ከጉግል የተባረረችው ትምኒት ገብሩ ለፍትሐዊ ቴክኖሎጂ የሚታገል ተቋም መሠረተች

የሰው ሠራሽ ልኅቀት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ባለሙያዋ ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) ገለልተኛ የሰው ሠራሽ ልኅቀት የምርመር ተቋም መሠረተች።

የሰው ሠራሽ ልኅቀት ባለሙያዋ ትምኒት ለቢቢሲ እንደገለጸችው፤ ይህ ተቋም በሰው ሠራሽ ልኅቀት ዘርፍ አማራጭ የጥናት መስመር ይከፍታል ብላ ተስፋ ታደርጋለች።

አሁን ላይ በዘርፉ ምርምር የሚደረገው በትምህርት ቤቶች እና በግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ውስጥ ነው።

"የትምህርት ተቋማት ለተመራማሪዎች ዝግ ናቸው። ማጭበርበር እና ብዝበዛ የሞላባቸው ናቸው" ትላለች ትምኒት።

ተቋማቱ ሥልጣን ላይ ያሉ አካላትን ለማስደሰት ስለሚሠሩ፤ አማራጭ ድምጾችን እና ለየት ያሉ አስተሳሰቦችን የመጨፍለቅ አዝማሚያ እንደሚያሳዩም ታክላለች።

ሌላው ምርምር የሚደረግባቸው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ አፋኝ እንደሆኑ ባለሙያዋ ታስረዳለች።

እሷ ከጉግል ጋር የገባችበትን ቅራኔ በማስታወስ "ግዙፍ ተቋማት እንደ እኔ ያሉ ባለሙያዎችን የሚገፋ አሠራር ዘርግተዋል" ትላለች።

በሌላ በኩል መንግሥታትም ቢሆኑ የሰው ሠራሽ ልኅቀት ምርምርን የሚደግፉት ከወታደራዊ መሣሪያዎች ጋር በተያያዙ ጥናቶች ዙርያ ብቻ መሆኑን ትተቻለች።

"ተቋሙ ለአማራጭ ሐሳቦች ቦታ በመስጠት ለሌሎችም ተመሳሳይ ተቋሞች መነሻ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ስትልም ለቢቢሲ አስተያየቷን ሰጥታለች።

ፍትሐዊ ቴክኖሎጂ እንዲሰፍን በመታገል የምትታወቀው ትምኒት ገብሩ የመሠረተችው አዲስ ተቋም፤ መገለል የሚደርስባቸው ቡድኖች ላይ በቴክኖሎጂ አማካይነት የሚከሰተውን ተጨማሪ ጭቆና ለመግታት እንደሚሠራ ጠቁማለች።

ባለሙያዋ አምና ከጉግል መባረሯ ይታወሳል። በጉግል የሰው ሠራሽ ልኅቀት የሥነ ምግባር ክፍል ትሠራ የነበረችው ትምኒት፤ ከጉግል መባረሯ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለሙያዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ትምኒት ያቋቋመችው ገለልተኛ የሰው ሠራሽ ልኅቀት ምርምር ተቋም Distributed Artificial Intelligence Research Institute (DAIR) ይባላል።

የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሰው ሠራሽ ልኅቀት የሚገጥማቸውን ችግር የሚያጠና እንዲሁም ለለውጥ ንቅናቄ የሚያደርግ ተቋም ነው።

ጥቁር እና ቡናማ ሕዝቦች፣ ሴቶች፣ ዐቅመ ደካሞች በሰው ሠራሽ ልኅቀት ብሎም በሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶችም መገለል ይገጥማቸዋል።

በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚገጥማቸው ማኅበረሰባዊ ጫና በሰው ሠራሽ ልኅቀት አማካይነት እንዳይጎላ ትምኒት እና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ይታገላሉ።

ትምኒት ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ አዲሱ ተቋም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ ይሆናል። አሁን ላይ ዋነኛ ትኩረቱ በአፍሪካ እና በአሜሪካ ላይ ነው።

አሁን ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ አራት ባለሙያዎች ሁለቱ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ሁለቱ ደግሞ ከአሜሪካ ናቸው።

"ከተለያየ ቦታ የመጡ ሰዎች እንዲህ በአንድነት መሥራታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል። አእምሯዊ ጫናንም ይቀንሳል" ትላለች።

ተቋሙ ከማክአርተር ፋውንዴሽን፣ ፎርድ ፋውንዴሽን፣ ካፖር ሴንተር፣ ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን እና ሮክፌለር ፋውንዴሽን በተገኘ የ3.7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ነው የተቋቋመው።

ጉግል እየሰጠ ያለው አገልግሎት ከቴክኖሎጂ ሥነ ምግባር አንጻር ያለበትን ክፍተት በመንቀፏ ነበር ትምኒት ከሥራ የተባረረችው።

ጉግልን ጨምሮ ሌሎችም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች በአጠቃላይ ለተጠቃሚዎቻቸው፣ በዋነኛነት ደግሞ መገለል ለሚደርስባቸው ማኅበረሰቦች የሚሰጡት አግልግሎት ፍትሐዊነት እንደሚጎድለው ይተቻሉ።

ትምኒት ከዚህ ቀደም የሠራችው ጥናት ለዚህ ማሳያ ነው። የሰዎችን ገጽታ በማየት ማንነታቸውን የሚለየው መሣሪያ (ፌሻል ሪኮግኒሽን ሲስተም) የጥቁር ሴቶችን ምስል ተመልክቶ ማንነታቸውን መለየት የሚችልበት ዕድል ውስን እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።

መሣሪያው የሠለጠነው በዋነኛነት በነጭ ወንዶች ምስል መሆኑ ነበር ክፍተቱን የፈጠረው።

አዲሱ የትምኒት ተቋም እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን አርሞ በቴክኖሎጂው ፍትሐዊነትን ለማስፈን እንደሚሠራ የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ገለልተኛ ተቋሙ በሚሠራቸው ጥናቶች እንደ ጉግል ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች አሠራርን እና ሰው ሠራሽ ልኅቀት ተኮር ፖሊሲዎችን እንደሚያስተካክልም ይጠበቃል።

በተቋሙ የሚሠሩ ጥናቶች፤ በሰው ሠራሽ ልኅቀት ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ማኅበረሰቦች የሚጋሩ እንጂ በቴክኖሎጂ ተቋሞች ዘንድ ብቻ የሚቀሩ እንደማይሆኑም ተጠቁሟል።