባር ዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፋቸውን ቢያጠናክሩም ካለው ፍላጎት ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ ድርጅቱ አመልክቷል።

ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያትም የምግብ ዋስትና ችግር ለገጠማቸው 2.4 ሚሊዮን በሶማሌ ክልል ለሚገኙ ሰዎችና በመላው አገሪቱ ለሚገኙ 710 ሺህ ለሚሆኑ ስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ ቀንሷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን ያስታወቀው ከአንድ ሳምንት በፊት ነበረ።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ቶምሰን ፊሪ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብለዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየው በአማራ ክልል መሆኑን ድርጅቱ አመልክቶ፤ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር የተሰበሰቡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በሦስቱ ክልሎች ከሚገኙ ሕጻናት መካከል ከ16 እስከ 18 በመቶ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ነፍሰ ጡር ከሆኑ እና ከሚያጠቡ እናቶች መካከል 50 በመቶ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው መለየቱን እና ይህም የመንግሥታቱን ድርጅት በእጅጉ እንዳሰሰበው አመልክቷል።