ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ለወራት የቆየው የብድር እቀባ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ምን ውጤት ነበረው?
ላለፉት አራት ወራት ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው የብድር ክልከላ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ሳምንት አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ ኅዳር 20/2014 ዓ.ም ባንኮች የብድር አገልግሎት ለሁሉም ደንበኞቻቸው እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የብድር ክልከላው 'የምጣኔ ሀብትን አሻጥር' ለመከላከል በማለምና በጥቁር ገበያና በመደበኛ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት መስፋቱን ተከትሎ የተጣለው ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር።
ለመሆኑ ይህ ለወራት የቆየ የብድር እቀባ ምጣኔ ሀብቱን እንዴት ጎድቶታል?
"ብድር የምጣኔ ሀብት ሞተር ነው" የሚሉት በኩዌት የሳይንስና ምርምር ተቋም የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶ/ር አየለ ገላን እቀባው ቀድሞውኑም መጣል አልነበረበትም ይላሉ።
ተመራማሪው እንደሚሉት "ከአገር ደኅንነትና ሕገ ወጥ ገንዘብን ለመቆጣጠር ጭራሽኑ ገንዘብ ምጣኔ ሀብቱ ውስጥ አይግባ፤ ከምንጩ እናድርቀው ማለት አግባብ አይደለም" ብለዋል።
ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎችም ብሔራዊ ባንክ በአብዛኛው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ምንን መሠረት እንደሚያደርጉ ግልጽ አለመሆኑን በማንሳት ውሳኔዎቹ ውጤት አስገኝተዋል፤ አላስገኙም ለማለት እንደሚያስቸግር ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ባለበት አገር ባንኮች መሠረታዊ ሥራቸውን እንዳይሠሩ ማገድ ምጣኔ ሀብቱን እንዲቆም ማድረግ ነው ይላሉ።
ባለሙያዎቹ እያንዳንዱ የሚዘዋወረው ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በብድር መልክ ከባንክ የሚመጣ ነው በማለትም እቀባው በተጣለባቸው ጊዜያት "ብዙ ነገር ጠፍቷል" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት ዶ/ር አየለም በምጣኔ ሀብቱ ላይ ጠቅላላ ጉዳት የሚያመጣ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ቁጥጥሩን ማጥበቅ ይቻል ነበር ብለዋል።
"ብድር አይነኬ መሆን አለበት፤ ብድር ማቆም ማለት የአንድን ሰው የደም ዝውውርን እንደማቆም ነው" ብለዋል ተመራማሪው።
የብድር ክልከላው በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት እንዴት ይገለጻል? በሚል ለቀረበለቸው ጥያቄም ዶ/ር አየለ "ምጣኔ ሀብቱን ካለበት ወደ ኋላ የመለሰ፣ በምንም መለኪያ የማይገለጽ አጠቃላይ ውድቀት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
የብድር አገልግሎት ሳይከለከልም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ችግር እንደነበረበት ያስታወሱት ተመራማሪው፤ እቀባው መጣሉ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር መሆኑን አስረድተዋል።
ተጥሎ የነበረው የብድር እቀባ ምን የሚል ነበር?
ነሐሴ ወር ላይ በብሔራዊ ባንክ ተላልፎ የነበረው የብድር ክልከላ ባንኮች ሕንጻ፣ መሬትና ቤቶችን መያዣ በማድረግ የሚሰጡ ብድሮችን በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ ያዛል።
ከማስያዣ ውጭ የሚሰጡና ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ የብድር ዓይነቶችም ተቋርጠው ነበር።
ይሁን እንጂ እቀባው በሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚሰጥን ብድር የሚከለክል አልነበረም።
በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔው የተላለፈው "በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ እየታየ ያለውን አሻጥር" ለመቆጣጠር በማሰብ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ብሔራዊ ባንኩ ባለፍነው መስከረም ወር ላይ ባስተላለፈው የብድር ክልከላ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ባንኮች አምስት የብድር ዓይነቶችን መፍቀድ እንደሚችሉ አስታውቆ ነበር።
ከእነዚህም መካከል ባንኮች የሰጡትን ብድር ለማስመለስ በሐራጅ ያወጧቸውን ንብረቶች ለመግዛት ለሚጠይቁ ገዥዎች፣ ባንኩ ብድር መውሰድ ያስችላሉ ያላቸው በሁለተኛ እና ሦስተኛ ወገኖች መካከል የሚደረግ ግብይትና ለባንክ ሠራተኞች የሚሰጥ አስቸኳይ ብድር ይገኙበታል።
ከዚህም ባሻገር በጎንደር አካባቢ ለሚገኙ ሰሊጥ አምራቾች የፀደቀ የብድር ዓይነት እንዲለቀቅም ባንኩ ባወጣው ማሻሻያ መገለፁ ተዘግቧል።
የብድር ክልከላው መነሳቱ ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን?
