የፍሪዳ ካህሎ የጥበብ ስራ በጨረታ 34.9 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሜክሲኳዊቷ አርቲስት ፍሪዳ ካህሎ ሥዕል በጨረታ በ34.9 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።
በኒውዮርክ በሚገኘው ሶቴቢ የጨረታ አቅራቢ ድርጅት የቀረበው ይህ ስዕል ሽያጭ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል ተብሏል።
በላቲን አሜሪካ የስነ ጥበስ ስራም በጨረታ የተከፈለ ከፍተኛ ዋጋ ነው።
ክብረ ወሰኑ ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው ለብዙ አስርት ዓመታት ውዥንብር በተሞላበት ግንኙነት የነበራት ሌላኛው አርቲስት የዲያጎ ሪቬራ ስራ ነው። የዲያጎ ስራ በአውሮፓውያኑ 2018 በ9.76 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።
'ዲያጎ ያ ዮ' የሚል ስያሜ የተሰጠው የፍሪዳ ስዕል በመጨረሻ ከሰራቻቸው የራሷ ምስሎች አንዲ ነበር።
ይህ ስራ እያለቀሰች ያለች ፍሪዳና ባለቤቷ ሪቬራ ከአይኖቿ በላይ ተስሎ ያሳያል።
የስዕል ስራውን ያቀረበው ሶቴቢስ ማክሰኞ በነበረው ጨረታ " እስካሁን ለጨረታ ከቀረቡት የፍሪዳ ስራዎች በጣም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው" ሲል ገልፆታል።
ስዕሉን የገዛው በአርጀንቲና ሙዚየም ያቋቋመው ኤድዋርድ ኤፍ ኮሳንቲኒ እንደሆነም ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም ይሄው ስዕል ለመጨረሻ ጊዜ በጨረታ የተሸጠው በአውሮፓውያኑ 1990 ሲሆን ዋጋውም 1.4 ሚሊዮን ዶላር ነው።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ ሰዓሊዎች አንዷ የሆነችው ፍሪዳ የሰውን ልጅ ህመምና መገለልን በሚያንፀባርቁ የራሷ ምስሎች ታዋቂነትን አትርፋለች።
ፍሪዳ የኖረችው በአውሮፓውያኑ ከ1907 እስከ 1954 ሲሆን በኪነ ጥበብ ዘርፉም የሜክሲኮን ባህል በኩራት አስተዋውቃለች።
የጥበብ ስራዎቿ ከሰውነቷ ጋር ያላት በህመም የተሞላ ግንኙነት በተለይም በልጅነቷ በፖሊዮና በአውቶብስ አደጋ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ መሆኗም ይንፀባረቃል።












