ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴክኖሎጂ ፡ ከጉግል ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያዊት ትምኒት ገብሩ ማናት?
የአዲስ አበባ ልጅ ናት። ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር)።
ዓለምን በፍጥነት እየለወጠ ያለው ሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ኤአይ) ውስጥ አሉ ከሚባሉ ጥቁር ሴት ባለሙያዎች መካከል አንዷ ነች።
ትምኒት፤ ጉግል ውስጥ የኤአይ የሥነ ምግባር ዘርፍ ባልደረባ ነበረች። ቴክኖሎጂው አካታች እና ፍትሐዊ እንዲሆን ከሚጥሩ መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።
ባለፈው ሳምንት ከጉግል አመራሮች ጋር በተፈጠረ ውዝግብ ከሥራዋ መባረሯ በርካታ የዘርፉ ሙያተኞችን አስቆጥቷል።
ትምኒት አዲስ አበባ ሳለች. . .
የናዝሬት ስኩል ተማሪ ነበረች። አስረኛ ክፍል ስትደርስ ወደ አየርላንድ አቀናች። የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው አሜሪካ ነው።
ለቤተሰቧ የመጨረሻ ልጅ ናት።
ከሁለት ዓመት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ ልጅነቷን ስታስታውስ "ሕጻን ሳለሁ ትምህርት እወድ ነበር። ስታመም ራሱ ከትምህርት ቤት መቅረት አልወድም ነበር" በማለት ነው።
በተለይም ለሒሳብ እና ፊዚክስ ልዩ ፍቅር ነበራት።
አባቷ ኤሌክትሪካል መሀንዲስ መሆናቸው ወደ ሳይንስ እንድታዘነብል እንዳደረጋት ትናገራለች። ሁለት ታላላቅ እህቶቿም በዚሁ የሙያ ዘርፍ ነው የተሰማሩት።
ትምኒት በአሜሪካ. . .
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ገባች።
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዋን የሠራችው በኤሌክትሪካል ምህንድስና ነው።
በዓለማችን ስመጥር ከሆኑት መካከል በሚጠቀሱት አፕል፣ ከዚያም ጉግል ውስጥ ሠርታለች።
ትምኒት በግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ውስጥ ፍትሐዊነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ቡድን ውስጥ ሠርታለች።
በሰው ሠራሽ ልህቀት ዘርፍ የጥቁር ሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ 'ብላክ ኢን ኤአይ' የተባለ ተቋምን ከመሠረቱ መካከል አንዷ ናት።
የፈጠራ ሥራዎችን አካታችነት በሚፈትሹ ጥናቶቿ እንዲሁም ቴክኖሎጂና የሰብአዊ መብት ጥያቄን በማስተሳሰርም ትታወቃለች።
ብላክ ኢን ኤአይ፤ ጥቁር ሴቶች ወደ ሰው ሠራሽ ልህቀት ዘርፍ እንዲገቡ፣ በሙያው የተሰማሩ እርስ በእርስ እንዲደጋገፉና ተደማጭነት እንዲያገኙ ለማስቻል ነው የተቋቋመው።
ትምኒት እንደምትለው፤ ስብስቡ ጥቁር ሴቶችን የሚያበረታታ፣ ወደላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያስችልም ነው።
ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ "ከዚህ ሙያ ልወጣ ነበር፤ ወደ እናንተ ተቋም ከመጣሁ በኋላ ግን ጥናት መስራት ጀምሬያለሁ ብለው ኢሜል ያደርጉልናል። ሥራ ያገኙ፤ ማስተርስና ፒኤችዲ ማጥናት የጀመሩም አሉ። በእኛ ወርክሾፕ ተገናኝተው በጥምረት መስራት የጀመሩም አሉ" ስትል ነበር ብላክ ኢን ኤአይ ያለውን ሚና የገለጸችው።
