አሜሪካዊው ህጻን በዓለም ያለጊዜው በመወለድ ክብረ ወሰን ሰበረ

ከርቲስ ሚንስ

የፎቶው ባለመብት, University of Alabama at Birmingham

ለ21 ሳምንታት ከአንድ ቀን በእናቱ ሆድ የቆየው አሜሪካዊው ጨቅላ ያለ ጊዜው ተወልዶ በህይወት በመቆየት የዓለምን ክብረወሰን በመስበር በጊነስ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሰፈረ።

ኩርቲስ ሚንስ የተሰኘው ይህ ህጻን ባለፈው ዓመት በአሜሪካ አላባማ ግዛት ውስጥ ሲወለድ 420 ግራም ይመዝን ነበር። ህጻኑ አንድ ዓመት ከአራት ወር በህይወት በመቆየቱ ነው ክብረ ወሰኑን የተቀዳጀው።

የህጻኑ እናት መንትዮችን ከወለደች በኋላ አንደኛው ጨቅላ በተወለደ በማግስቱ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ኩርቲስ የመትረፍ እድሉ አንድ በመቶ ነበር። ኩርቲስ 275 ቀናት በሆስፒታል ውስጥ ከተደረገለት ክትትል በኋላ በህይወት ለመቆየት ችሏል።

"በመጨረሻም ልጄን ወደ ቤት መውሰድ እና ታላላቆቹ ልጆቼ በድንገት ሲያዩት የነበረውን ቅጽበት ሁልጊዜ የማስታውሰው ነገር ነው" ስትል ወላጅ እናቱ ተናግራለች።

ኩርቲስ አሁንም በተጨማሪ የመተንፈሻ እርዳታ እንዲሁም የመመገቢያ ቱቦ አማካይነት በህወይወት ያለ ቢሆንም ሐኪሞች ግን መልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ጨቅላው ከናቱና ከዶክተሩ ጋር

የፎቶው ባለመብት, University of Alabama at Birmingham

በአላባማ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና የማዋለድ ሂደቱን የመሩት ሐኪም ዶ/ር ብራያን ሲምስ "በዚህ ሥራ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ስቆይ እንዲህ ያለጊዜው ተወልዶ በዚህ ልክ ጠንካራ ልጅ አላየሁም። ኩርቲስ የሆነ የተለየ ነገር አለው" ሲሉ ለጊነስ የዓለም ክብረወሰን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ክብረወሰኑን ይዞ የቆየው ህጻን በ21 ሳምንት ከሁለት ቀኑ ነበር የተወለደው። ክብረ ወሰኑ ለ34 ዓመታት የቆየ ነበር።