ብዙ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ መሠል ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ መነሻው እንደማይታወቅና ለውይይትም ክፍት አለመሆኑን የሚያስታውሱት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ እቀባው መነሳቱ ምን አስገኘ የሚለውን ለመናገር መጀመሪያ የተፈለገው ምን እንደሆነ መታወቅ እንዳለበት ይናገራሉ።
"በመሆኑም በውሳኔው ምን እንደተገኘ ሊያብራራ የሚችለው ብሔራዊ ባንክ ነው" ይላሉ።
ብሔራዊ ባንክ የብድር ክልከላው መነሳቱን ከመግለፅ ያለፈ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ የለም።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለበርካቶች መተዳደሪያ ነው። ባንኮችም ብድር በመስጠት ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ። ሌሎችም ብድርን የተንተራሱ በርካታ ዘርፎች አሉ።
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የበርካቶች መተዳደሪያ እንደሆነ እንደ አብነት በመጥቀስ፤ እቀባው መነሳቱ ይህን ዘርፍ እንዲያንሰራራ ያደርገው ይሆን? ተብለው የተጠየቁት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዶ/ር አየለ፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉም ሆነ ሌላው ከባንክ ከሚገኝ ብድርና ራሱ ካለው ጋር አዋህዶ ነው የሚንቀሳቀሰው ይላሉ።
ነገር ግን የኮንስትራክሽን ዘርፉ ብዙ ሰዎችን ቢቀጥርም፤ እርሱን "እንደ ኢኮኖሚ ሞተር" አድርጎ መውሰድ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
"ትልቁ የኢኮኖሚ በሽታ ኮንስትራክሽንን እንደ ኢኮኖሚ ሞተር ማሰብ ነው" ይላሉ ዶ/ር አየለ።
ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ የኮንስትራክሽን ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወሱት ተመራማሪው፤ ይህ ግን የኢኮኖሚ መረጋጋትን እንዳላመጣና የኑሮ ውድነትን እንዳልቀነሰም ያስረዳሉ።
በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ ለኮንስትራክሽን የሚሰጠውን ብድር ቀንሶ ወደ ግብርና ወይም ጥቃቅን ኢንደስትሪዎች እንዲዞር ማድረግ አለበት ሲሉም ይመክራሉ።
"ብድር ለእንስሳት እርባታ፣ ለፍራፍሬ ምርት፣ ለወተት፣ ለአልባሳት ምርት እና ምርት ለሚገኝባቸው ዘርፎች ቢዛወር፤ ከባንክ የተሰጠው ብድር ወደ ዋጋ ግሽበት (ኢንፍሌሽን) ሳይሆን የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ያደርግ ነበር" ብለዋል ዶ/ር አየለ።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፈው ዓመት በ2020 ከነበረበት 6 በመቶ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በ2021 ሁለት በመቶ ብቻ እንደሚያድግ ተገምቷል።
ይህም በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከታየው በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርክት (አይኤምኤፍ) መረጃ አሳይቷል።
አገሪቱ በዓመት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እቃዎችን ከውጭ የምታስገባ ሲሆን ወደ ውጪ የምትልከው 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የሚያወጡ ምርቶችን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ በዚህ ዓመት 60 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 70 በመቶ ይደርሳል ተብሏል። በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም "ይህ የሚያሳስብ ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል ማገዷ፣ የአበዳሪዎች ብድር ለመስጠት ማቅማማት እንዲሁም በጦርነቱ ሳቢያ የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል በምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።