ለብላክ ኢን ኤአይ መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ መካከል ኢትዮጵያዊቷ ረድኤት አበበ ትገኝበታለች።
የኮምፒውተር ሳይንቲስቷ ረድኤት፤ በአልጎሪዝም እና ኤአይ ዙርያ ትሠራለች። ከኮርኔል ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ፒኤችዲ [ዶክትሬት] በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ናት።
በዘርፉ ያሉ ጥቁሮች፣ በተለይም ደግሞ ጥቁር ሴቶች ውስን እንደሆኑ የምታስረዳው ትምኒት፤ አብዛኞቹ ጥናቶቿ የፆታና የዘር አካታችነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
የትምኒት ጥናቶች
ከትምኒት ታዋቂ ጥናቶች መካከል ፌሻል ሪኮግኒሽን ሲስተም ወይም የሰዎችን ፊት ገጽታ በማየት ማንነታቸውን የሚያሳውቅ መተግበሪያን በተመለከተ የሠራችው ይጠቀሳል።
መተግበሪያው የጥቁር ሰዎችን በተለይም ደግሞ የጥቁር ሴቶች ገጽታ አይቶ ማንነታቸውን ለመለየት እንዲችል ተደርጎ አለመሠራቱን ጥናቱ ይጠቁማል።
ትምኒት እንደምትናገረው፤ ጥናቱን የጀመረችው ኤምአይቲ ከምትሰራ ጓደኛዋ ጋር ነው።
"ጓደኛዬ ጥቁር ሴት ነች። ለአንድ ፕሮጀክት 'ፌስ ሪኮግኒሽን' ስትጠቀም ፊቷን 'ዲቴክት' ማድረግ [ማንበብ] አልቻለም። እንደሌለች ነው የሚቆጥራት። ነጭ 'ማስክ' [ጭንብል] ፊቷ ላይ ስታደርግ ግን ያነባል" በማለት የጥናቱን መነሻ አጋጣሚን ታስታውሳለች።
'ፌስ ሪኮግኒሽን' ነጮችና ጥቁሮች ላይ እኩል እንደማይሠራና በተለይ ደግሞ ጠቆር ያሉ ሴቶች በአግባቡ ማንበብ ወይም ማወቅ እንደሚሳነው ጥናታቸው ያመለክታል።
እንዲህ አይነት ዘረኛ እና ፆተኛ መድልዎ በብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ እንደሚስተዋል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ትምኒት ከምታደንቃቸው መጽሐፎች አንዱ በሆነው 'ዌፐንስ ኦፍ ማት ዲስታራክሽን' ላይ ስለመድልዎ በዝርዝር ተጽፏል።
ጸሐፊዋ ካቲ ኦኒል ሰው ሠራሽ ልህቀት አካታች አይደለም ስትል ትተቻለች። ዘር፣ ፆታ፣ ቀለምና መደብን መሠረት ያደረገ መድልዎን ማስወገድ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ዘርፉን የበለጠ አካታች ማድረግ እንደሆነ ካቲ ትጠቁማለች።
ሰዎች እነሱን የሚመስል ሰው የሚያካትት ወይም እነሱን ለሚመስል ሰው ጥቅም የሚሰጥ ቴክኖሎጂ መፍጠር የሚችሉት በዘርፉ ሲሰማሩ መሆኑን ትምኒት፣ ካቲና ሌሎችም ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
'ዳታ አክቲቪዝም'
ትምኒት፤ ከበይነ መረብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙርያ ንቅናቄ ከሚያደርጉ የመብት ተሟጋቾች (ዳታ አክቲቪስትስ) አንዷ ነች።
እነዚህ የመብት ተሟጋቾች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምን ያህል አካታች ናቸው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ክፍተት ሲያገኙም ከግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ሳይቀር ይፋለማሉ።
ለትምኒት ቴክኖሎጂ ከመብት ሙግት ጋር የተያያዘ ነው።
"ለአብዛኛው ሰው የማይሠራ ቴክኖሎጂ ከተሠራ ለሰው የማይሆን ነገር እየተሠራ ነው ማለት ነው" የምትለው ባለሙያዋ፤ አፍሪካውያን ሴቶች ለራሳቸው የሚሆን ነገር እንዲሠራ ቴክኖሎጂ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ታሳስባለች።
እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው የዘረ መል ቅንጣት ላይ የተሠሩ እንዲሁም ለተለያዩ ህመሞች የሚቀመሙ መድኃኒቶችን ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ከአፍሪካውያን ወይም ከጥቁሮች ናሙና እንደማይወሰድ፣ ቢወሰድም የናሙናው መጠን ውስን እንደሚሆን በማስረጃነት ትጠቅሳለች።
ለዚህም ነው ትምኒት ቴክኖሎጂ ከሰብአዊ መብት ትገል ጋር ጎን ለጎን እንደሚሄድ የምትናገረው።
ትምኒት፤ ቴክኖሎጂ አካታችና ፍትሐዊ እስከሆነና ለበጎ አላማ እስከዋለ ድረስ መጪው ዓለም ብሩህ የመሆን እድሉ ሰፊ እንደሆነ ከሚያምኑ ባለሙያዎች አንዷ ናት።
በእሷ ዕይታ፤ አፍሪካ ውስጥ የድሮን ጥናት የሚሠሩ ጀማሪዎች በመኖራቸው መንገድ ሳያስፈልግ በድሮን መድኃኒት ማዳረስ ይቻል ይሆናል። ትልልቅ ሆስፒታል መሥራት ሊቀር፣ ምናልባትም በትንንሽ መሣሪያ ሕክምና መስጠት ይቻል ይሆናል። ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ መኪኖች ሲበራከቱ አይነ ስውራን በራሳቸው ይንቀሳቀሱም ይሆናል።
ትምኒት፤ "ጥያቄው ግን እንዴት አድርገን ነው ቴክኖሎጂን የምንጠቀመው የሚል ነው? ብዙ ጦርነት ይኖራል? ኢ-ፍትሐዊነት ይኖራል? ምን አይነት ፖለቲካዊ ሁኔታ ይኖረናል? በጣም ጥቂት ሰዎች ብዙ ገንዘብ ኖሯቸው ብዙዎች ገንዘብ ከሌላቸው 'አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ' ነገሩን ያባብሰዋል" ትላለች።
የትምኒት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት
ኢትዮጵያ ውስጥ ለወጣቶችን የኮዲንግ ሥልጠና የተሰጠበት 'አዲስ ኮደር' የተሰኘ ፕሮጀክት ነበራት።
ከዚህ በፊትም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተካሄደ የአይሲቲ ኮንፈረንስም ተሳትፋለች።
ከኢትዮጵያ የወጡ የሰው ሠራሽ ልህቀት ባለሙያዎችን በብላክ ኢን ኤአይ እንዳካተተችም ትናገራለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሠራሽ ልህቀት እየታወቀ መምጣቱን የምታምነው ትምኒት "ዘርፉ መታወቅ እየጀመረ ነው። ግን የተዋቀረ አካሄድ መኖር አለበት። ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት እቅድም መኖር አለበት። ሰዎች ወደ ቴክኖሎጂው እንዲገቡ እድል መስጠትም አለብን" ትላለች።
በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እንዲገቡ መንገዶች መመቻቸት እንዳለባቸው ትጠቁማለች።
"ሰዎች የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ድርጅት እንዲጀምሩ ወይም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲመጡ መደረግ አለበት። በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ የሚሆኑ ተቋማት ቢበራክቱ ጥሩ ነው። መንግሥት ገንዘብ የሚሰጠው የጥናት ተቋም ያስፈልጋል። የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች በደንብ እየተከፈላቸው በትኩረት ጥናት እንዲሰሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።
ጉግል ውስጥ የተፈጠረው ምንድን ነው?
በጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት የሥነ ምግባር ቡድን አጋር መሪ የነበረችው ትምኒት፤ ከጉግል እንደተባረረች ያስታወቀችው በትዊተር ገጿ ነበር።
ትምኒት እንዳለችው፤ በሰው ሠራሽ ልህቀት ዘርፍ ላለው መድልዎ ትኩረት እንዲሰጥና በዘርፉ እምብዛም ውክልና ያላገኙ ሰዎች እንዲቀጠሩ የሚያሳስብ ኢሜል ከላከች በኋላ ነው እንደተባረረች የተነገራት።
ዜናውን እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያሉት ግዙፍ የአሜሪካ የሚዲያ ተቋማት ይዘውት ወጥተዋል።
በሰው ሠራሽ ልህቀትና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሠሩ እውቅ ባለሙያዎች የትምኒትን መባረር በመቃወም ትዊተር ላይ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
#ISupportTimnit እና #BelieveBlackWomen በሚሉ ሁለት ሀሽታጎች የጉግል ሠራተኞችን ጨምሮ በርካቶች ከትምኒት ጋር አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በሰው ሠራሽ ልህቀት ውስጥ ካሉ ጥቂት ጥቁር ሴቶች አንዷ የሆነችው ትምኒት መባረሯ በጉግል አመራሮችና መድልዎን የሚቃወሙ ሠራተኞች መካከል የተፈጠረው ውጥረት አንድ ማሳያ ነው ተብሏል።
ከቀናት በፊት ኤምአይቲ ባወጣው ዘገባ መሠረት ለትምኒት መባረር ምክንያት የሆነው ጥናት "On the Dangers of Stochastic Parrots: Can Language Models Be Too Big?" ይሰኛል።
አራት የጉግል ሠራተኞችን ጨምሮ በስድስት ባለሙያዎች የተጻፈ ነው።
ጥናቱን የተመለከተ ውይይት ላይ እንድትሳተፍ ከተጋበዘች በኋላ ጽሑፍ ውድቅ እንድታደርገው ትዕዛዝ እንደተሰጣት ትምኒት ተናግራለች።
የጉግልን ውሳኔ ያልተቀበለችው ትምኒት፤ ከጥናቱ ላይ ስሟን ለማውጣት ለድርጅቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጧን እና ጉግል ግን በምላሹ በገዛ ፍቃዷ ሥራዋን መልቀቋን እንደሚቀበል በመግለጽ እንዳባረራት ተናግራለች።
ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ አለመልቀቋንና የጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት ምርምሮች ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ ጄፍ ዲን እንዲሁም ሌሎችም የተቋሙ አመራሮች እንዳባረሯት አስረድታለች።
ከቀድሞውም በተቀጣሪዎቹና በሌሎችም የሰው ሠራሽ ልህቀት ባለሙያዎች ትችት የሚሰነዘርበት ጉግል፤ ትምኒትን ማባረሩ ወቀሳውን አብዝቶበታል።
የጉግል ሠራተኞች፤ ለፍትሐዊ ቴክኖሎጂና አካታችነት የቆመችው ትምኒት መባረሯ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ውስጥ ያለውን መድልዎና ጭቆና አደባባይ ያወጣ ነው ብለዋል።
ትምኒት ከሥራ ውጪ. . .
ትምኒት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደተናገረችው፤ ፒያኖ መጫወት ታዘወትራለች። ትምህርት ቤት ሳለችም ፒያኖ ተምራለች።
"የምወደው ምግብ ሽሮ በጥቅል ጎመን ነው። ጣፋጭ ነገር በተለይም ቸኮሌት እወዳለሁ። ቡና በወተት እወዳለሁ። ሁሌ ጠዋት ስነሳ ቡና በወተት እጠጣለሁ" ትላለች።
'ብሮድ ሲቲ' የተባለውን ተከታታይ ፊልምና 'ደይሊ ሾው ዊዝ ትሬቨር ኖሀ' እንደምትከታተልም ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።
ትምኒት ከፌስቡክ እና ትዊተር ውጪ፤ 'ስታክ ኦቨር ፍሎ'፣ 'ሬድዮ ላቭ ፖድካስት' እና 'አፍሪካ ኢዝ ኤ ካንትሪ' የተባሉ ድረ ገጾችን ትከታተላለች።
የምታደንቃት ሳይንቲስት የሁለት ጊዜ ኖቤል ተሸላሚዋ ሜሪ ኪዩሪ (ማዳም ኪዩሪ) ናት።
'just do it!' እጅግ የምታምንበት አባባል ነው።
"ሰዎች በተደጋጋሚ እንዲህ ባደርግ ከማለት ማድረግ አለባቸው። ሰዎች አቅማቸውን አያውቁም። የይቻላል መንፈስ ካላቸው ግን ያደርጉታል" ትላለች ትምኒት።