በኮሎምቢያ እጅግ ተፈላጊው የዕፅ አዘዋዋሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኮሎምቢያ እጅግ ተፈላጊው የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ እና የአገሪቱ ትልቁ የወንጀለኞች ቡድን መሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ዳይሮ አንቶንዮ ኡሱጋ አሊያም በቅፅል ስሙ ኦቶኒዬል የኮሎምቢያ ምድር ጦር፣ አየር ኃይልና ፖሊስ ተባብረው ባካሄዱት ተልዕኮ ነው ሊያዝ የቻለው።
መንግሥት ሰውዬው ያለበትን ለጠቆመ 800 ሺህ ዶላር ሽልማት እከፍላለሁ ብሎ ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር። አሜሪካ ደግሞ ያለበትን ለሚያውቅ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ማለቷ ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ኢቫን ዱክዌ በቴሌቪዥን መስኮት ባስተላለፉት መልዕክት የሰውዬውን መያዝ አድንቀዋል።
"ይህ በአገራችን ዕፅ ለሚያዘዋውሩ ሰዎች ትልቅ ኪሳራ ነው። ይህን ጉዳይ የማነጻጸረው በ1990ዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋለው ፓብሎ ኤስኮባር ጋር ነው" ብለዋል።
ኦቶኒዬል የተያዘው በሰሜን ምዕራብ ኮሎምቢያ በምትገኘው አንቲኩያ ግዛት፤ ከፓናማ ድንበር ብዙም ሳትርቅ ካለች የገጠር መንደር ውስጥ ተደብቆ ሳለ ነው።
የኮለምቢያ ጦር ኦቶኒዬል በካቴና ታስሮ በወታደሮች ተከቦ ያለበትን ፎቶ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
የ50 ዓመቱን የፅዕ አዘዋዋሪዎች ቡድን አለቃን ለመያዝ በቅርብ ዓመታት የተለያዩ ተልዕኮዎች ቢሞከሩም እስካሁን አልተሳኩም ነበር።
ኦቶኒዬል 'ገልፍ ክላን' ተብሎ የሚታወቀው የዕፅ አዘዋዋሪዎች ቡድን መሪ የሆነው የቀድሞው የቡድኑ አዛዥ የነበረው ወንድሙ ከ10 ዓመት በፊት በፖሊስ ከተገደለ በኋላ ነው።
የኮሎምቢያ ፀጥታ አካላት ይህን የዕፅ አዘዋዋሪዎች ቡድን በአገሪቱ ያለ አደገኛ የወንጀለኛ ቡድን ሲሉ ፈርጀውት ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ ይህ ቡድን "እስከ አፍንጫው የታጠቀ እና እጅግ አመፀኛ" ሲል ይፈርጀዋል።
ቡድኑ በበርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያለውና ከዕፅ አልፎ ሰዎችንና የጦር መሣሪያ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውር ነው።
ቡድን 1800 የሚሆኑ የታጠቁ አባላት እንዳሉት፤ እኒህ አባላት ደግሞ የቀኝ ዘመም አስተሳሰብ አራማጆች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
የዚህ ቡድን አባላት የሆኑ ሰዎች ከዚህ ቀደም ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ሆንዱራስ፣ ፔሩና ስፔን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ይህ የወንጀለኞች ቡድን አደንዛዥ ዕፅ ከኮሎምቢያ እስከ አሜሪካ እንዲሁም ሩሲያ ድረስ እንደሚያዘዋውር ይታወቃል።
የኮሎምቢያ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በወሰደው እርምጃ በርካታ የቡድኑ አባላት ወደ ገጠር ሄደው ተደብቀዋል ይላል።
አሁን በቁጥጥር ሥር የዋለው ኦቶኒዬል ዕፅ ወደ አሜሪካ በመላክ፣ የፖሊስ አባላትን በመግደልና ሕፃናትን በመመልመል ክስ ይቀርብበታል ተብሏል።
ሰውዬው ከዚህ ቀደም አሜሪካ ውስጥ ተከሶ ስለነበር ምናልባት አሁን ለአሜሪካ ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል እየተባለ ነው።












