ትምኒት ገብሩ ፡ የጉግል ሠራተኞች ከሥራዋ ከተባረረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ጎን መቆማቸውን ገለጹ

በመቶዎች የሚቆጠሩ የጉግል ሠራተኞች በድርጅታቸው ከሥራዋ የተባረረችውን ትውልደ ኢትዮጵያዊት ታዋቂ የቴክኖሎጂ ተመራማሪዋ ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) የሚደግፈውን ደብዳቤ በመፈረም ከጓኗ መቆማቸውን አሳወቁ።

የአርቴፌሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ ልህቀት) ተመራማሪዋ ትምኒት፤ ከቀናት በፊት እንዳሳወቀችው ጉግል ከሥራዋ ያባረራት "ድርጅቱ ትኩረት የተነፈጋቸው ድምጾችን ያፍናል" በማለት ለሥራ ባልደረቦቿ የኢሜል መልዕክት ከላከች በኋላ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጉግል ባልደረቦች በእርግጥም የዓለማችን ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ጉግልን በዘረኝነትና መልዕክቶችን ቀድሞ በመመርመር (ሳንሱር) የሚከሰውን ደብዳቤ በመፈረም ከትምኒት ጎን ቆመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጉግል በትምኒት ላይ የወሰደውን እርምጃ በመቃወም የትዊተር ተጠቃሚዎች ከትምኒት ጎን መቆማቸውን #ቢሊቭብላክዊመን [#BelieveBlackWomen] በሚለው መሪ ቃል ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው።

ነገር ግን ጉግል ትምኒት ከሥራዋ ስለመባረሯ ያቀረበችውን ምክንያት አስተባብሏል።

ዶ/ር ትምኒት በቴክኖሎጂው ዘርፍ እጅግ ትኩረትን ባገኘው በሰው ሰራሽ ልህቀትና ተያያዥ በሆነው የሥነ ምግባር ዘርፍ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈች ተመራማሪ ነች።

በተለይ የፊት ገጽታን በሚለየው የፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂ ወደ አንድ የዘር ቡድን ማተኮርን በተመለከተ ባከናወነችው ሥራ በስፋት ትታወቃለች። በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ጥቁሮችን ያካተተ ሥራ አለመስራታቸውን አጥብቃ ተችታለች።

ትምኒት ካከናወነቻቸው በርካታ ታዋቂ የምርምር ሥራዎች መካከል በአንዱ አብራት የሠራችው ጆይ ቦላምዊኒ በሰጠችው ምስክርነት "ትምኒት ከጉግል ከፍ ያለ ነገር ማግኘት ይገባት ነበር" ብላለች።

"ትምኒት በሰው ሰራሽ ልህቀት ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ሥነ ምግባርን የተከተሉ፣ ጥልቀት ኖሯቸው አስተማማኝነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን በድፍረት ስለጠየቀች ከሥራዋ መባረሯ በዘርፉ ጉግል ያለውን ተአማኒነት የሚጎዳ ነው" በማለት የትምኒትን መባረር ተቃውማለች።

ጨምራም ትምኒት በሰው ሰራሽ የልህቀት ዘርፍ በኩል ላበረከተችው አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን "የእኩልነት ጥያቄን በትህትናና በልበ ሙሉነት በማንሳቷ ውለታዋ አለብን" ስትል ተናግራለች።

ዶ/ር ትምኒት ከምትሰራበት ጉግል ጋር ስለተፈጠረው ነገር እንደተናገረችው፤ እረፍት ለመውጣት እየተዘጋጀች ባለበት ጊዜ ከባልደረቦቿ ጋር ስላዘጋጀችው አንድ የምርምር ጽሁፍ በሚወያይ ስብሰባ ላይ እንድትሳተፍ ተጋበዘች።

በዚያ ውይይት ላይ በምርምር ያዘጋጀችውን ጽሁፍ ውድቅ እንድታደርገው ትዕዛዝ እንደተሰጣትና ጉግልም በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ዝግጁ እንዳልነበረ ገልጻለች።

በመልዕክቱ ላይም "በዚህ ድርጅት ውስጥ ዕውቅናና ዋጋ የተሰጠን ሰዎች ስላልሆንን በጉዳዩ ምንም አይነት ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ፍላጎት የለም" በማለት አስፍራ ነበር።

ጨምራም "ምንም አይነት ውጤት ስለማይኖረው እያዘጋጃችሁት ያለውን ሰነድ መጻፍ አቁሙ" ብላም ነበር።

የጉግልን ውሳኔ ያልተቀበለችው ዶ/ር ትምኒትም ከምርምር ጽሁፉ ላይ ስሟን ለማውጣት ለድርጅቱ ቁልፍ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ የማይሟሉ ከሆነ የራሷ ውሳኔ ላይ እንደምትደርስ አሳውቃ ነበር።

ነገር ግን ከጉግል የተሰጣት ምላሽ "ጉግልን ለመልቀቅ ውሳኔሽን እናከብራለን . . . በዚህም መሰረት የሥራ መልቀቂያሽን ተቀብለነዋል" በማለት ለሥራ ባልደረቦቿ የጻፈችው ኢሜል የድርጅቱን ደንብ የማይከተል መሆኑን በመግለጽ ሥራዋን በቶሎ እንድትለቅ የሚል ነበር።

ትምኒትም ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ ሳይሆን የለቀቀችው የጉግል የሰው ሰራሽ ምርምሮችን የሚመራው ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ በሆነው ጄፍ ዲን ከሥራዋ እንደተሰናበተች በመግለጽ ትዊት አድርጋ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆነ።

"የጉግል ሥራ አመራር በእኔ ላይ እንደወሰነ እገምታለሁ" ብላለች።

የጉግል ከፍተኛ ኃላፊ የሆነው ጄፍ ዲን በኢሜል በሰጠው ምላሽ ስለትምኒት ከሥራ መሰናበት "በርካታ በግምት ላይ የተነመሰረቱ የተሳሳቱ ነገሮች አሉ" በማለት ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል።

ዲን እንደሚለው፤ በዶ/ር ትምኒት የተዘጋጀው የምርምር ወረቀት "ከማቅረቢያው ጊዜ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የገባ ስለሆነ ጉግል ጽሁፉን የሚገመግምበት በቂ ጊዜ አልነበረውም" ጨምሮም "ወረቀቱ በርካታ አስፈላጊ ምርምሮችን ችላ ያለ ነው" ብሏል።

ትምኒትም በኢሜል በሰጠችው ምላሽ፤ "በሥራዋ ላይ ለመቆየት፤ ምርምሩን በመገምገም አስተያየት የሰጡና በግምገማው የተሳተፉ ሰዎች ማንነት እንዲሁም የሰጡት አስተያየት እንዲገለጽ ጠየቀች። ሌሎች መሟላት አለባቸው ያለቻቸውን በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችንም አስቀመጠች። የጠየቀቻቸው ነገሮች የማይሟሉ ከሆኑ ጉግልን እንደምትለቅ በማሳወቋ እኛም ውሳኔዋን ተቀብለነዋል" ብሏል።

የትምኒትና የታዋቂው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ውዝግብ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎችና የታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ርዕስ ሆኗል።